“በትንሹ ምህረት ማድረግ ከለመድክ ለትልቁ በደልም ምህረት ታደርጋለህ” – ዳግማዊ አሠፋ

ዳግማዊ አሠፋ

የዛሬው የንጋት እንግዳችን ወጣት ዳግማዊ አሠፋ ይባላል፡፡ የህግ ባለሙያና ደራሲ ነው፡፡ በ2ዐዐ7 ዓ.ም የአካል ጉዳት በሥራ ላይ እያለ የደረሰበት ሲሆን በብዙ ውጣ ውረድ አልፎ፣ አሁን ከህይወት ልምዱ በመነሳት በህይወት ክህሎት እና በሥነ ልቦና ዙሪያ የምክር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከእርሱ ጋር ባደረግነው ቆይታ ያካፈለንን ተሞክሮ እነሆ ብለናችኋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

በመሐሪ አድነው

ንጋት፡- ልምድህን ለማካፈል ፍቃደኛ ስለሆንክ በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመስግናለሁ፡፡

ዳግማዊ፡- እኔም የጋዜጣችሁ እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ አመሠግናለሁ፡፡

ንጋት፡- በመጀመሪያ ስለትውልድና እድገትህ እናውራ፡፡ ዳግማዊ አሠፋ ማን ነው?

ዳግማዊ፡- አሠላ ነው የተወለድኩት። ቤተሠቤ ወደ ሐዋሣ ከተማ ሲዛወር እኔም ሐዋሳ መጣሁ፡፡ በከተማዋ በሚገኙት አድቬንቲስት እና ማውንት ኦሊቭ በተባሉት ት/ቤቶች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ተማርኩ፡፡ የሁለተኛ ደረጃና መሠናዶ ትምህርቴን ደግሞ በኢቫንጄሊካል ት/ቤት ተምሬ ካጠናቀኩ በኋላ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት እንድማር ደረሰኝ፡፡ አንድ አመት ከተማርኩ በኃላም ወደ ሐዋሣ ዩኒቨርሲቲ ዝውውር በመጠየቅ በዩኒቨርሲቲው በህግ ትምህርት ክፍል በማዕረግ ተመርቄአለሁ፡፡ አሁንም ከህግ ጋር የተያያዘ ሥራ በመሥራት ላይ እገኛለሁ፡፡

ንጋት፡- በተማርክበት ሙያ ለምን ያህል ጊዜ አገለገልክ? ምኞትህስ እስከ ምን ድረስ ነበር?

ዳግማዊ፡- ህግ ስማር ዳኛ ለመሆን ነው የተማርኩት፡፡ ፈርሀ እግዚአብሔር ስላለኝ መማለጃ ጉቦ ወይም የዘር የፖለቲካ እንቅፋት /ፈተና/ ይሆንብኛል ብዬ ስለማላምን ዳኛ የመሆን ፍላጐት ኖሮኝ ነው የተማርኩት፡፡

ዩኒቨርሲቲ እያለሁ ከሦስተኛ እስከ አምስተኛ አመት ድረስ በሐዋሣ ማረሚያ ተቋም፣ በሐዋሣ የመጀመያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በሐዋሣ ዩኒቨርሲቲ ነፃ የህግ ድጋፍ ማዕከላት ነፃ አገልግሎት እሰጥ ነበር፡፡ ከተመረቅኩኝ በኃላ ሥራ የሠራሁት ሦስት ወር ነው፡፡ በዚህ መሃል ነው አደጋ የደረሰብኝ፡፡

ንጋት፡- አደጋው የደረሠብኝ ለምንድን ነው ብለህ ታስባለህ?

ዳግማዊ፡- ይሄ ለፍትህ የተከፈለ ዋጋ ነው። እኔና ጓደኛዬ (በዚህ ጥቃት ህይወቱ ያለፈ) ቁጭ ብለን ስንማከር፤ ይህን ያህል ገንዘብ ጉቦ ተሰጥቷል፣ በቃ እንውሰደውና እንዲህና እንዲያ እናደርግበታለን ብንባባል ኖሮ ይህ አደጋ አይመጣም ነበር፡፡ ለእግዚአብሔርና ለህሊና ስትኖር፣ ለህግና ለፍትህ ስትኖር የሚያጋጥም አደጋ ነው፡፡

በሌላ በኩል ለወንድም ፍቅር የተከፈለ መስዋዕትነትም ነው፡፡ ምክንያቱም ጥይቱ በቅድሚያ የተተኮሰው በጓደኛዬ ላይ ነው፡፡ እርሱን ነው የመታው፡፡ እኔ ተደብቄ ወይም ተሸፍኜ በዝምታ ማለፍ እችል ነበር፡፡ ነገር ግን የወንድሜ ገዳይ እንዳያመልጥ ብሎ ለፍትህና ለእውነት በመጋፈጥ የተከፈለ ዋጋ ነው፡፡ የሆነው ሁሉ ያለምክንያት ነው የሆነው ብዬ አላምንም፡፡

ዛሬ እግዚአብሔር እኔን ተጠቅሞ በእኔ እውቀትና ብቃት ሳይሆን የፈረሱ ትዳሮችን እያቀና ነው፡፡ ራሳቸውን ለማጥፋት ገመድ የሰቀሉ ሠዎች ከገመድ ወርደው ደውለውልኛል፡፡ መርዝ ለመጠጣት የወሰኑ ሠዎች እኔን አይተውና ታሪኬን አንብበው ዳግማዊ እንዲህ ከሆነማ እኛ ለምን ብለው ሃሳባቸውን እንዲቀይሩና ተስፋ እንዲታያቸው እግዚአብሔር እኔን ተጠቅሞ ብዙዎችን አድኗል፡፡

ለበቀል ለተዘጋጁ ሠዎች ይቅርታ ማድረግ ምህረት ዋጋ አለው፡፡ የዚህ ልጅ ህይወት እኛን ቀይሮናል ብለው ከጥፋት መንገድ ተመልሰዋል፡፡ የጓደኛዬን ገዳይ ይቅር ያለ ወላጅ አንተን አይቼ ነው ይቅር ያልኩት ብሎ ደውሎልኛል፡፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ካንተ የህይወት ልምድ ብዙ ትምህርት አግኝተናል የሚሉ የስልክ ጥሪዎች ይደርሱኛል፡፡

ማን ያውቃል ይህ አደጋ እንዲመጣ እግዚአብሔር የፈቀደው ለዚህ አገልግሎት ለዚህ ሥራ አስቦት ከሆነ፡፡ ሆነም ቀረ የምንኖረው አንዴ ነው፡፡ ያቺን የምንኖራትን ኑሮ በአግባቡና በሥርዐቱ ኖሮ ማለፍ ነው ትልቁ ቁም ነገር፡፡

ንጋት፡- የደረሠብህ አደጋ ባይመጣ ኖሮ አሁን ከምሠራው በላይ የተሻለ ነገር እሠራ ነበር ብለህ ታምናለህ?

ዳግማዊ፡- በፍፁም ይሄ አደጋ ባይመጣ ኖሮ ዛሬ የሠጠሁት ለዓለም የሚተርፍ ነገር አይኖርም ነበር፡፡ ዳኛ እሆናለሁ፤ ለተወሰኑ ሠዎች እውነተኛ ፍትህ ልሰጥ እችላለሁ። ለመቶ ለሺህ ሠው ጠበቃ ሆኜ ፍትህ እንዳይዛባ ማገዝ እችል ይሆናል፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ግን በየሠዉ ጓዳ ገብቼ የሠዎችን ህይወት ልቀይርና የተስፋ ምክንያት ልሆን ችያለሁ፡፡ ስለዚህ ይሄ አደጋ ይዞ የመጣው ሌላ ማንነት፣ ሌላ መንገድና ሌላ የመኖር ምክንያት ይዞ የመጣ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡

ንጋት፡- ሠዎች በትንሽ ነገር ቶሎ ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ አንተ ግን ይህን ከባድ አደጋ እንደ አመጣጡ ተቀብለህ ለማስተናገድ ልምዱን እንዴት አዳበርክ?

ደግማዊ፡- ፈተና እንደሠዉ ይለያያል። ዋናው ነገር የምትቀበልበት መንገድ ነው፡፡ የምትቀበልበት መንገድ ደግሞ ከመጣህበት መንገድ ጋር ይገናኛል፡፡ እየገነባኸው የመጣኸው ማንነት፣ እየተሠራህበት የመጣኸው ማንነት ፈተናውን የምትቀበልበትን መንገድ ይወስናል፡፡ ስለዚህ ፈተና ነው ብሎ መቀበልና ከእያንዳንዱ ተግዳሮት /Challenge/ መማር ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ነገር ስታጣ ማጣት የሚፈጥረውን ህመም ትረዳለህ፡፡ ልታዝን ትችላለህ፣ ልታለቅስ ትችላለህ፡፡

እሱ ተፈጥሯዊ ነው ምንም ችግር የለውም፡፡ ከሆነ ጊዜ በኃላ ተመሳሳይ እጦት /ችግር/ ድጋሚ ሲገጥምህ እንደ መጀመሪያው ጊዜ ካዘንክ /ከተሠበርክ/ ግን አልተማርክም። ሁለተኛው ደግሞ ከሌሎች መማርም ያስፈልጋል፡፡ “ብልህ ከሠው ይማራል፤ ሞኝ ደግሞ ከራሱም አይማርም” ይባላል፡፡ እኔ የራሴን ነገር ደብቄ መኖር አቅቶኝ አይደለም። ሁሉንም ነገር ግልፅ አድርጌ የወጣሁት ሠው ከእኔ እንዲማር ነው፡፡ ስለዚህ ከእኔ መፅሐፎች፣ ከእኔ የፈተና መንገዶች መማርና ለነገ ህይወት ስንቅ መሠነቅ የተሻለ ነው፡፡

ንጋት፡- ልጆች እንዲህ አይነት ስብዕና እንዲኖራቸው ወላጆች እንዴት አድርገው ማሳደግ አለባቸው?

ዳግማዊ፡- ወላጆች ልጆቻቸውን በፈተና ውስጥ ማሳደግ አለባቸው፡፡

ንጋት፡- እንዴት?

ዳግማዊ፡- ብዙ ወላጆች ልጆች ካልሲና የውስጥ ሱሪያቸውን እንኳን እንዳያጥቡ ሲያደርጉ እየተንከባከቧቸው ነው የሚመስለው፡፡ ከዚያ ልክ 12ኛ ክፍል ጨርሰው ዩኒቪርሲቲ ሲገቡና ስራም ሲይዙ ሁሉም ነገር ይጨልምባቸዋል፡፡ ያልተማሩትን ከየትም አያመጡም፡፡

ህይወትም ሆነ ያለንባት አለም ነፃ ስጦታ የላትም ሁሉም ነገር በስቃይ ነው የሚገኘው፡፡ ስለዚህ ልጆችን ራሳቸውን እንዲችሉ አድርጐ ማሳደግ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ ወደ እኔ ቢሮ ምክር ፍለጋ ከሚመጡ ሠዎች መካከል ወላጆቻቸውን ያጡ ሠዎች ይገኙበታል። እናት አባት ማጣት ከባድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እናትና አባት ሲኖሩ የልጆቹ እስትንፋስ ሆነው ነው የሚኖሩት፡፡ ልጆች ቀላልም ችግር በገጠማቸው ጊዜ እናት “እኔ ፈታልሀለሁ” ትላለች፡፡

አባት በበኩሉ አይዞህ /ሽ/ እኔ አለሁ አስተካክለዋለሁ . . . ወዘተ ስለሚሏቸው ልጆች ሁሉን ነገራቸውን በወላጆቻቸው ላይ ጥለው ይኖራሉ፡፡ ይህ የወላጆች የአስተዳደግ ጥፋት ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ችግር ሲገጥማው በመጀመሪያ ራስህ/ሽ ሞክር/ሪ፡፡ ካቃተህ/ሽ ነውየምመጣው በማለት የመፍትሔ ሠው እንዲሆኑ በማለማመድ ማሳደግ ነው ያለባቸው፡፡

ይህ ካልሆነ ዞሮ ዞሮ ዳፋው ለሀገር ነው፡፡ የራሳቸውን ችግር መፍታት የማይችሉ ልጆች የሀገር ችግር ይፈታሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ልጆች በፈተና ውስጥ እንዲያድጉ መታገል ጥሩ ነው፡፡

ንጋት፡- ወጣቶች ከአንተ ህይወት ምን መማር ይችላሉ?

ዳግማዊ፡- አንደኛ ቀደም ብዬ እንዳልኩት ስብእናን መገንባት ለሆነ ክፉ ቀን ይጠቅማቸዋል ገንዘብ የምታጠራቅመው በቸገረህ ጊዜ አውጥተህ ልትጠቀመው ነው። ልክ እንደዚያው ጥንካሬህን ስትገነባ ለሆነ ቀን ይጠቅምሀል፡፡ ሁለተኛ ፅናትን መማር ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔ በዚህ ፈተና ውስጥ መፅናት ባልችል ዛሬ ምናልባትም ሞቼ ተቀብሬ ተረስቼ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ ስለዚህ መፅናት ውጤቱ ብዙ ነው፡፡

ሌላው ይቅርታን ከእኔ መማር ይችላሉ። በቀል፣ ጥፋትና መግደል ቀላል ነገር ነው። በተለይ በአሁን ጊዜ መግደልም ማስገደልም በጣም ቀላል ነገሮች ናቸው፡፡ ከባድ ነገር ተሸንፎ ማሸነፍ ነው፤ ይቅርታ ማድረግ ነው፡፡ ምህረት መስጠት ነው፡፡ ይህ ነው በጣም ጥሩ ነገር፡፡ ያንን መማር ይችላሉ፡፡ ለዓላማ መኖር መቻልን ወጣቶች ከእኔ መማር ይችላሉ፡፡ እኔ አሁን የምኖርለት ዓላማ አለኝ፡፡ ጠዋት ጠዋት ከእንቅልፌ የሚቀሰቅሰኝ ዓላማ አለኝ፡፡ ቶሎ ተነስቼ መሥራት የምፈልገው ነገር አለኝ፡፡ ይህንን መማር ይችላሉ፡፡ እምነትንም በፈጣሪ ላይ መደገፍንም ጭምር መማር ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡

ንጋት፡- አንተ ይቅር ማለትን እንዴት ተለማመድከው?

ዳግማዊ፡- እንግዲህ በትንሽ በትንሹ ነው የምትለማመደው፡፡ በአንድ ጊዜ ይህን የሚያክል ነገር ላይመጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከቤተሠብ፣ ከእህት ከወንድም ጋር የሚኖሩ ግጭቶችን የምትፈታበት መንገድ ከሌሎች  ሠዎች ጋር የምትፈታበት መንገድ ከሥራ ባልደረባህ፣ ከት/ቤት ጓደኛ፣ ከእነዚህ ሁሉ ጋር የምትፈታው ነገር ልምድ ነው የሚሆንህ። በትንሹ በትንሹ ምህረት ማድረግን ይቅር ማለትን ስትለምድ በሂደት ለትልቁ ችግርና በደልም ምህረት ታደርጋለህ፡፡ እኔም ጋር እንደዚያው ነው፡፡ ቅድም እንዳልኩህ ለይቅርታ መቼም ከኢየሱስ ክርስቶስ የበለጠ ለማንም አስተማሪ የለም፡፡ ከእርሱ ከተማርን ደግሞ እኛ ያንን እንድንተገብር ነው የታዘዝነው፡፡ ስለዚህ ከኢየሱስ የምማረው ነገር አለ፡፡ ሌሎችም በሀገራችንም ሆነ በውጪ ሀገር የይቅርታ ሠዎች አሉ፡፡

የበደሉአቸውን የገደሉባቸውን ሠዎች ይቅር ያሉ በርካቶች አሉ፡፡ መፅሐፌም ላይ አካትቻቸዋለሁ፡፡ ስለዚህ እነዚህንና መሠል ነገሮችን ወደ ራስ ደግሞ ማምጣት ይቅርታ ለማድረግ እድል ይሠጣል፡፡ ትልቁ ነገር ግን ምንድን ነው የሚሆነው? የሚለውንም ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በበደለኝ ሠው ላይ የአፀፋ በቀል ብወስድ ቀጣዩ ነገር ምን ይሆናል፡፡ ብለህ ስታስብና በግድያው ምንም የምታገኘው ነገር እንደሌለ ስታውቅ ወደዚህ ውሳኔ ትመጣለህ። የእኔም ይቅርታ የመጣው በዚህ መንገድ ነው።

ንጋት፡- የአዲስ ዓመት መልእክት ለወጣቶች ካለህ እድሉን ልስጥህ?

ዳግማዊ፡- ለመስተካከል አዲስ አመትን መጠበቅ አያስፈልግም፡፡ መቼ እንደምንሞት አናውቀውምና አሁንም ጥረትን፣ አሁንም ትግልን አሁንም ማሸነፍን መቀጠል ጥሩ ነው፡፡ አዲስ ዓመት እየመጣልን ነው፤ እድሜ እየተጨመረልን ነው፤ ያ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህን ቀን ለማየት የፈለጉ ብዙ ሠዎች አሉ፡፡ ግን ለዚህ አልታደሉም። ለዚህ ቀን የታደሉ ደግሞ በጣም ብዙ ሠዎች አሉ፡፡ እኛም አዲስ አመት እንድናገኝ ታድለናል ማለት ነው፡፡ አዲስ አመት እንደግለሠብ ራሳችንን የምናይበት አምና ከነበረን ህይወት አንድ ደጃ የምንሻሻልበት ለእርሱ የሚከፈለውን ዋጋ ደግሞ በታማኝነት የምንከፍልበት አመት እንዲሆን ሃሳቤን ምክሬንም አስቀምጣለሁ፡፡

ያሳለፍናቸው ሁለት፣ ሦስት አመት እንደ ሀገር የኪሣራ አመቶች ናቸው፡፡ ደም መፍሰስና ውጊያ ብቻ የነበረባቸው አመታት ናቸው። ይህኛውን አመት እንደ መንግሥትም፣ እንደግለሠብም፣ እንደ ታጣቂም፣ እንደ ቡድንም ቆም ብለን የምናስብበት፣ ይቅር የምንባባልበት፣ ወንድሜ ያንተ መኖር ለእኔ መኖር ነው የምንልበት አመት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ትርጉም የሌለው ሞት የማንሞትበት አመት እንዲሆንልን እመኛለሁ። እግዚአብሔር ፍቅርና ሠላምን ያብዛልን!

ንጋት፡- ፈቃደኛ ሆነህ ሠፊ የህይወት ልምድህን ስላካፈልከን በድጋሚ ከልብ እናመሠግናለን፡፡

ዳግማዊ፡- እኔም አመሠግናለሁ፡፡