የመኖሪያ ቤት ፍላጎትን ለማሟላት በትኩረት እንደሚሰራ ተጠቆመ

የመኖሪያ ቤት ፍላጎትን ለማሟላት በትኩረት እንደሚሰራ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 30/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

ከዚህ ቀደም በማህበር ለተደራጁ የከተማው ነዋሪዎች የቀረበላቸው መሬት የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን እንደቀረፈላቸው አንዳንድ ተጠቃሚዎች ተናግረዋል።

በከተማው ልዩ ስሙ ቤቴል መምህራን ሳይት አካባቢ በማህበር ተደራጅተው ባገኙት መሬት ላይ ቤት የገነቡት መምህራን በተፈጠረላቸው ዕድል የነበረባቸውን የመኖሪያ ቤት ችግር እንደቀረፈላቸው ተናግረዋል።

የከተማውን ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በተሰራው ስራ ከዘጠኝ የቤት አማራጮች አንዱ በሆነው በጋራ መኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማህበር ለተደራጁ መምህራን፣ ለክብር ተመላሽ ሠራዊትና ለመደበኛ ለ185 ማህበራት ቤት መስሪያ ቦታ በማቅረብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በከተማ አስተዳዳሩ የቤቶች ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ወንድሙና የቤቶች ህንፃ ልማትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ መለሰ ወርቁ ገልጸዋል።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ  አቶ ሊሬ ጀማል በበኩላቸው በዘርፉ በተለያዩ የቤት አማራጮች  በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንና በተያዘው በጀት ዓመትም በተለይ በማህበር ለተደራጁ ነዋሪዎች መሬት ለማስተላለፍ እየተሰራ ነው።

በሪል ስቴትና በማህበራት የመኖሪያ ቤት አማራጮች መሳተፍ ለማይችሉ ለአቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች ነባር የመንግስት ቤቶች ጥገና እየተካሄደ ስለመሆኑም ካንቲባው ጠቁመዋል።

ለመኖሪያ ቤት መስሪያ መሬት ወስደው ያላለሙ ነዋሪዎች በፍጥነት ማልማት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በዞኑ ሆሳዕና ከተማና በስድስት ፈርጅ ሶስት ከተሞች የቤት ልማት ፕሮግራም ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንና ከነዚህም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥርና የቤት ፍላጎት ያለው የሆሳዕና ከተማ በዘርፉ ብዙ መስራትን ይጠይቃል ያሉት ደግሞ በሀዲያ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ምክትል ኃላፊና የከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ናቸው።

በቀጣይም በዘርፉ ከሀዋሳ ከተማ በተገኘው ልምድ መሠረት በሁሉም የዞን ከተሞች መሬትና ወጪን በቆጠበ መልኩ አዲስ ፕሮቶታይፕ ዲዛይን ተግባራዊ እንደሚደረግም አብራርተዋል።

ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ  ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን