በኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው በየዘርፎቹ በርካታ ለውጦችን ማምጣት ችለናል- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
በኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው በየዘርፎቹ በርካታ ለውጦችን ማምጣት ችለናል ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ፤ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ሲከናወኑ የነበሩ ሪፎርሞች በከፍተኛ ደረጃ ኢኮኖሚያችን ጽኑ ሆኖ እንዲቆይ እንደ ሀገር አግዘዋል ብለዋል፡፡
ጠንካራ ወይም ጽኑ ኢኮኖሚ የሚለካበት አንዱ መስፈርት በችግርና ኢ-ተገማች በሆኑ አደጋዎች ጊዜ ተቋቁሞ የማለፍ አቅም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የመጡትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራዎች ከለውጡ በፊት ከነበረው ጋር በማነጸጻጸር በማሳያም አመላክተዋል፡፡
በማመላከቻቸውም አስቀድመው፣ በሀገራችን ላለፉት 11 ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መልሶ ክለሳ እንዳልተካሄደበት ጠቁመው፤ በዓለም አቀፍ ፋይናንሺያል ኤጀንሲስ መስፈርት መሰረት አንዳንድ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ከገበያው ሊወጡ ስለሚችሉና አዳዲስ እንቅስቃሴዎች ሊጨመሩ ስለሚችሉ የተጨመረውን ለማካተትና የወጣውን በገበያ ላይ በቂ ሚና የማይጫወተውን ለመቀነስ ቢበዛ በየአምስት ዓመቱ ኢኮኖሚዎች መከለስ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
መንግስት ግን ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ከአንድ ዓመት በላይ የወሰደ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ያሳተፈ በጣም ሰፊ የጥናት ሥራ በስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እና በዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ የኢኮኖሚ ክለሳ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ በዚህ የክለሳ ሥራ ውስጥ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ከለውጥ በኋላ በሪፎርም አዳዲስ የተካተቱ ኢኒሼቲቮችን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን መልክ እንዳለው ለማየት ዕድል ሰጥቷል፡፡
ለአብነትም ዲጂታል ኢኮኖሚ ወይም የሞባይል ገንዘብ ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ አይታወቅም ነበር፡፡ ዛሬ አጠቃላይ ዲጂታል ኢኮኖሚ በትሪሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ያንቀሳቅሳል ሲሉ በማብራሪያ አስደግፈው ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማሻሻያው ያመጣውን ለውጥ በዘርፎች ለይተው በማሳያነትም አቅርበዋል፡፡ በዚሁ መሰረት ከለውጥ በፊት ከተሞች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ስላልነበሩ በከተሞች አካባቢ የኮሪደር ልማት የሚባል እንቅስቃሴ አለመኖሩን፣ አሁን ግን በኮሪደር ልማት መመራታቸውን አስገንዝበዋል፡፡
በግብርናው ረገድ በክላስተር አርሶ አደሮች መሬቶቻቸውንና ጉልበታቸውን ደምረው የተሻለ ምርትና ምርታማነት እንዲያገኙ የሚደረገው አሰራር የሚጨበጥ ውጤት ያመጣ ቢሆንም በነበረው አለካክ በእያንዳንዱ ማሳ ምን ያክል ምርት እንደምናገኝ በቂ ቆጠራ ማካሄድ ይፈልግ ነበር በማለት አሁን ከመጣው ለውጥ ጋር በማስተሳሰር ተናግረዋል፡፡
ከሌማት ትሩፋት አንጻር በተለይም በዶሮ፣ በእንቁላል፣ በወተት፣ ከፍተኛ እመርታ የመጣ ቢሆንም ከዚህ ቀደም አዲሱን አሰራር ለመለከት የሚያስችል ስርዓት እንዳልነበረና አሁን ግን በዚሁም ማሻሻያ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢንደስትሪ አንጻር የለውጥ ምልከታቸውን ያስቀመጡ ሲሆን፤ በመንግስት የነበሩ ኢንደስትሪ ፓርኮች ከለውጡ በፊት ሐዋሳ፣ ኮምቦልቻ እና መቀሌ ብቻ እንደነበሩና አሁን ግን በመንግስትና በግል ከ15 በላይ ትላልቅ የኢንደስትሪ ፓርኮች መገንባታቸውን፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪውም ዕድገት ማሳየት መጀመሩን አመላክተዋል፡፡
ከኢነርጂ አኳያም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለምሳሌ በንፋስ የአሰላና የአይሻ የነፋስ ፕሮጀክቶች፤ በግድብ ሕዳሴ፣ ገናሌ እና ዳዋ ግድቦች ተጠናቅቀው ተመርቀዋል ያሉ ሲሆን፤ ከሶላር አንጻር በርከት ባሉ የገጠር የኮሪደር ልማት እንዲሁ የሶላር ሲስተም እየተገነባ እንደሚገኝ አብራርተዋል ከዚህ በፊት ግን እነዚህን የኢነርጂ ግብዓቶች በበቂ ደረጃ ታሳቢ የሚያደርግ የኢኮኖሚ አለካክ ስርዓት እንዳልነበር በማስረዳት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአረንጓዴ አሻራ፣ በቱሪዝም እና በሌሎችም ዘርፎች በኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ የመጣውን ለውጥ ከቀድሞው ጋር በማነጻጸር አመላክተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኢያሱ ታዴዎስ

More Stories
የግብርናው ዘርፍ ለጂዲፒ ካለው ድርሻ አኳያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢንደስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፎች ተበልጧል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ኢትዮጵያን ማወክ ለሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች
ሠላምና ይቅርታን በሚመለከት