የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ የ2015 በጀት ዓመት የአፈፃፀም ግምገማ እና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 16/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ የ2015 በጀት ዓመት የአፈፃፀም ግምገማ እና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የጎፋ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ጠንክር ጠንካ እንዳሉት፤ መምሪያው የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት በማሻሻል የእናቶችና ሕፃናትን ሞት በመቀነስ የማህበረሰቡን ጤና ለማሻሻልና ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረጉ ተግባራት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ማኖቴ በበኩላቸው በበጀት አመቱ በእናቶችና ህጻናት እንክብካቤ፣ በግልና አከባቢ ንጽህና፣ በጤና መድህን አፈጻጸም፣ በሽታ መከላከል ስራዎችና በመሳሰሉ ተግባራት ጊዜ ጎፋና መሎ ኮዛ ወረዳዎች እንዲሁም በቶ ከተማ አስተዳደር የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ይህንን ተሞክሮ ወደ ሌሎች መዋቅሮች በማስፋትና የተጀመሩ ጠንካራ አፈጻጸሞችን በማስቀጠል የጤና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችን ለማሳካት በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በርካታ ሞዴል ቀበሌያት ተመርቀዋል ያሉት አቶ ማርቆስ፣ በኮሌራ ወረርሽኝ የተጎዱ ሞዴል መዋቅሮች ከወረርሽኙ ራሳቸውን መከላከል መቻላቸውን አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ600 በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች በኮሌራ በሽታ መያዛቸውን ያስታወቁት ኃላፊው በበሽታው የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አመላክተዋል።
አክለውም የወባ በሽታ መከላከል ሥራዎችን ለማጠናከር 312ሺህ በላይ አጎበር የተሰራጨ ሲሆን ከአጠቃቀም አንጻር የሚታዩ ጉድለቶች መታረም እንዳለባቸው ገልፀዋል።
በዞኑ በሚገኙ አንዳንድ መዋቅሮች ከአምቡላንስ አያያዝና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ችግሩን ለመፍታት የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አንስተዋል።
ካነጋገርናቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አበበ ኤርሚያስ፣ አቶ መርደኪዮስ ማርቆስ እና አቶ ኤልያስ ለማ በሰጡት አስተያየት በመዋቅራቸው በ2015 በጀት ዓመት የታዩ ጠንካራ አፈጻጸሞች በማስቀጠል የጤና ትራንስፎርሜሽኑን ለማሳካት ከወትሮ በተሻለ ትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አለማየሁ ባውዲ በክልሉ የሚገኙ የየተለያዩ ብሔሮች ዘመን መለወጫ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ !!
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አት ደመቀ መኮንን በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ንግግር አደረጉ
300 ለሚሆኑ ወላጅ አጥ ተማሪዎች ኢትዮ- ቴሌኮም ሳውላ ድስትሪክት ከ270 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ