ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 05/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በብቃት እያለፈች ወደ ብልጽግና ማማ መገስገሷን ቀጥላለች!

የአንድነታችን ውጤት ፋና ወጊ የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር ሙሌት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከሥራ አጋሮቹ ጋር በመሆን ከስፍራው ተገኝተው አብስሮልናል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተባበርን እና በአንድነት ከቆምን ታሪክ ከመስራት አልፈን በአለም ፖለቲካም ሆነ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ተጽኖ ማሳደር እንደሚንችል ፍንትው አድርጎ ያመላከተን የብልጽግና ጎዳና ጠቋሚ ኮከባችን ነው!

የለውጥ ጉዞ ከጀመርን ከባለፉት 5 አመታት ወዲህ ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎች ተደቅነውባታል፡፡ ብዙዎችም ትበተናለች ሲሉ በድፍረት ተናግረዋል። በርካታ የተቀናጁ ሴራዎች ተጎንጉነውባታል። የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶች ለመፍረሷ መንገዱን ጠርገውላታል።

ሆኖም ግን በህዝቧና በለውጡ መንግስት ጽናትና አንድነት ማንም ወደሗላ እንደማይጎትታት በተግባር ማሳየቷን ቀጥላለች።

ህዝቦቿ በራሳቸው ጥረት ብቻ ከድህነትና ሗላ ቀርነት ተመንጥቀው በመውጣት ለቀጣይ ትውልድና ሀገር አኩሪ ቅርስ ማውረስ እንደሚችሉ እያረጋገጡ ይገኛሉ።

ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን የዜጎቻችንን ብሩህ ተስፋ በማለምለም ላይ ናቸው። ታላቁ የህዳሴ ግድብ የጽናት መገለጫ፤ የመተባበር ቱሩፋት ማሳያ፤ የአንድነት መደምደሚያ ነው፡፡

ከእነዚህ ብርቅዬ ተስፋዎቻችን ትልቁ የሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድባችን አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት በተሳካ ሁነታ መጠናቀቅ እኛን ብቻ ሳይሆን ጠላቶቻችንም ጭምር የሚያስደንቅ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።

በሁሉም ዘርፍ ጉዟችን ተጠናክሮ ይቀጥላል። ሀገራችን ኢትዮጵያም ፈተናዎችን በብቃት እያለፈች ወደ ብልጽግናዋ መገስገሷን ትቀጥላለች!

ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የምናደርገውን ማናቸውንም አይነት ድጋፍ እስከ ፍጻሜው ድረስ አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የህዳሴ ግድባችን ቀጣይ ቀሪ ስራዎች ተጠናቀው በሙሉ አቅሙ ወደ አገልግሎት መግባት እንዲችል የክልሉ ህዝብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

መጪው ጊዜ ብሩህ ነው፡፡ በተከናወነው አኩሪ ተግባርም ለክልሉ ህዝብ ለመላው ኢትዮጵያውያን እና ለወዳጆቻችን እንኳን ደስ አለን ለማለት እወዳለሁ!!