ከህብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 11ኛ የሥራ ዘመን 23ኛ መደበኛ ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል።

ምክር ቤቱ 4ኛ ዙር 11ኛ የሥራ ዘመን 23ኛ መደበኛ ጉባኤ የምክር ቤት የአስተዳደርና የከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም መገምገምና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡

የምክር ቤት አፈጻጸም ግምገማም የህብረተሰብ ተወካይ ከሆኑ የምክር ቤት አባላት ጉባኤያት በወቅቱ አለመከናወናቸው፣ ከኦዲት ግኝት፣ ከበጀት እጥረት እና የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት እንደተደረገባቸው የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ምስጋና ዋቃዮ ገልጸዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች በተለይም የቀበሌ ምክር ቤቶች አለመጠናከር ለመሬት ወረራና ለመሳሰሉት ችግሮች መዳረጉ በጉባኤው ተመላክቷል።

የስልጣን ባለቤት የሆነው ምክር ቤት ከህብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን አሰፈጻሚ አካላት ትኩረት ሰጥተው ቀጣይ የበጀት አካል አድረገው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ አፈ ጉባኤዋ አሳስበዋል።

በዛሬው ውሎም አዳዲስ ሹመቶችንና የመስጠትና የ2016 በጀት ያጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ፡ ውብሸት ካሣሁን – ከፍስሐገነት ጣቢያችን