የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት በትኩረት እየተሠራ ነው – የኮንታ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ

የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት በትኩረት እየተሠራ ነው – የኮንታ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 02/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የኮንታ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ገልጿል፡፡

ካነጋገርናቸው የትራፊክ ፖሊስ አባላት መካከል ዋና ሳጅን ውድነሽ ገብሬ እና አዝማች አበራ እንደገለፁት በዓልን ምክንያት በማድረግ የትራፊክ ፍሰትና ከዞኑ የሚወጣና የሚገባ ሕዝብ ቁጥር መብዛትን ተከትሎ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ይህንን ለመቆጣጠር ስምሪት ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

የትራፊክ አደጋ በየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ላይ የሚከሰት በመሆኑ አደጋውን መቀነስ እንዲቻል እግረኞችና አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉና አሽከርካሪዎች የቴክኒክ ችግር ያለባቸውን ተሽከርካሪዎችን ፈትሸው እንዲያወጡ እንዲሁም እግረኞችም መንገድ ሳይመርጡ የራሳቸውን ግራ መስመር ብቻ ይዘው መጓዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተጨማሪም አሽከርካሪዎች በዓልን ምክንያት በማድረግ መጠጥ ጠጥተው ማሽከርከር እንደሌለባቸውም ዋና ሳጅን አዝማች አበራ አስገንዝበዋል።

በኮንታ ዞን ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥርና አደጋ መከላከል ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ባሻው በካሎ በበኩላቸው የትራፊክ አደጋ በዚህ ወቅት አሳሳቢ በመሆኑ በዞኑ በዓልን ምክንያት በማድረግ  አደጋ እንዳይከሰት በሁሉም መዋቅሮች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የትራፊክ ፖሊስ አባላት ፍሰቱን ለመቆጣጠር ስምሪት ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውን የገለፁት ኃላፊው አሽከርካሪዎችም የራሳቸውን ቀኝ መስመር ብቻ ይዘው በማሽከርከር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የዞኑ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ም/ኃላፊና የዩራኘ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አይናለም ኡሸቾ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ደረጀ ተፈራ – ከዋካ ጣቢያችን