ከጐዳና እስከ ባለሙያ

በጌቱ ሻንቆ

“ሢሣይ ሠለሞን እባላለሁ። ይርጋለም ነው የተወለድኩት። ቤተሠቦቼ ሰባት ልጆች አሏቸው። አራቱ ሴቶች ሲሆኑ ሶስቱ ወንዶች ናቸው። እኔ ለወላጆቼ አራተኛ ልጅ ነኝ። የወላጆቼ መተዳደሪያ ግብርና ነው። ነገር ግን ልጆች ለማሳደግና ለማስተማር የሚበቃ አልነበረም። በዚህ ምክንያት ትምህርቴን ከስምንተኛ ክፍል በላይ ከፍ ማድረግ አልቻልኩም። ብቻም አይደለም። የተወለድኩበት አካባቢ መቆየት አልቻልኩም ።ወደ ሀዋሳ መጣሁ። ወደ ሀዋሳ ስመጣ የማውቀው አንድም ሰው አልነበረም።

“የነበረኝ አማራጭ የጎዳና ልጅ መሆን ነበር። ሀሮኒ አካባቢ። ባህል አዳራሽ፣ እዛ ሠፈር ነበርኩ። ከሆቴል የሚወጣ ትራፊ ነበር የምንመገበው። በዚህ መልኩ ነበር ኑሮዬን የምገፋው። ይሁንና የመሻሻል፣ የመለወጥ ፍላጎቶች ውስጤ ይመላለሱ ነበር። በዚህ ምክንያት ስራ መጀመር እንዳለብኝ ራሴን አሳመንኩ።

“ስራ የጀመርኩት ሞተር ሳይክሎች በሚጠገኑበት ቦታ ነው። ባለቤቱ ወንድዬ ይባላል። መፍቻ በማቀበል፣ በመላላክ፣ ሞተር በማጠብ ነው ወደ ስራ የገባሁት። 50 ብር ነበር በሳምንት የሚከፈለኝ። የሚከፈለኝ ገንዘብ ለምንም የሚበቃ አልነበረም። ሌላው ቀርቶ ከጎዳና ተነስቼ ቤት የመከራየት እድል አልፈጠረልኝም። አሁንም አዳሬ ጎዳና ነበር። ያማረ ሆቴል ግቢ ውስጥ።

“ቅዳሜ ሲመጣ ደሞዛችን ሀምሳ ብር ትሰጠናለች። እንበላባትና ታልቃለች። እሁድ ዕለት በጣም ፈታኝ ነው። ምግብ ይጠፋል። በማግስቱ ጭምር በባዶ ሆድ ስራ መግባት ግድ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ። ብቻም አይደለም። ጎዳና ስታድር የሌሊቱ ብርድ እንቅልፍ አያስተኛህም። ከነጋ በኋላ ፀሀይ ደብድቦህ፣ ሞቆህ ነው የምትነሳው። በዚህ ምክንያት ስራ አርፍዶ መግባትም ነበር። ፈተናው ከባድ ነበር።

“ከቀኖች ሁሉ የተሻሉት ቀኖች የበዓላት ናቸው። የዛን ዕለት ምግብ አይጠፋም። ከየቤቱ እያመጣ ሠው ይሰጥሃል። እኛም ሠብሰብ ብለንና ሆ! እያልን ከአላፊ አግዳሚ ገንዘብ እንቀበላለን። የተሻሉ ቀኖች ናቸው -በዓላት። ጠግበን እንበላ ነበር።

“ስራ ከጀመርኩ ወዲህ አንዳንድ ነገሮችን ለምጃለሁ። ዕግር መፍታትና ማሰር። ግሪስ ማድረግ። ግን ስራዎችን እንድታውቅ አይፈለግም። መጀመሪያ የተቀጠርኩበት ቦታ እንደዛ ነበር። ወንድዬ ጋ ከመጣሁ በኋላ ነው እነዚህን አንዳንድ ነገሮች የለመድኩት። እንጂማ እንድትለምድ ስለማይፈለግ ወይ አንተ ለምሳ ስትወጣ የሚጠገነው ሞተር ተገጣጥሞ ትደርሳለህ። ወንድዬን ግን አመሠግናለሁ። ሙያ እንድንለምድ አድርጎናል። የሞተር፣ የኤሌክትሪክ ክፍሎችን አሠራር አውቄያለሁ።

“ወንድዬም ጋ እያለሁ ደሞዜ ራስ የሚያስችል አልነበረም። በ6 ወር ነበር የሀያ አምስት ብር ጭማሪ የሚደረግልን። በርግጥ ሠዎች የሚሰጡን “ቲፕ” ታክሎበት ለአራትና ለሶስት ቤት ተከራይተን መኖር ጀምረናል። ቤትም እንደዛሬው ውድ አልነበረም። ርካሽ ነበር።

“በርግጥ ሙያ የቀሰምን ቢሆንም ክፍያው አሁንም ትንሽ ነበር። በዚህ ምክንያት ትተን ወጣን። ትተን ስንወጣ መፍቻዎች መግዣ አልነበረንም። በዚህ ምክንያት ራሴን የምችልበት ዕድል አልነበረኝም። መልሼ ተቀጣሪ ነው የሆንኩት። መሣይ የሚባል ሰው። ብየዳ ቤት ነው የገባሁት። እዛ ደግሞ ቁጥጥሩ አይጣል ነው። ስንት ነው ያገኘኸው? የሚል ጥያቄ ይበዛል። ይህ ሁሉ ራስህን ችለህ እንዳትወጣ ነው። ካልወጣህ ጉልበትህ ይጠቅማል።

“ራሴን የምችልበት እድል የተፈጠረው አንድ ዕለት ነው። የሺ ሆቴል አጠገብ። አቶ ዘውዴ የተባሉ ሠው ናቸው። ሠውየው ሞያ እንዳለኝ ቀድሞ ያውቁ ነበር። ብቻም አይደለም። ያዝኑልኝ ነበር። ሞተራቸውን ፈትቼ እንድገጥም ሰጡኝ። መፍቻዎች ለምኜ ፈትቼ ገጠምኩ። መፍቻ ያዋሰኝ አሸናፊ የሚባል የ05 ልጅ ነበር። አንዳንዴ ሰው ይጥልልሀል። አቶ ዘውዴ ሞተራቸውን ፈትቼ ከገጠምኩ በኋላ በሰጡኝ ብር የተወሰኑ መፍቻዎችን ገዛሁ። ከአሮጌ ተራ።

“ከዚያም ከአለታ ምንጭ ሆቴል ጀርባ አንድ አጥር ጥግ ስራ ጀመርኩ። ለአጥር ጥጉ ሶስት መቶ ብር ኪራይ ይከፈልበት ነበር። ነገር ግን ሰዎች የሚያውቁት እነ በለጠንና እነ ወንድዬን ስለነበር ወደ እኔ የሚመጣ አልነበረም። እንዲያም ሆኖ ግን የዕለት አይጠፋም ነበር።

“አለታ ምንጭ አካባቢን ትቼ ወደ አቶቴ መጣሁ። ስራው እየለመደልኝ መጣ። አንድ ሰው ከመቅጠር ሁለት ሰው። ሶስት ሰው። እያለ እያለ አደገ።

“እኔጋ ተቀጥረው ከሚሰሩት ልጆች ከሀያ በላይ የሚሆኑት ሞያ ተምረው ራሳቸውን ችለው ወጥተዋል።

“ቤተሠብ መስርቻለሁ ። አንድ ልጅ አለኝ። ቤተሠቤን በተገቢው መንገድ እያስተዳደርኩ ነው። እንደባለፉት ጊዜያት ፈተናዎች ባይኖሩም አንዳንድ ችግሮች አሉ። የራሳችን “ሼድ” ነበረን። ቦታው ለልማት ይፈለጋል ተብሎ ስንነሳ አውሮፕላን የቆመበት ግቢ በጊዚያዊነት ተሠጠን። አሁን ግን ግቢው ላይ ግንባታ እየተከናወነ ነው። መልቀቄ አይቀርም። ስለቅ ግን መስሪያ ቦታ የለኝም”

ታሪኩ በየነ የሲሳይ ሠለሞን የቆየ ጓደኛ ነው። ክፉንም ደጉንም አብረው አሳልፈዋል። ታሪኩ አባቱን ያጣው በልጅነቱ ነው። እናቱ ጉልት ቸርችረው የሚያገኙት ገቢ ልጆቻቸውን ለማሳደግ የሚበቃ አልነበረም። በዚህ ምክንያት እሱም ወደ ጎዳና ወጥቶ ነበር። የህይወት ዕጣ ነበረች ያገናኘቻቸው። ሁለቱም የሞተር ጥገናን የተማሩት አንድ ላይ ነው። አሁን ታሪኩ የባጃጅ ጥገናዎችን ያከናውናል።

ታሪኩ:-

“ሲሳይ በጣም ደግ ልጅ ነው። ሳይኖረው ስለሠው ያስባል። ያኔም ቢሆን በመተዛዘን ነው ጊዜውን ያሳለፍነው። ያኔም ቆቀር ይገዛልኝ ነበር። ሌተስት የሚባል ቁርስ ቤት ነበር። እዛ ነበር የምንገባበዘው። እኛ ቤት ይዤው እሄድ ነበር። ቂጣ በጎመንም ይገኝ ሌላ አብረን እንበላ ነበር። አሁንም አንድ ላይ ነን ። አልተለያየንም ። የምንሰራው ጎን ለጎን ነው።”