“ውትድርና ሁሉንም ነገር አስተምሮኛል”

በደረሰ አስፋው

በውትድርናው ዓለም ለ30 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ በተለያዩ ግንባሮች ተሳትፈው ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡

ከ1984 ዓ.ም ጡረታ በኋላ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ንጋት ኮከብ ቀበሌ መኖሪያቸው አድርገዋል። በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት ባለታሪካችን በከተማ አስተዳደሩ መሃል ክፍለ ከተማ ንጋት ኮከብ ቀበሌ በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች በመሳተፍ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛል፡፡

ዛሬም ጉልበታቸው አልደከመም፡፡ መቶ አለቃ ጥበቡ ሰናይ ይባላሉ፡፡ በ1931 ዓ.ም በቀድሞው ወሎ ጠቅላይ ግዛት ወረኢሉ አውራጃ ደጎል ወረዳ ተወልደዋል። አብዛኛው የሕይወት ዘመናቸውን ያሳለፉት ግን በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በመዘዋወር ነው። ቤተሰቦቻቸው የቤተ ክህነት አገልጋዮች ናቸው፡፡ ለአገልግሎት ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ እሳቸውም የዚሁ አካል ነበሩ፡፡

ከልጅነታቸው ጀምረው ኢትዮጵያን ከሰሜን እሰከ ደቡብ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ቃኝተዋታል። የመጀመሪያ ማረፊያቸው የነበረውም ኦሮሚያ ክልል አምቦ ገርጀዳ ስላሴ እንደነበር ያስታውሳሉ። የቤተሰቡ አራተኛ ልጅ የሆኑት ባለታሪካችን የቤተ ክህነት አገልጋይ ከነበሩት ወላጅ አባታቸው ከፊደል ቆጠራ እስከ ቅስና ትምህርት ቀስመዋል፡፡ በመደበኛ ትምህርትም እስከ 4ኛ ክፍል ተምረዋል። ከ1948 ዓ.ም ጀምረው በመንፈሳዊ አገልግሎት በኦሮሚያ፣ አዲስ አበባና ደብረዘይት አብያተ ክርስቲያናትን በመትከል ጭምር አገልግለዋል። ከመንፈሳዊ አገልግሎቱ በተጨማሪ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በመዘዋወር መንፈሳዊ አስተማሪነት በርካታ ዲያቆናትንና ቀሳውስትን አፍርተዋል፡፡ እነዚህ የመንፈስ ልጆቻቸውም በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የአገልግሎት ኃላፊነቶችን እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

መቶ አለቃ ጥበቡ መተዳደሪያ የሚሉት መንፈሳዊ አገልግሎት ግን በጀመሩት ልክ አልቀጠለም፡፡ ልጅ ሆነው የሚመኙት አንድ ሙያ ወደ ቀልባቸው እየመጣ አላስተኛ አላቸው፡፡ ወታደሮች የወታደር ልብስ ለብሰው ሲመለከቱ ይማረኩ ነበር፡፡ ቤተሰብም “አንተ አድገህ ጥሩ ወታደር ነው የምትሆነው” የሚሏቸው ፍላጎታቸውን ይበልጥ አነሳሳው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎቱን እርግፍ አድርገው ትተዉት ወደ ወታደርነት ሙያ አማተሩ፡፡ በአንዳንድ ተቋማት የነጻ አገልግሎት ስራ ጀመሩ፡፡ ከሰዎች ጋር ለመተዋወቅ ዕድል ፈጠረላቸው፡፡ በ1954 ዓ.ም በ18 ዓመታቸው ምኞታቸው እውን ሆኖ በፈቃዳቸው ወደ ውትድርና ገቡ፡፡ በፍቼ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ለ7 ወር የኮማንዶ ወታደራዊ ስልጠና አጠናቀቁ። በ4ኛው ክፍለ ጦር ቅጥር ፈጽመው በ1955 ዓ.ም ወደ ነጌሌ ቦረና ተመደቡ፡፡ የኮሪያ ሠላም አስከባሪ ዘማቾች ሲመለመሉ እሳቸውም የዚሁ እድል ተጠቃሚ ለመሆን ቢያስቡም በአገልግሎት ዘመን ማነስ አልተሳካም። ባለመሳካቱም መቆጨታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በውትድርና አገልግሎታቸው በግንባር ተሰልፈው የተዋጉት በኬኒያ አዋሳኝ ድንበር ነው፡፡

ሀገርን ከሰርጎ ገቦች ለመከላከል በሚል ምደባውን አግኝተው ወደዛው አቀኑ፡፡ በ1969 ዓ.ም የሶማሌ ወረራ ከነበሩበት ግንባር በመዘዋወር በ14ኛው ሻለቃ በ4ኛው ክፍለ ጦር በባሌ፣ ድሬዳዋ፣ በሀረር፣ ጎዴ እና ሌሎች አውደ ውጊያዎች ወታደራዊ ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡ በጸሀፊነት፣ በሂሳብ ሰራተኛ፣ የሰራዊቱ ደመወዝ ከፋይ እና በሚንስ ቤቶች አስተዳደር ክፍል በኃላፊነት በማገልገል ላቅ ያለውን የአገልግሎት ጊዜ አሳልፈዋል። በውጊያ ግንባሮች መሳሪያቸውን አንግበው ከሻለቃው ጋር ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ውጊያው ሲፋፋም ወረቀትና እስክርቢቷቸውን በቢሮ አስቀምጠው በውጊያው አውድ ይሰለፋሉ፡፡ ወራሪውን የሶማሌን ጦር ለመደምሰስ በተደረገው ትግል ህዝቡ ለሀገር የነበረው ፍቅር ድንቅ ይላቸዋል፡፡ የህዝቡ ስሜት ዛሬም በህሊናቸው ትውስ ይላቸዋል፡፡ ሀገር ተደፈረች ዳር ድንበሯ ተጣሰ ከተባለ ቀፎው እንደተነካ ንብ ገንፍሎ ይወጣል፡፡ ወታደሩ ቢበላ ባይጠጣ ግድ አልነበረውም ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

የሶማሌው ጦርነት እንደተጠናቀቀ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ተዋግተዋል። ኢህአዲግ አብዛኛውን የሀገሪቷን ክፍል እየተቆጣጠረ ሲመጣ በወታደሮች የተፈጸመውን ግፍ ሲያስታውሱ ያንገሸግሻቸዋል፡፡ የትግል አጋሮቻቸው አጠገባቸው ሲወድቁ ተመልክተዋል። ወታደራዊ ልብሳቸው ተገፎ እራቁታቸውን እንዲሄዱና የግፍ ጽዋን ሲጎነጩ ተመልክተዋል፡፡ ወታደሮች በጠላት እጅ እንዲወድቁ የሚደረገውን የሴራ ተግባርም እንዲሁ፡፡ ወታደሩ ካለምንም ደመወዝ በሚሰጠው ሬሽን ብቻ ነበር የሚዋጋው ሲሉም ነው ያስታወሱት፡፡ በወታደሩ ስነ ልቦና ላይ የፈጠረው ተጽእኖ ከባድ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በችግር መካከል ሆኖ

የሚሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ግን ወደ ኋላ የሚል አልነበረም፡፡ በ1982 ዓ.ም በርካታ አካባቢዎች በኢህአዴግ ቁጥጥር ውስጥ ሆኑ፡፡ በርካታ ወታደራዊ ማዘዣዎች ለጉዳት ተጋለጡ።

ወታደሩ ወደ ኋላ ማፈግፈግ ግድ አለው፡፡ በወጉ የሚመራው አካል ጠፋ፡፡ የመበታተን አደጋ ገጠመው፡፡ እሳቸውም በእግራቸው ከሰራዊት አባላት ጋር ከአንባሰል ግንባር ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ገቡ፡፡ አዲስ አበባ ከቆዩ በኋላ ከሌሎች የሰራዊት አባላት ጋር ሻሸመኔ ካምፕ ቆዩ፡፡ በዚህ ጊዜ ጡረታ ለመውጣት አመለከቱ፡፡ የ30 ዓመታት የውትድርና አገልግሎታቸውም በጡረታ ተቋጨ፡፡ ጡረታ ወጥተው መኖሪያቸው ያደረጉት ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር መሃል ክፍለ ከተማ ንጋት ኮከብ ቀበሌ ነው፡፡ መቶ አለቃ ጥበቡ ከጡረታ በኋላ በሚሰጡት ማህበራዊ አገልግሎቶች በህዝብ ልብ ውስጥ ገብተዋል። ወታደርነት ሁሉንም ነገር እንዳስተማራቸው የሚገልጹት መቶ አለቃ ለዛሬው አገልግሎት እንዳገዛቸውም ነው የተናገሩት። በ1984 ዓ.ም ጡረታቸውን ካስከበሩ ጀምሮ ያልገቡት ማህበራዊ አገልግሎት የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በሀገራችን ተንሰራፍቶ በነበረው ኤች አይ ቪ ኤዴስ መከላከልና መቆጣጠር ስራ ተሳትፈው ያስመዘገቡት ለውጥ የመጀመሪያው የበጎ አገልግሎታቸው ነው፡፡ ሰዎች ሰዎችን በተጸየፉበት፣ ማግለልና መድሎ በገነነበት ክፉ ጊዜ ለሰዎች ርህርሄን አሳይተው ተንከባክበዋል፡፡ “ኦሳ” ከተባለው ድርጅት ጋር በሽታው እንዳይስፋፋ በተደረገው እልህ አስጨራሽ ርብርብ ትጋትን አሳይተዋል፡፡ ጽ/ቤት አቋቁመው እድሮችን በማስተባበር ጭምር ድጋፋቸውን ለግሰዋል፡፡ በበጎ ተግባር የተሰማሩ አካላትን በማሰልጠን የበኩላቸውን ተወጥተዋል። ለትራንስፖርት ከሚሰጣቸው ሃምሳ ብር ውጪ የሚያገኙት ክፍያ አልነበረም፡፡ ያው ለህዝብ ካለቻው ፍቅርና ክብር እንጂ። በሰጡት ነጻ አገልግሎትም ተደጋጋሚ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሰጡት ባለታሪካችን ከጡረታ መልስ የሰጡት ሌላው አገልግሎት በቀበሌያቸው የማህበራዊ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ለረጅም ዓመታት መስራታቸው ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን በዚሁ ስራ ላይ እንዳሉ ሳይዘነጋ፡፡ ብስለት በተካነው የዳኝነት ስራቸው ተጎጂ የነበሩትን እንባ አብሰዋል፡፡ በአከራይ ተከራይ በሚፈጠረው እሰጥ አገባ፣ የተጣሉትን በማግባባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ማህበራዊ ፍርድ ቤት መቅጫ ሳይሆን በማስተማሪያነት ተጠቅመውበታል። በቤተሰብ መካከል የተፈጠሩ ማህበራዊ ምስቅልቅሎሽን በማለዘብ የፈረሰን ጎጆ አድሰዋል፡፡ በትምህርት ቤት በወላጅ መምህራን ህብረት (ወመህ) ሰብሳቢነት የነቃ ድርሻ አበርክተዋል። ንጋት ኮከብ ትምህርት ቤት በ1999 ዓ.ም ሲቋቋም የሳቸው ድርሻ ከፍተኛ ነበር፡፡ የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽን በመከፋፈል ለመማሪያ ምቹ በማድረግ ለዛሬው ትምህርት ቤት መሰረት ጣሉ። በትምህርት ቤቱ የሚገኙት መማሪያ ክፍሎች በእሳቸው ሊቀመንበርነትና ትዕዛዝ የተገነቡ ናቸው። የትምህርት ቤቱ ስያሜንም ያገኘው በእሳቸው ነው፡፡

የትምህርት ቤቱ የተማሪዎች የድንብ ልብስ የእሳቸው ትርጉም ነው፡፡ የትምህርት ቤቱ ስያሜ ዛሬ ድረስ የቀበሌውም ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ በ1992 ዓ.ም የተቋቋመው የአረጋዊያን መህበርን አቋቁመዋል፡፡ ከማቋቋም ባለፈ በሊቀመንበርነት አገልግለዋል፡፡ የመሰረቱት “ቀስተዳመና አረጋዊያን ማህበር” ከ200 እስከ 300 አባላትን ያቀፈ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ጠዋሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋዊያን ከሚደርስባቸው ጉዳት ታድጎ ነበር። ለጎዳና የተዳረጉትን ተቋማትንና ግለሰቦችን በማስተባበር በሚያገኙት ገንዘብ አረጋዊያንን ይረዱበታል፡፡ ማህበሩ ግን ከአቅም ውስንነት የተነሳ የያዘውን ራዕይ ማስቀጠል አልቻለም፡፡ መቶ አለቃ ጥበቡ በገለልተኛ አማካሪነትም እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በቤተሰብ መካከል፣ በጎረቤት እና በአካባቢው የሚፈጠሩ ችግሮችን በእርቅ በመፍታት የሠላም አምባሳደርነታቸውን እየተወጡ ነው፡፡ የተጋጩ አካላትን ከፖሊስ ፈርመው በማውጣት እርቀ ሰላም ይፈጥራሉ። ስለ ሰላም ያገባኛል በሚል በህብረተሰቡ ውስጥ ያስተምራሉ፡፡ “በህብረተሰቡ ውስጥ ታፍነው የሚገኙ በቃላት ሊገለጹ የሚከብዱ ችግሮችን መቅረፍ ከምግብ በላይ እርካታን የሚፈጥር ነው” ሲሉ ነው የገለጹት፡፡ በቅርቡ የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ አካባቢዎች በሚያስገነባቸው የፖሊስ ቅኝት ማዕከላት ግንባታ የእሳቸው ተሳትፎ አልተለየውም። ባለሀብቶችን፣ ነዋሪዎችንና የፖሊስ አባላትን ጭምር በማስተባበር በተገኘው ወደ 250 ሺህ ብር የሚጠጋ ወጪ የተደረገበት ነው። በዚህም በማስተባበርና በመሳተፍ ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡ ይህ ማዕከል በአካባቢው ወንጀልንና ዝርፊያን ለመከላከል ሁነኛ ፋይዳ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡ ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር የክፍለ ከተማና የቀበሌው ኮሚቴዎችን በማስተባበር አቅም ለሌላቸው የሚያደርጉት ድጋፍም ሌላው የበጎ ፈቃድ ስራቸው ነው፡፡ አቅመ ደካሞች አመት በዓሉን ተከፍተው እንዳይውሉ ገንዘብ፣ ዱቄት፣ አልባሳትና ሌሎች ድጋፎችን ያሰባስባሉ፡፡ የገንዘቡ አቅም ከፍ ካለም የእርድ ሰነ ስርዓት በመፈጸም ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡

መቶ አለቃ ጥበቡ በህዝብ ልብ ውስጥ ገብተዋል የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡ “የሀገራችን ወቅታዊ ፖለቲካ የተወሳሰበ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ ይህን ችግር መቅረፍ የሚቻለው በውይይትና በመነጋገር ብቻ ነው። የጦርነት ታሪካችን ሊያከትም ይገባል። በግጭት ሀብት ይወድማል፣ የሰዎች ህይወት ያልፋል፡፡ ማህበራዊ ቀውስ ያስከትላል፡፡ ሀገርን ወደ ኋላ ይጎትታል። በየወቅቱ ከሚነሱ በሽታዎችና ወረርሽኞች ይልቅ ጦርነት ጎድቶናል፡፡ በውትድርና የአገልግሎት ዘመኔም ይህን ተረድቻለሁ፡፡ መንግስትም በሆደ ሰፊነት ለውይይት በሩን መክፈት አለበት” ሲሉም ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ወቅቱ የበዓል ጊዜ ነው፡፡ በሀገራችን አሮጌው ዓመት አልፎ አዲስ ዓመት የምንቀበልበት የዘመን መለወጫ እንቁጣጣሽ የሚከበርበት ጊዜ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ምን ትውስታ አለዎት። የበዓሉ አከባበር ሁነትስ ምን ይመስላል? ስንል ጥያቄ አቀረብንላቸው፡፡ “ያን ጊዜ ስራ ስቀጠር ደመወዜ 18 ብር ነበር፡፡ 18 ብር ግን በርካታ ቁም ነገር የሚሰራበት ነው፡፡ የቁም ከብት አንድ ሁለት ብር እየተባለ የሚገዛበት ነው። ስጋ እንዳሁኑ በልኬት ሳይሆን በግምት ተመድቦ በሁለት ብር የሚገዛበት የበረከት ጊዜ ነበር፡፡ “በዓል ደስታ ነው፡፡

ጎረቤት ከጎረቤቱ ያለው ለሌለው መረዳዳቱ ልዩ ስሜትን የሚፈጥር ነው። አንተ እንዲህ ነህ፣ የዚህ ብሄር ነህ፣ የዚህ ሀይማኖት ተከታይ ነህ የሚሉ አስተሳሰቦች አልነበሩም፡፡ ሰው መሆኑ ብቻ ነው የሚታየው፡፡” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አሁን ላይ ይህ ማህበራዊ ትስስር የቀዘቀዘ ቢመስልም እሳቸው ግን አሁንም አለመልቀቃቸውን ነው የተናገሩት። በዓል ሲያከብሩ ከቤት ተከራዮቻቸው ጋር ተሰባስበው ያከብራሉ፡፡ ጎረቤት ይጠራሉ፡፡ የተቸገሩትን ይረዳሉ፡፡ “አሁን ያለው ትውልድ ጊዜው የፈጠረው ተጽእኖ ቢኖርም ተሳስቦ መኖርን ሊያጎለብቱ ይገባል፡፡ ትውልዱ ቴክኖሎጂው ተጠቃሚ አድርጎታል፡፡

ይህን ለበጎ ዓላማ ሊጠቀምበት ይገባል፡፡ ከውጭ አስተሳሰብና ተጽእኖ መውጣት ይገባል” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በነርስ ሙያ ለበርካታ ዓመታት አገልግለው ጡረታ የወጡትን ባለቤታቸውን ሳያመሰግኑ አላለፉም፡፡ ባለቤታቸው በህይወታቸው የጣሉት አሻራ ከፍተኛ ነው። ስራ አቁመው ከደመወዝ ውጪ ሲሆኑ በሞራል በመደግፍ አግዘዋቸዋል፡፡ አሁን ላይ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በመሳተፍ አብረዋቸው ያገለግላሉ፡፡ መቶ አለቃ ጥበቡ ባቋቋሙት የአረጋዊያን ማህበር ውስጥ በሙያቸው አረጋዊያንን አገልግለዋል፡፡ ጡረታ ሲወጡ 126 ብር ይዘው ነው የወጡት። በ30 ዓመት የውትድርና አገልግሎታቸው አንድም ጉዳት አልገጠማቸው፡፡

በዚህም “እድል ከኔ ጋር ነበረች” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡ መቶ አለቃ ጥበቡ በመሰረቱት ትዳር 9 ልጆችን አፍርተዋል። ልጆቻቸውንም አስተምረው ለቁም ነገር አድርሰዋል፡፡ ከሀገር ውጪ በሀገረ አሜሪካ የሚገኙ አሉ፡፡ በሀገር ውስጥም በህክምና፣ በንግድ ስራ እና በሌሎች የስራ ዘርፎች ተሰማርተዋል፡፡ ዛሬ አቅማቸው በደከመበት ጊዜም ጠዋሪና ደጋፊ ሆነዋቸዋል።