አቅመ ደካማ ወገኖችን በመርዳት የምናሳየው በጎነት የዜግነት ግዴታችን ከመሆን ባለፈ የሀገራችንን የድህነት ታሪክ በመረዳዳት የምንቀይርበት አንዱ መንገድ መሆኑ ተገለፀ

አቅመ ደካማ ወገኖችን በመርዳት የምናሳየው በጎነት የዜግነት ግዴታችን ከመሆን ባለፈ የሀገራችንን የድህነት ታሪክ በመረዳዳት የምንቀይርበት አንዱ መንገድ መሆኑ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 03/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) አቅመ ደካማ ወገኖችን በመርዳት የምናሳየው በጎነት የዜግነት ግዴታችን ከመሆን ባለፈ የሀገራችንን የድህነት ታሪክ በመረዳዳት የምንቀይርበት አንዱ መንገድ መሆኑ ነው – የካፋ ዞን ሴቶች ህፃናት ወጣቶችና ማህበራዉ ጉዳይ መምሪያ፡፡

በየአካባቢው የሚገኙ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት የማይችሉ ወገኖቻችንን በመርዳት የትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲቆዩ ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን የካፋ ዞን ሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶችና ማህበራዉ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ፡፡

የዞኑ ሴቶች ህፃናት ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የበጎ ፍቃድ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በጎነት በማንኛውም መንገድ ልናገኝ የማንችለውን የህሊና እርካታ የሚሰጠን በመሆኑ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሰማያዊና ምድራዊ ትርፍ ማግኘት እንደሚቻል የመምሪያው ሃላፊ ወ/ሮ መዓዛ ሀይለማሪያም ገልፀዋል፡፡

አሁንም የተለያዩ በጎ ፍቃደኞችንና ተቋማትን በማቀናጀት የመማሪያ ቁሳቁስና ልዩ ልዩ የበዓል መዋያ ግብዓቶች እየሰበሰበ ሲሆን ዜጎችም በቀረው ጊዜ ውስጥ በነቂስ የበጎ ፍቃድ ስራ ላይ እንዲሳተፉ መምሪያው ሀላፊዋ ጠይቀዋል፡፡

በዕለቱ በካፋ ዞን መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ አስተባባሪነት የመማሪያ ቁሳቁስ ልገሳ ሲያደርጉ ያገኘናቸው የፀጋአብ አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም ባለቤት አቶ ፋሲካ ክፍሌ እንደገለፁት ማንኛውም ተቋም ከሚያገኘው ነገር ላይ መለገስን መልመድ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በማንኛውም ድርጅት በየተሰማራበት የሙያ መስክ ፍላጎት ኖሯቸው አቅም የጎደላቸው ወገኖችን በመርዳት ከህልማቸው በማገናኘት የድህነት ቅነሳው ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለበትም አቶ ፋሲካ ጠቁመዋል፡፡

በጎነትንና በመረዳዳት አብሮ መኖር የቆየ ባህላችን መሆኑን በመገንዘብ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ ግዴታችን በመሆኑ ይበልጥ በበዓላት ወቅት ማጠናከር እንዳለብን የገለፁት ደግሞ የካፋ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ሃላፊው አቶ ዘመዴ አንዳርጌ ናቸው፡፡

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ጣቢያ