በበዓል ገበያ ወቅት የሚከሰተውን የምርት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 03/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በበዓል ገበያ ወቅት የሚከሰተውን የምርት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የወላይታ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መመሪያ አስታወቀ፡፡

የምርት አቅርቦት ቢኖርም የዋጋ ጭማሪ ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በወላይታ ሶዶ ያነጋገርናቸው ሸማቾች ጠይቀዋል።

የበዓል መዳረሻ ቀናት የሸማቾች ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ የምርት እጥረትና አላስፈላጊ የሆነ የምርት ላይ ዋጋ መጨመር ይስተዋላል።

በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ካነጋገርናቸው ነዋሪዎች መካከል ወ/ሮ ንግስት አያሌውና ወ/ሮ አመለወርቅ አብረሃም በበአል ገበያ የምርት አቅርቦት ቢኖርም የገበያ ሁኔታ ከአምናው ጋር ስነጻጸር የዶሮ፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ዘይትና ቅቤ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋቸው መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

ሸማቾች እንደገለጹት አንድ መለስተኛ ዶሮ እስከ 7 መቶ ብር እየተሸጠ ሲሆን ከፍተኛው 1ሺ 2 መቶ ብር መሆኑን ጠቁመዋል።

ከፋብሪካ ምርቶች የስኳርና ዘይት ዋጋ መጨመሩን አንስተው የዋጋ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረገ ጠይቀዋል፡፡

አቶ ፈለቀ ወንባ በመርካቶ ገበያ የዶሮ ነጋዴ ሲሆን በበዓል ገበያ የዶሮ ዋጋ ከ8 መቶ እስከ አንድ ሺ ሁለት መቶ ከባለፈው ጋር ሲነጻጸር ዋጋ መጨመሩን ተናግሯል።

የበሬ ስጋ ከሸማቾች እስከ ሆቴል 1 ኪሎ ከ8 መቶ እስከ 1 ሺ 2 መቶ እንደሚሸጥ ያነሳው አቶ ፈለቀ ከባለፈው ጋር ሲነፃፀር ብዙም የዋጋ ጭማሬ ያለታየበት መሆኑን ተናግሯል፡፡

የወላይታ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ወረስሶ ገበያውን ለማረጋጋትና የምርት አቅርቦት እጥረት ለመቀነስ ከአምስት ማህበራት ጋር በጋራ በመሆን የጤፍ አቅርቦት ላይ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በገበያ ውስጥ ያለውን የዋጋ ቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶችን ከማስወገድ አኳያ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ጉዳዩን ተከታትለው እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከሃምሳ በላይ የእህል በረንዳዎችና የእህል መጋዘኖች ላይ የማስጠንቀቂያና የማሸግ እርምጃ እንደተወሰደ ኃላፊው ገልጸዋል።

የበዓል ገበያ ሰሞን ምርቶችን ከበዓድ ነገሮች ጋር የሚቀላቅሉና አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደረጉ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የተቀናጀ የህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ለሚመለከተው አካላት ጥቆማ በማድረግ እንዲተባበሩ አቶ ወንድሙ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ድርሻዬ ጋሻው – ከዋካ ጣቢያችን