ውበት በትዝታ

ውበት በትዝታ

በአለምሸት ግርማ

በራሳቸው ጥረት የብዙ ሙያዎች ባለቤት የሆኑ ሰዎች ቁጥር በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መጥቷል። እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፍ ይጠይቃል። በተለይም የውበት ስራ ፈጠራን የሚጠይቅ በመሆኑ ትኩረትን እና ጊዜን የሚፈልግ ሙያ ነው።

የስራ ፈጠራ ባለቤት መሆን አድካሚ ቢሆንም ከራስ አልፎ ለሌሎች የስራ ዕድልን ከመፍጠር ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። ከእነዚህ ጠንካራ ሰዎች መካከል የዛሬዋ እቱ መለኛችን አንዷ ናት። ዲዛይነር ትዝታ ፀጋዬ ትባላለች።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ ስትሆን በዲዛይኒንግ እና በዲኮር ስራ የተሰማራች ባለሙያ ናት። ባለትዳርና የሁለት ሴት ልጆች እናት ናት። መደበኛ ትምህርቷን የተማረችው ሉትራን ሚሽን ትምህርት ቤት ቀጥሎም ሊጋባ በየነ ትምህርት ቤት ተከታትላለች።

ከፍ ሲልም ከሰሊሆም ቢዝነስ ኮሌጅ በዲፕሎማ፣ ከኢንፎሊንክ በዲግሪ መርሃ-ግብር በሂውማን ሪሶርስ ማናጅመንት፣ ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም የፀጉር ስራ ሙያ የቀሰመቻቸው ሙያዎቿ ናቸው። ወደ ዲዛይን እና ዲኮር ሙያ ከመሰማራቷ በፊት የወላይታ ዞን ባህል ውዝዋዜ ቡድን አባል እና ለሶስት ዓመታት የወላይታ ሴቶች እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች ነበረች። በወቅቱ ለሴቶች እግር ኳስ ብዙም ትኩረት እንዳልነበራት የምትናገረው ትዝታ ለስፖርት ፍቅር ስለነበራት ብቻ ትጫወት እንደነበርም አስታውሳለች።

ከዚህ በኋላ ነበር ወደ ግል ስራ ለመግባት የወሰነችው። ለዚህ መነሻዋ ደግሞ ሰናይት ማሪዎ የምትባል በጣሊያን ሀገር የምትኖር ሴት መሆኗን ትናገራለች። በአንድ ወቅት ያች ሴት የአካባቢውን የባህል ልብስ በዘመናዊ መልክ በማዘጋጀት የፋሽን ሾው ፕሮግራም አዘጋጅታ ነበር። በዚያም ዝግጅት ከዚች ሴት ጋር የመስራት ዕድሉን በማግኘቷ የፋሽን ሾው ከሚያቀርቡት አንዷ ነበረች- የዛኔዋ ወጣት የአሁኗ ዲዛይነር ትዝታ። ጊዜው ወደ ሙያው ለመግባት የወሰነችበት ወቅት እንደነበር ትናገራለች።

ከዚያም በ2012 ዓ.ም “ሚስ ጊፋታ” በሚል በሶዶ ስታዲየም የፋሽን ሾው ማዘጋጀቷን አጫውታናለች። በዚያም እውቅናን ያገኘችበት አጋጣሚ መሆኑን እንዳልዘነጋች ነው የምትናገረው። በወቅቱ የባህል አልባሳት ተቀባይነት ዝቅተኛ እንደነበር የምትናገረው ዲዛይነርና የዲኮር ባለሙያ ትዝታ የመጀመሪያ ዘመናዊ ይዘት ያላቸው የባህል አልባሳትን በከተማው ያስተዋወቀች ሴት ለመሆን ችላለች። ከተዘጋጀው የፋሽን ሾው በኋላ ግን ተቀባይነቱ እየጨመረ መጥቷል። በዚያም ብዙ ባለስልጣናትን እንዲሁም ወደ አካባቢው የሚመጡ እንግዶችን የማልበስ ዕድሉን አግኝታለች። የምታዘጋጃቸውን የባህል አልባሳት፣ ጫማዎች፣ ቦርሳዎች እና መጋረጃዎች ወደውጭ ሀገር ለመላክም በቅታለች።

ከዚሁ ስራዋ ጎን ለጎን የዲኮር ስራ ትሰራለች። ለሰርግ፣ ለምርቃት፣ ለልደት እና ለተለያዩ መድረኮችና ሁነቶች የማሳመር ስራ ትሰራለች። በዚህም በአካባቢዋ ለነበሩ ወጣቶች ምሳሌ መሆን መቻሏን ትናገራለች። ለዚህ ደግሞ ከእሷ በኋላ በከተማው የተለያዩ ዲዛይነሮች ወደ ስራ መሰማራታቸው ምስክር መሆኑን አስረድታናለች። በስራ ዓለም ውስጥ መውደቅ መነሳት የሚያጋጥም እንደሆነ የብዙዎች ህይወት ይመሰክራል። የተለያዩ ፈተናዎችን መጋፈጥም ወደስኬት የሚያንደረድሩ መሆናቸውንም እንዲሁ።

በንግድ ስራ ውስጥ ችግር ሲያጋጥም ወደኋላ የሚመለስ ስኬታማ መሆን አይችልም። ይልቁንም ከችግሩ የሚወጣበትንና የተሻለ ስራ የሚሰራበትን ዘዴ በመዘየድ ውጤታማ ለመሆን የሚያልም ሰው ስሌታማ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ዲዛይነርና የዲኮር ባለሙያ ትዝታም በስራ መሐል ያጋጠማትን ችግር የተወጣችበትን መንገድ እንደሚከተለው አጫውታናለች፦ “የዲዛይን ስራ ስጀምር በሰው ዘንድ ያን ያህል ተቀባይነት ስላልነበረው ለማስተዋወቅ ብዙ አድክሞኛል። በተለይም የዲኮር ስራ ምንም ፈላጊ ያልነበረው ሙያ ነበር።

በዚያም ምክንያት ሰዎች እንዲያውቁት በነፃ እስከ መስራት ድረስ ደርሻለሁ። ቀስ በቀስ በዝቅተኛ ዋጋ መስራትን ጀመርኩ። ያንን ማድረጌ ሙያው እንዲተዋወቅ እና ተገቢው ዋጋ እንዲያገኝ በር ከፍቶልኛል። ዝቅ ብለን ሰርተን ስራውን ከፍ አድርገነዋል። ይህን የመሳሰሉ ብዙ ችግሮችን አልፌ ነው እዚህ የደረስኩት” ስትለን አሁንም ፊቷ ላይ የድል አድራጊነት ስሜት ነበር የሚነበበው። በአሁኑ ሰዓት የምፈልገውን ዲዛይን በምፈልገው ግብዓት የሚሰሩ ሸማኔዎች አሉኝ። ያንን ተጠቅሜ ዘመናዊ መልክ ያላቸውን አልባሳት፣ ጫማዎች፣ ቦርሳዎች በትዕዛዝም እሰራለሁ፤ ለገበያም አቀርባለሁ። ቀሚስ ከ2ሺ ብር ጀምሮ እስከ 10 ሺ ብር የምትሰራ ሲሆን ጫማዎችን ደግሞ 1ሺ 5መቶ ብር ድረስ ትሸጣለች። አላባሾችን የሴቶች 1ሺ 3መቶ ብር ለወንዶች ደግሞ 1ሺ 5 መቶ ብር ድረስ ይሸጣል። የወንዶች ኮት 5 ሺ ብር ሲሆን ቡሉኮ 2ሺ 5 መቶ ብር ድረስ እንደሚሸጥ ነው የገለፀችው።

የሚያግዙሽ ሰዎች አሉ ወይ ስንል ላነሳንላት ጥያቄ እንደሚከተለው መልሳልናለች፦ ረዳቶቼ ወንድሞቼ ናቸው። አጋጣሚ ወንድሞቼ ትምህርታቸውን ጨርሰው ቤት ተቀምጠው ነበር። አሁን 6 ሆነን ስራውን በጋራ እየሰራን እንገኛለን። ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ወደ ስራው ተቀላቅለዋል። እንዲሁም ባለቤቴ በሌላ ሙያ የተሰማራ ቢሆንም እኔን በሃሳብ ያግዘኛል። ትልቅ ቦታ እንድደርስ ስለሚፈልግ የተሻለ ስራ እንድሰራ ይመክረኛል። “በእርግጥ ልጅ ሆኜም የራሴ ስራ እንዲኖረኝ እመኝ ነበር። ለዚያም በልጅነቴ የተለያዩ ትንንሽ ንግዶችን እሞክር ነበር።

ያሰቡበት ለመድረስ ዝም ብሎ መቀመጥ አይገባም። መሞከር ከዚያም ጠንክሮ መስራት አስፈላጊ ነው” ትላለች። “አንድ ስራ ላይ መቆየት አልፈልግም። በተለይም በስራው የምፈልገውን ዓይነት ውጤት ካላገኘሁበት አልቆይበትም” በማለት፥ ከዚያ ይልቅ ወደ ሌላ ስራ ማማተሩ እንደሚቀላት ለውሳኔም እንደማትቸገር ነው ያጫወተችን። ከልምዷ በመነሳት ለሴቶችም እንዲህ በማለት ነበር ምክሯን የለገሰችው፦ ልጅ ሆኜ እናቴ ያሳደገችኝ አባቴ በሚያስገኘው ገቢ ነበር። በዚያም እናቴ እጇ ላይ ባላት ነገር አብቃቅታ እንጂ የፈለገችውን ማድረግ አትችልም ነበር። እኔም ያ ነገር በህይወቴ እንዲደገም አልፈለኩም። ለዚያም ነው ተግቼ ለመስራትና ከፍ ያለ ቦታ ለመድረስ የወሰንኩት።

በዚህም ምክንያት የወንድ እጅ ላለማየት ወሰንኩ። አሁንም አድርጌው አላውቅም፤ ወደፊትም አላደርገውም። ይህም የፈለኩትን እያደረኩ ከመኖር በላይ ልጆቼ የእኔን ጥንካሬ እያዩ እንዲያድጉ አስችሎኛል። ሌሎች ሴቶችም እንዲሁ እንዲሆኑ ነው የምፈልገው። በማንም ላይ ጥገኛ መሆን የለባቸውም።

ጠንክረው ከሰሩ ፍላጎታቸውን አሟልተው መኖር ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። በቀጣይ ያላትን ዕቅድ እንድታካፍለን ጠይቀናት እንዲህ በማለት ነበር ያጫወተችን፦ “ወደፊት ቅርንጫፎችን የመክፈት እቅድ አለኝ።” ከዚያም በተጨማሪ ስራዎቼን አለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖራቸው ማድረግም ሌላኛው ዕቅዴ ነው። ምርቶቼን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዕቅድም እንዲሁ።