የተፈጥሮ ፀጋን ወደ ሀብት ቀይሮ መጠቀም እንደሚገባ ተገለፀ

የተፈጥሮ ፀጋን ወደ ሀብት ቀይሮ መጠቀም እንደሚገባ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የክልሉን ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፉን በማጠናከር የአካባቢውን የተፈጥሮ ፀጋ ወደ ሀብት ቀይሮ መጠቀም እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

የሚዛን ግብርና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ከዴች ሲኖ ምስራቅ አፍሪካ የቀርቀሃ ልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ክልል ከሁለት ዞኖች ለተውጣጡ ወጣቶች በቀርከሃ ምርት አጠቃቀም ላይ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል፡፡

በስልጠና ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ ክልሉ የሚገኘው ሀብት ቢለማ ከራሱ አልፎ በሀገሪቱ የሚገኙትን ክልሎችን መመገብ የሚችል አቅም እንዳለው ጠቁመው፥ ደቡብ ምዕራብ ክልል ካለው ሰፊ ሀብት አንዱ ቀርቀሃ ተክል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢንተርፕራይዝ ቢሮ ከአምና ጀምሮ ስራ አጦችን ለይቶ በተርጫና ከፋ ዞን ስልጠና ሲሰጥ እንደነበር አውስተው አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ሠልጣኞች ባገኙትን ክህሎት በአካባቢያቸው የሚገኘውን ቀርቀሃ ወደ ገንዘብ ከመቀየር ባለፈ ራሳቸውን እንዲለወጡበትና ተክሉን ከብክነት እንዲከላከሉ አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛው ጋጊያብ በበኩላቸው፥ መሰል ስልጠናዎች ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለስራ አጥ ወጣቶች እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልፀው በቀርቀሃ ተክል የጥበብ ስራ ላይ ከዴች ሲኖ ምስራቅ አፍሪካ የቀርቀሃ ልማት ኘሮግራም እና ከሚዛን ግብርና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ጋር በመተባበር በተግባር ላይ የተደገፈ ስልጠና መስጠቱን አስረድተዋል፡፡

የዴች ሲኖ ምስራቅ አፍሪካ የቀርቀሃ ልማት ኘሮግራም አስተባባሪ አቶ ፍቅር አሰፋ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ከቻይና ሀገር ባገኘው 56 ሚሊዬን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ቀርቀሃን ወደ ሀብት ለመቀየር የሚያስችል ኘሮጀክት ተቀርጾ ሰፊ ስራ መጀመሩን አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ፍቅር ማብራሪያ በሀገራችን ኢትዮጵያ 1 ነጥብ 47 ሚሊዬን ሄክታር የቀርቀሃ ሽፋን እንዳለ የተረጋገጠ ሲሆን ኘሮጀክቱ ኢትዮጵያን ማዕከል በማድረስ በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ 5 ሀገሮችን ኬኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያና ማዳካስካርን ያገለግላል ተብሎ ተስፋ መጣሉን አመልክተዋል፡፡

የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ዲን አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በበኩላቸው በቻይና ሀገር ለትምህርት በሄዱበት አጋጣሚ ቀርቀሃ ለምገብነት፣ ለቤት ቁሳቁስና ለሌሎች አገልግሎቶች መዋል እንደሚችል ማየታቸውን ተሞክሮአቸውን አካፍለው ኮሌጁ በአካባቢው የሚገኘውን የቀርቀሃ ሀብት ለቤት ቁሳቁስ ማዋል የሚያስችል ስልጠና ለተመረጡት ወጣቶች መስጠቱን ገልፀዋል፡፡

ሰልጣኞች ባገኙት ክህሎት ወደ ትግበራ መግባታቸውን በቀጣይ ኮሌጁ እየተከታተለ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ያስገነዘቡ ሲሆን የክልሉ ኢንተርኘራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ከኮሌጁ ጋር በቀጣይ ለመስራት የሚያስችል መግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

ከክልሉ ሸካና ቤንች ሸኮ ዞን 30 ወጣቶችን ክልሉ መልምሎ እንደሰጣቸውና ዴች ሲኖ ምስራቅ አፍሪካ የቀርቀሃ ልማት ኘሮግራም የስልጠናውን ወጪ በመሸፈን ኮሌጁ ስልጠና መስጠቱን አስረድተዋል፡፡

ሠልጣኝ ወጣቶችም በበኩላቸው ባገኙት ስልጠና ከቀርቀሃ ተክል ቁሳቁስ በማዘጋጀት ወደ ሀብት በመቀየር ራሳቸውን ለመቀየር ዝግጁ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ ከሚዛን ቅርንጫፍ