የዋቸሞ ዩንቨርሲቲ የእንሰት አጠውልግ በሽታን ለመከላከል በምርምር የተደገፈ ስራ እየሠራ እንደሚገኝ አስታወቀ

የዋቸሞ ዩንቨርሲቲ የእንሰት አጠውልግ በሽታን ለመከላከል በምርምር የተደገፈ ስራ እየሠራ እንደሚገኝ አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 30/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዋቸሞ ዩንቨርሲቲ የእንሰት አጠውልግ በሽታን ለመከላከል በምርምር የተደገፈ ስራ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በዩኒቨርስቲው የአዝርዕትና ስራ ስር ሰብሎች መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል መኖሬ ጉዳዩን አስመልክቶ ሙያዊ ማብራሪያ የሰጡት፤ በሀገራችን የእንሰት ምርት በብዛት ከሚገኝባቸው ክልሎች የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚጠቀስ ነው።

የእንሰት ምርት ከምግብነት በተጨማሪ ለዘርፈ-ብዙ ግልገሎት የሚውል ሲሆን “የእንሰት አጠውልግ” በሽታ በምርቱ ላይ በሚያደርሰው ጉዳት የምርቱ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ስለ መምጣቱ ተመላክቷል።

የዋቸሞ ዩንቨርስቲ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በበሽታው ዙሪያ ጥናትና ምርምር እያካሄደ እንደሚገኝ ነው ረ/ፕሮፌሰር ዳንኤል መኖሬ የተናገሩት።

ዩንቨርስቲው በበሽታው ዙሪያ ከሀዋሳና አረካ የምርምር ማዕከላት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝና በዚህም የአርሶ አደሩን ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ከአጎራባች ዞኖች የተለያዩ የእንሰት ዝርያ አይነቶችን በማሰባሰብ በምርምር ማዕከሉ ማስፋፋት ተችሏል የሚሉት ተመራማሪው ይህም የምርት ሁኔታንና ፋይዳውን መሠረት ባደረገ መልኩ እንደሆነም ገልጸዋል።

ለምግብነት፣ ለመድኃኒትነትና ለቁስነት የሚያገለግሉ የእንሰት አይነቶችን በየፈርጁ በማዘጋጀት የምርምር ሥራ እየተሠራ ነው።

የእንሰት አጠውልግ በሽታን በመቋቋምም ሆነ በምርታማነት የተሻለ የእንሰት ዝሪያን በምርምር በመለየት ለአርሶ አደሩ የማዳረስ ሥራ እየተሠራ እንደሆነና በተላይም በሽታው በቆላማ አከባቢ ላይ በብዛት የሚከሰት በመሆኑ የግንዛቤ ሥራም ጎን ለጎን እየተሰራ ነው ብለዋል።

እንሰት በተላይም በችግኝ ደረጃ ላይ ሲሆን ርቀትን ጠብቆ መትከል አስፈላጊ እንደሆነ የሚመክሩት ረ/ፕሮፌሰር ዳንኤል ይህም በስር አማካይነት ከመሬት የሚያገኘውን ንጠረ ነገርንና አየርን በአግባቡ አግኝቶ እንዲያድግ ያስችላል ብለዋል።

በደጋማ አከባቢ የለው የአየር ሁኔታ ቀዝቃዛ መሆን ለበሽታው በቀላሉ እንዳይስፋፋ ያደርጋል የሚሉት ተመራማሪው አርሶ አደሩ በበሽታው የተጎዳ እንሰት ካገኘ  ለሌሎች መጠቃት ምክንያት እንዳይሆን ተገቢውን ክትትል ማድረግ እንደለበት አሳስበዋል።

እንሰት በሚፋቅበት ወቅት አርሶ አደሩ ለመፋቂያ የሚጠቅማቸውን ቁሳቁስ ከጎረቤት ጋር መዋዋስ ለበሽታው መዛመት ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በእንሰት ምርት ላይ ትኩረት መደረግ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፡ አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን