የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መዲና ሆሳዕና የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሊሬ ጀማል ገለፁ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋና መቀመጫ ሆሳዕና የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሊሬ ጀማል ገለፁ

ከተማዋ የምትታወቅበትን የሰላም አምባሳደርነቷን ለማስቀጠል ህዝቡና አመራሩ በቅንጅት እየሰራ ስለመሆኑም ተጠቁሟል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋና መቀመጫ የሆነችው ሆሳዕና እንግዶቿን ለመቀበል በዝግጅት ላይ ትገኛለች።

ቀድሞም ቢሆን በሰላሟና የርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማረፊያና መኖሪያ ሆነ የቆየች የሆሳዕና ከተማ በአዲስ መልክ ከተደራጀው ክልል ጋር ተያይዞ የሚመጡ እንግዶቿን ለመቀበል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ስለመደረጉ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሊሬ ጀማል ገልፀዋል።

ከተማዋም ሆነች ዞኑ የሰላም አምባሳደርነታቸውን እያስመሰከረ የቆየ መሆኑን ያረጋገጡት ከንቲባው ይህን ለማስቀጠል ህዝቡና አመራሩ በቅንጅት እየሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የክልሉ በአዲስ መልክ መደራጀት የህዝቦች የዘመናት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ መንገድ ሆኗል ያሉት ካንቲባው ይህም በቀጣይ ሌሎች ጥያቄዎችም ምላሽ እንደሚያገኙ ማሳያ ነው ብለዋል።

ለሚመጡ እንግዶች የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ፍላጎቶችንና የመንግስት ተቋማትን በተገቢ መንገድ ማቅረብ እንዲቻልና ህገወጥ የዋጋ ጭማር እንዳይኖር ከአገልግሎት ዘርፍና ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር መግባባት ላይ ስለመደረሱም አሳውቀዋል።

የሆሳዕና ከተማ ነዋሪው የተለመደውን የእንግዳ አቀባበል ባህሉን በማጠናከር የሚጠበቅበትን እንዲወጣ በየማህበራዊ መሠረቱ ውይይት ስለመደረጉም አቶ ሊሬ አብራርተዋል።

ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን