የድርቅ ወቅትን ተከትሎ በአርብቶ አደሩ ላይ የሚደርሰዉን ተጽዕኖ ለመታደግ የቁም እንስሳት መድን ዋስትናን በአርብቶ አደር ደረጃ ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለፀ

የድርቅ ወቅትን ተከትሎ በአርብቶ አደሩ ላይ የሚደርሰዉን ተጽዕኖ ለመታደግ የቁም እንስሳት መድን ዋስትናን በአርብቶ አደር ደረጃ ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለፀ

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ኢትየጵያ ሕዝቦች ክልል መንግስት አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ታምሩ ቦኒ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ በእንስሳት ሀብት ቀዳሚ ብትሆንም በአየር ንብረት ለውጦች በሚከሰቱ ድርቅና መሰል ጉዳቶች ምክንያት በእንስሳት ሀብቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም አርብቶአደሮች ከእንስሳት ቁጥራቸዉ የሚመጣጠን ሃብት ሳያገኙ መቆየታቸውን የጠቆሙት የቢሮ ሃላፊው አርብቶ አደሩን ከእነዚህና መሰል ችግሮች ለመታደግ የቁም እንስሳት መድን ዋስትናን በአርብቶ አደር አካባቢ ማረጋገጥ እንደሚገባም ነዉ የገለፁት።

የመድን አገልግሎት የአርብቶ አደሩን የአደጋ ጊዜ ስጋትን ከመቀነስ አንፃር ጠቀሜታው ከፍተኛ በመሆኑ የህብረት ስራ ማህበራትና በየደረጃዉ የሚገኙት ባለድርሻ አካላትም ለተግባራዊነቱ የድርሻውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትየጵያ ሕዝቦች ክልል መንግስት አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ የአደጋ ስጋት ቅነሳ አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት (DRIVE) አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ኦይጌሌች በበኩላቸዉ በአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች ኢኮኖሚ ዘርፍ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩን ስጋት በመቀነስ የአየር ንብረት ለወጥን የሚቋቋም የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይም አርብቶ አደሩን ከእንስሳት እርባታ ባሻገር በአካታች የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ዘርፍ በማሳተፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በክልሉ የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ነዉ የገለፁት።

በተለይም የአርብቶ አደሩን የቁም እንስሳት መድን ዋስትናን የማረጋገጥ ተግባር በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ተስፋዬ ለዚህም በየደረጃዉ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ዉይይት መደረጉን አስረድተዋል።

በሚዛን አማን በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ከካፍና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች የተውጣጡ አርብቶ አደሮች እንዲሁም በአርብቶ አደር አካባቢ የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ አሰፋ – ከሚዛን ጣቢያችን