“የሚገጥሙን ፈተናዎች ጊዜያዊ እንጂ ነገን እንዳናይ የሚያደርጉ አይደሉም” – ወጣት ገነት በለጠ

በሊዲያ ታከለ

ፈተና ሳይገጥመው ለስኬት የሚደርስ የለም፡፡ በህይወታችን የሚገጥሙን ፈተናዎች ደግሞ ወደ ስኬት የሚመሩን ናቸው፡፡ በብዙ ተፈትኖ የሚመጣ ስኬት ደግሞ የህይወትን ጣዕም በተገቢው እንድንረዳ ያስችለናል፡፡ ለዚህ አመላካች የሆነ የአንዲት አካል ጉዳተኛ ታሪክ ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ፡፡

ገነት በለጠ ቱምቻ ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው በሲዳማ ክልል አለታ ጩኮ ልዩ ስፍራው ሩፎጨንጫ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ነው፡፡

ስትወለድ እንደ አብዛኞቹ ሕፃናት ሙሉ አካል ነበራት፡፡ ከእኩዮቿ ጋር በጨዋታ እየቦረቀችም አድጋለች፡፡ በዚህ በኩል ጥሩ ትዝታ እንደነበራት ታስታውሳለች፡፡

እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም እዛው በትውልድ መንደሯ ከ1ኛ እስከ 8ተኛ ክፍል ድረስ ተምራለች፡፡ ይሁን እንጂ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለች ነበር ዛሬ ላይ ላለባት አካል ጉዳት የተዳረገችው፡፡

በወቅቱ ታላቅ እህቷ መውለዷ ለገነትም ሆነ ለመላው ቤተሰቧ የፈጠረው ልዩ የደስታ ስሜት ነበር፡፡ ገነትም የእህትነት ድርሻዋን ለመወጣት የወለደችውን እህቷን ለመጠየቅ ወደ ቤቷ አቀናች፡፡

ድንገት ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጠረ። ይህንንም ክስተት እንዲህ ስትል ታስታውሳለች፡-

“በወቅቱ በእህቴ በሰላም መገላገል ሁላችንም ደስተኞች ነበርን፡፡ ነገር ግን ደስታው ብዙም አልቆየም፡፡ ወደ ሀዘን ተለወጠ፡፡ አንዲት ላም ከኋላዬ መጥታ ድንገት ወጋችኝ፡፡ እኔም ላሚቷን አላየኋትም ነበር፡፡

“በወቅቱ ስትወጋኝ የወደኩት ከፊት ለፊቴ በነበረው ትልቅ ድንጋይ ላይ ነበር። ከዚያም ጉልበቴ ላይ ከባድ ጉዳት ደረሰብኝ። ምክንያቱም ድንጋዩ የጉልበቴን አጥንት ስለጎዳው፡፡ ያ ጊዜ በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡

“ይሁን እንጂ ቤተሰቦቼ ወደ ቀድሞ ጤናዬ እንድመለስ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ቢሆንም ግን ለእኔ ክስተቱን አምኖ መቀበል ቀላል አልነበረም፡፡ በህይወት የምኖር ሁሉ አይመስለኝም ነበር፡፡

“ነገር ግን ለህክምና በምዘዋወርበት ወቅት ከእኔም በባሰ ችግር ውስጥ የሚያልፉ ወገኖቼን ሳይ መፅናናት ጀመርኩኝ፡፡ እናም ያጋጠመኝን አምኜ መቀበል እንዳለብኝ እና ጉዳቴ ከአላማዬ ሊያሰናክለኝ እንደማይገባ ለራሴ በመንግር እራሴን አበረታታሁ፡፡

“ቢሆንም ግን ጉዳቱ እጅግ ከፍተኛ ስለነበር ለ6 ወራት ያህል ማንኛውንም እንቅስቃሴ የማደርገው እናቴ እያዘለችኝ ነበር። ታላቅ ወንድሜም እህቴን ያግዛት ነበር። በዚህም ጉዳቴ ምክንያት ለአንድ ዓመት ያህል ትምሀርቴን አቋርጬ ነበር፡፡”

ወጣት ገነት የገጠማት የአካል ጉዳት ከባድ ቢሆንም ለችግሯ እጅ መስጠት አልፈለገችም። አስቀድማ ለወደፊት ጠንክራ በመስራት ዓላማዋን ከግብ ለማድረስ የስነልቦና ዝግጅት አድርጋ ነበርና ወደ ተግባር ለመቀየር ቆርጣ ተነሳች፡፡

“የለውጤ መነሻ ያደረግኩት ትምህርቴን ነበር፡፡ እንደ አዲስ መቀጠል ስለነበረብኝ ለ3 ዓመታት ያህል የድጋፍ ጫማ ተጠቅሜ ትምህርቴን ተከታተልኩኝ። እዚያው በትውልድ መንደሬ ነበር ካቋረጥኩበት 8ተኛ ክፍል የቀጠልኩት፡፡ የ2ተኛ ደረጃ ትምህርቴንም ወደ አለታ ጩኮ ተዘዋውሬ በአለታ ጩኮ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት 9ኝና 10ኛ ክፍልን ተማርኩ፡፡

“በወቅቱ ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ ድካም እና ህመም ይሰማኝ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም እንደሚያልፍ ስለገባኝ ነገ የተሻለ ቀን ይመጣል በማለት እራሴን አበረታሁ። የማንም ጥገኛ መሆን በፍፁም አልፈለግኩም። ቢሆንም ግን ትምህርቴን ከጀመርኩ በኋላ ፈተና የሆነብኝ ነገር በዱላ ተደግፎ መሄድ አለመቻሌ ነበር፡፡” ስትልም የገጠማትን ፈተና ታወሳለች፡፡

የገጠማት ፈተና ግን እንዲሁ በዋዛ ያለፈችበት ቢመስልም ብዙ ያስተማራትም ነበር፡፡ ለዚህም ደጋግማ በምልሰት ትቃኘዋለች፡፡ በሃሳብ የነጎደችበትን ትዝታዋን ስታስቃኝም፡-

“አካል ጉዳቱ ያጋጠመኝ የ14 አመት ታዳጊ እያለሁኝ ስለነበር በዱላ ተደግፌ እንኳን መራመድ አለመቻሌ እጅግ አስጨንቆኝ ነበር፡፡ ነገር ግን አንድ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረልኝ፡፡ ቸሻየር የተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት የዊልቸር ድጋፍ አደረገልኝ፡፡

“ሆኖም ግን አንዳንድ ጊዜ ሲደክመኝ ወንድሜን እየጠራሁት በሞተር ሳይክል እያመላለሰኝ ትምህርቴን ተከታተልኩኝ።

እናም የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ተፈትኜ የመሰናዶ መግቢያ ነጥብ ስላላመጣሁ ወደ አለታ ወንዶ አቀናሁ፡፡

“በአለታ ወንዶ በቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ በጨርቃ ጨርቅ የትምህርት ክፍል ትምህርቴን ተከታትዬ ተመረቅኩኝ፡፡” ብላለች፡፡

የገነት ትምህርት የመማር ፍላጎት በዚህ ዓይነት መልኩ ውጤት አምጥቷል፡፡ ሰው ተምሮ ካጠናቀቀ ደግሞ ወደ ስራ ዓለም ማማተሩ አይቀርም፡፡ ስራ የመስራቱ ፍላጎት እያደረ ቢጨምርም የተወሰነ ጊዜ ያለስራ መቀመጡ ግድ ሆነባት፡፡

አንድ አጋጣሚ ግን ይህ ሁኔታ እንዲቀየር ምክንያት ሆናት፡፡ ታላቅ ወንድሟ ወደ ሀዋሳ ሄዳ የተወሰነ ስራ እየሰራች እንድትንቀሳቀስ ጠየቃት፡፡ እሷም አላንገራገረችም፡፡ ወደ ሀዋሳ መጣች፡፡

ታላቅ ወንድሟ የራሱ ሱቅ ነበረውና የእሱን ሱቅ ትጠብቅ ጀመር፡፡ የወንድሟን ሱቅ እየጠበቀች ለአንድ ዓመት ከቆየች በኋላ ሌላ የተሻለ ስራ መስራት እንዳለባት አመነች። ይህ ሃሳቧ ራሷን እንድትችል መንገድ እንደሚከፍትላት ተማምናለች፡፡

ውሳኔዋም ወቅቱን የጠበቀ ነበርና ዕድል ቀንቷት በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተቀጥራ ስራ ጀመረች፡፡ አሁንም እዚያው በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡

ገነት አሁን ስላለችበት ሁኔታ ስትናገር፡-

“የቤት ኪራይም ሆነ ለሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ በተቻለኝ መጠን እራሴ ነኝ ወጪውን የምሸፍነው፡፡ ማንንም ሳላስቸግር እንደ ማንኛውም ሰው በማገኘው ገቢ ራሴን አስተዳድራለሁ፡፡ የምሰራውንም ስራ ቢሆን ከሌሎች ባልደረቦቼ እኩል እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ አካሌ ቢጎዳም አዕምሮዬ ጤነኛ ነው፡፡

“በትምህርቴም ቢሆን ራሴን ማሳደግ ስለነበረብኝ ከስራዬ ጎን ለጎን በመማር ከአትላስ ኮሌጅ በሴክሬተሪ የትምህርት ክፍል በዲፕሎማ ተመርቄአለሁኝ፡፡ ይህ በአንድ ወቅት የመማር ተስፋ ላልነበረኝ ለእኔ ትልቅ ስኬት ነው፡፡

“በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከማገኘው የወር ደመወዝ በተጨማሪ ለወንበር፣ ለአልጋና ለሌሎች ቁሳ ቁሶች የእጅ ስራዎችንም እየሰራሁ ገቢዬን ለማሳደግ ጥረት አደርጋለሁኝ። በቀጣይም እግዚአብሄር ከረዳኝ ከዚህ የተሻሉ ሌሎች ስራዎችን የመስራት ውጥን አለኝ፡፡” ብላለች፡፡

ከዚህ በፊት በሀዋሳ ከተማ መንግስት አደረጅቷቸው የስራ እድል እንደሚፈጥርላቸው ቃል ገብቶላቸው እንደነበር የምትናገረው ወጣት ገነት፣ እስካሁን ድረስ ምላሽ እንዳላገኘች ትገልጻለች። ይሁን እንጂ ከመንግስት ከመጠበቅ ይልቅ በራሷ ጥረት ማድረግን መርጣ አሁን ያለችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡

እንደ እሷ አካል ጉዳት ለገጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መልዕክት አለኝ ትላለች፡-

“ትንሽ ጉዳት ሲያጋጥማቸው ተስፋ ቆርጠው ልመናን አማራጭ ላደረጉት ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት አለኝ።

ሰው ከጠነከረ እና ተስፋ ካልቆረጠ የማያልፈው ፈተና የለም፡፡ አንድ ወቅት በመንገድ ስሄድ ያጋጠመኝ አካል ጉዳተኛ ወጣት ልጅ ሲለምን አግኝቼው፣ ስራ ከሰራ ራሱን መቀየር እንደሚችል አሳምኜው ለስራ ማስጀመሪያ እንዲሆነው ገንዘብ መስጠቴን አስታውሳለሁ። አሁን እሱ በሊስትሮ ስራ ተሰማርቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

“ለሌሎችም ቢሆን ልመና መፍትሄ አይደለም፡፡ ዋናው ራስን አሳምኖ ስራ ለመስራት መዘጋጀት ነው፡፡ ያን ጊዜ ስራው ወደ እኛ ይመጣል፡፡ ዝም ብለን ከተቀመጥን ወይም ልመናን አማራጭ ካደረግን ግን ህይወታችን ሊለወጥ አይችልም፡፡”

በእርግጥም ወጣት ገነት እንደ ተናገረችው እኛ የሰው ልጆች ከችግሮቻችን በላይ ነን። ራሳችንን ለመቀየር በምናደርገው ሩጫ ብዙ መሰናክሎች ይገጥሙናል፡፡ ሆኖም ግን ለገጠመን ችግር መፍትሄ የምናበጀውም እኛው ነን፡፡

ለችግሮቻችን እጅ ሳንሰጥ መፍትሄ አምጪ ሆነን ወደ ስኬት ኮረብታ መውጣት አለብን፡፡ ከራሳችን አልፈን ለሌሎች የምንትረፍ መሆን ይኖርብናል፡፡