ለረጅም ዓመታት በብሔረሰቡ ዘንድ ሲጠየቅ የቆየው በልዩ ወረዳ የመደራጀት ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ገለፁ

ለረጅም ዓመታት በብሔረሰቡ ዘንድ ሲጠየቅ የቆየው በልዩ ወረዳ የመደራጀት ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ገለፁ

አደረጃጀቱ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር በልዩ ወረዳው ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ምቹ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢማም ሀያቱ ሻሚል የቀቤና ልዩ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ በብሔረሰቡ ዘንድ የልዩ ወረዳ ጥያቄ ከ30 አመታት በላይ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ሲጠየቅ መቆየቱን አስታውሰው አሁን ላይ አዲስ በተዋቀረው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በልዩ ወረዳ እንዲደራጅ ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በልዩ ወረዳው ውስጥም ሆነ ከሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ከሚገኙ ወንድም ህዝቦች ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ብሔረሰቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ምቹ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል።

የልዩ ወረዳው የባህል ኪነት ቡድን አስተባባሪ አርቲስት መኪዩ ናስር በበኩሉ ብሔረሰቡ በልዩ ወረዳ መደራጀቱ ለህብረተሰቡ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን በማንሳት ብሄረሰቡ ባህሉን፣ ታሪኩና ቋንቋውን ይበልጥ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብሏል።

በቀጣይ ከብሔረሰቡ በተጨማሪ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተዋቀሩ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነትና ሰላም ማጠናከር የሚያስችሉ የሙዚቃ ስራዎችን ለመሥራት ዕቅድ እንዳላቸውም ነው ያስረዳው።

ሌላኛው ወጣት ሀያቱ ሁሴንና አብድረዛቅ ሸምሱ በሰጡት አስተያየት የህዝቡ የልዩ ወረዳ ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ጠቁመው የአደረጃጀቱ ጥያቄው ምላሽ ማግኘቱ ከመንግስት ጎን በመሆን የልዩ ወረዳውን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ ክስተት ነው ብለዋል።

በልዩ ወረዳው ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ችግር መኖሩን ያወሱት አስተያየት ሰጪዎቹ መላው የልዩ ወረዳው ማህበረሰብና ባለሃብቱ ከአመራሩ ጋር በመቀናጀት የልዩ ወረዳውን ልማት ለማፋጠን መረባረብ ይገባል ብለዋል።

በተለይም ብልጽግና ፓርቲና መንግሥት የህዝቡን በልዩ ወረዳ የመደራጀት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ላበረከቱት አስተዋጽኦ አስተያየት ሰጪዎቹ ምስጋቸውን አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን