የዳውሮ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ቶክበኣ”

የዳውሮ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ቶክበኣ”

በዓሉ ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ ዓለምአቀፍ እውቅና እንዲያገኝ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የዳውሮ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታውቋል።

የጨረቃ መውጣትና መግባትን መነሻ ባደረገው የዳውሮ ብሔረሰብ የዘመን አቆጣጠር እውቀት የአሮጌው ዓመት ማለፊያ እና የአዲሱ አመት መቀበያ “ቶክበኣ” በዓል ከጥንትም ጀምሮ  እየተከበረ የመጣ መሆኑን የብሔረሰቡ ሊቃውንት ይናገራሉ።

ካነጋገርናቸው መካከል አቶ ታዬ ግንባቶ፣ ወ/ሪት ስንቅነሽ ደነቀ እና ድምፃዊት ጥሩብር ግዛው፥ ለቶክበኣ በዓል ዘመድ ከዘመድ ተራርቆና አንዱ ከአንዱ ተጣልቶ ማክበር ስለማይቻል የተጣሉትን ማስታረቅ በብሔሩ አባቶች ከበዓሉ አስቀድሞ የሚፈፀም ተግባር መሆኑንና በተለያየ ምክንያት የተራራቁም ወደ ዘመድ ቤተሰብ እንደሚሄዱ ገልጸዋል።

በዓሉ ሁሉም እንደ የአቅሙ ካመረተውና ካፈራው ምርት የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችን በማዘጋጀት የሚከበር ሲሆን፥ ይህም አመቱን ሙሉ በስራና በድካም ያለፈውን ጊዜ በበዓሉ ጠግበው መብላት እንደሚያስፈልግ የሚያስረዳ ነው ብለዋል።

ለቶክበኣ በዓል  ወንዶች እህል ከጎተራው ለማጀት ማቅረብ፣ ወጣቶች እንጨትና የከብቶች መኖ ማዘጋጀት፣ ለቅርጫ ስጋ እቁብ በመግባት በዓሉ ሲደርስ ማረድ፣ በአሮጌው አመት የነበረው መጥፎ ክስተት እንዲወጣና አዲስ ዓመት የመልካም እንዲሆን የሚያበስር ችቦ(ፂፋ) መወርወር፣ የሐገር ሽማግሌዎች አድሱ ዓመት የሠላም የጤናና የመልካም ነገሮች እንዲሆን የመፀለይ ተግባር እንዳላቸው ያስረዳሉ።

ሴቶችም ቀድመው ቆጮ፣ እህልና ለምግብ የሚሆኑትን ነገሮች ማዘጋጀት፣ ወጣት ሴቶች ውሃ መቅዳት፣ እንሶስላ ሰብስበው መቀባትና በበዓሉ እለት መዝፈን እንደሚጠበቅባቸው በመግለፅ በበዓሉ ከሚታወቁ በርካታ የምግብ ዓይነቶች “ባጭራ” ቅድሚያ የሚጠቀስ ነው።

በዓሉ በሀገርና ዓለም አቀፍ ደረጀ እንዲታወቅ ከ2003 ዓ/ም ጀምሮ በአደባባይ እየተከበረ ቆይቶ በኮሮና ቫይረስና በተለያዩ ሀገራዊ ችግሮ ምክንያት በአደባባይ ማክበር እንዳልተቻለ ጠቁመው፥ ዘንድሮ ይህን ለማሻሻል ከወረዳም ጀምሮ በተለያዩ ባህላዊ ዝግጅቶች እየተበከረ እንደሚገኝ የዳውሮ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታሁን ግርማ ተናግረዋል ።

የበዓሉ  መከበር ደግሞ የዞኑን ባህላዊ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ሀብቶችን ከማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው በማስረዳት በሁነቱ ያለው ተጠራርቶ መብላት፣ እርቅና የጊዜ አቆጣጠር እውቀትና መሰል ተግባራት ሀገራዊ ፋይዳቸውም የጎላ መሆኑን የመምሪያው ኃላፊ ገልጸዋል።

“በዓሉን ይበልጥ ለማሳደግም መምሪያው በትኩረት እንደሚሠራ በመጠቆም በዘርፉ የሐይማኖት አባቶች፣ የዞኑ ተወላጆችና የመንግስት አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ አጠናክረው እንድቀጥሉም አቶ ጌታሁን ጠይቀዋል።

በዳውሮ ብሔረሰብ የሚከበረው የቶክበኣ በኣል በብሔረሰቡ የቀን አቆጣጣጠር እውቀት በነሐሴ መጨረሻ አካባቢ የሚውል ሲሆን ዘንድሮም በጳጉሜ 2 በዞኑ ዋና ከተማ ታርጫ ለማክበር ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል።

የዘገበው ዮሐንስ መካሻ ከዋካ ቅርንጫፍ