“መልካሙን ነገር አብዝቶ በመጠቀም፣ የሚያለያዩንን ደግሞ በማጥበብ በጋራ እንስራ” –  አቶ ታደለ ጥላሁን

“መልካሙን ነገር አብዝቶ በመጠቀም፣ የሚያለያዩንን ደግሞ በማጥበብ በጋራ እንስራ” –  አቶ ታደለ ጥላሁን

በቤተልሔም አበበ

በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦች የራሳቸው መገለጫዎች አሏቸው፡፡ እነዚህ መገለጫዎች ደግሞ የማህበረሰቦቹ መታወቂያ ሆነዋል፡፡ ባላቸው ባህል፣ ታሪካዊ ቅርስ፣ አልያም በሚያመርቱት ምርት እንዲታወቁ ያስችላቸዋል፡፡ በብዙዎች ዘንድ በቡና እና በእንሰት ምርት የምትታወቅ ከተማ ናት፡፡

ከምትሰጠው ምርት ባለፈ በኢኮኖሚው፣ በስፖርቱ፣ እንዲሁም በፖለቲካው ዘርፍ በርካታ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን ማፍራት የቻለችም ናት ይርጋጨፌ፡፡ ባለታሪካችን አቶ ታደለ ጥላሁን ይባላሉ። ይርጋጨፌ ካፈራቻቸው ወርቃማ ልጆች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ውልደታቸው እና እድገታቸውም በዚሁ ከተማ ነው፡፡ በከተማዋ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በአካውንቲንግ ከዲላ ዩንቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ድግሪያቸውን ደግሞ በእንሰሳት እርባታ (animal husbandry) ከሚዛን ቴፒ ዩንቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ባለታሪካችን ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት ናቸው፡፡ የልጅነት ጊዜያቸውን ሲያጫውቱን ወላጅ አባታቸው በልጅነታቸው ካረፉ በኋላ በርካታ የህይወት ውጣ ውረድ ገጥሟቸው እንደነበር ያነሳሉ፡፡ በዚህም ከወላጅ እናታቸው ጋር በጋራ በመሆን ኑሮን ለማሸነፍ በርካታ የህይወት ገጠመኞችን ማለፍ እንደቻሉም ያስታውሳሉ። የአቶ ታደለ ወላጅ እናት ወ/ሮ አዳነች ችግሮችን በመጋፈጥ ነገ ሰው መሆን እንደሚቻል ይመክሯቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ዛሬ ላይ ለመድረሳቸው ትልቁን ድርሻ ወላጅ እናታቸው እንደሚይዙም ያነሳሉ፡፡

ለዚህም እንደ ምክንያት የሚገልጹት ከራስ ይልቅ ለሰው እና ለአካባቢ ዕድገት እንዴት መኖር እንደሚቻል እየነገሯቸው ማሳደጋቸው ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ሞያ ላይ ጠንካራ አመራር መሆን የሚቻለው በምን አግባብ ነው የሚለውን አቅጣጫ ከታላቅ ወንድማቸው እንደቀሰሙም ይናገራሉ፡፡ ባለታሪካችን በህይወት የሚገጥሙ ፈተናዎችን ለማለፍ የጸና አቋም ያስፈልጋል የሚል አስታየታቸውን ይለግሳሉ፡፡ የህይወት መርህ አድርገው የሚመሩት ችግሮችን ከፈጣሪ ጋር በመሆን ማለፍ ይቻላል በሚል ፅናት ነው፡፡

የተለያዩ ውጥረቶች ሲገጥማቸውም ፍቅርን፣ ደስታን በመለገስ ደስተኛ እንዲሆኑ የምታደርጋቸውን ባለቤታቸው በህይወታቸው ውስጥ ትልቁን ድርሻ በመያዝ ሚናዋ የጎላ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ስለሆነም ከጠንካራ ወንድ በስተጀርባ ጠንካራ ሴት መኖሯን የሚገልጸው ብሒሉን ሲደግፉም ይስተዋላሉ፡፡ አቶ ታደለ በተለያዩ የመንግስት ተቋማትም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት መቻላቸውን ያለፉበት መንገድ ምስክር ነው።

በይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ፣ ባህል፣ ቱሪዝምና መንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የከተማው ንግድ እና ገበያ ልማት ምክትል መምሪያ ኃላፊ፣ በፓርቲ ውስጥ የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ፣ የጌዴኦ ዞን ኢንቨስትመንት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ እንዲሁም የዞኑ ፋይናንስ መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ ህገወጥ ግንባታ አፍራሽ ግብረሃይል ሰብሳቢ ሆነው የሰሩ ሲሆን አሁን ላይ የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

አቶ ታደለ ወደ ከንቲባነት ቦታ ከመጡ ሶስት አመት ሊሞላቸው እንደተቃረበ ነግረውናል፡፡ የተለያዩ የስራ ሀላፊነትን መወጣት የሚቻለው መጀመሪያ ለዓላማ መቆም ሲቻል እንደሆነ ያምናሉ፡፡ የስራ ተሞክሯቸው ልምድ የሚቀሰምበት እና ለመረዳትም የማያዳግት ሆኖ አግኝተዋል፡፡ አንዳንዴ “የተማሩ ናቸው፤ ያውቃሉ” ተብለው ትኩረት የሚሰጣቸው አካላት በትንሽ ስህተት ወድቀው ይገኛሉ፡፡ ባለታሪካችን ግን በተግባር የታገዘ እውቀትን በመጠቀም የተለያዩ ዘርፎችን በብቃት በመምራት ውጤታማ ስለመሆናቸው ያካበቱት የስራ ልምዳቸው አብነት ነው፡፡ በተሰጣቸው የስራ ዘርፍ ሰዎችን በመጠየቅ ደካማ እና ጠንካራ ጎኖችን በመረዳት የሚታዩ ክፍተቶችን በመሸፈን አቅማቸውን እንደሚያሳድጉም ይገልጻሉ፡፡

በዚህም ከሰዎች ጋር ተግባብተው እንዲሰሩ እና ተመራጭ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው ይናገራሉ፡፡ ይርጋጨፌ ከተማ ረጅም እድሜ እንዳላት እና በአፈታሪክ ደረጃ ሰባ አመት እንዳስቆጠረች ይነገርላታል፡፡ ለከተሞች ዕድገት በቂ የመሰረተ ልማት መሟላት ዋንኛው እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ከወረዳ እስከ ፌደራል፣ ከፍ ሲል ደግሞ ከውጪ ሀገራት በሚገኝ የእርዳታ ድጋፎች ከተሞች እንዲለሙ ይደረጋሉ፡፡ ተግባሩ በራሱ የባለድርሻ አካላትን ቁርጠኝነት እና ርብርብ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም የይርጋጨፌ ከተማ በብዙዎች ዘንድ እውቅና ቢኖራትም በዛው ልክ የተሟሉ መሰረተ ልማቶች ባለቤት አለመሆኗን ታዝበናል፡፡ ከተሞች በየጊዜው የዕድገት ደረጃዎች እንደሚወጣላቸው የሚናገሩት ባለታሪካችን ከተማዋ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ አንጻር ለውጡ ዘገምተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ይህም የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲሁም ከዞን፣ ከወረዳ፣ ከባለሀብቶች፣ ከክልል እና ከፌደራል ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ካለመስራት የመነጨ ችግር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ከንቲባው ወደ ቦታው ከመምጣታቸው በፊት በከተማዋ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይነሱ እንደነበር እና በዚያም ሳቢያ በአመራሩም ይሁን ከታችኛው መዋቅር አንስቶ እስከ ከፍተኛው ድረስ ቁርሾዎችና አለመግባባቶች እንደነበሩ ያነሳሉ፡፡ ይህን በመረዳትም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በሰለጠነ መንገድ በማቀራረብ ችግሮች እንዲፈቱ በማድረግ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት የባለታሪካችን ድርሻ የጎላ ነው፡፡ ተቀራርቦ በቅንጅት ያለመስራት እንዲሁም የገቢ ደረጃን አለማሳደግ ለከተማዋ ዕድገት ማነቆ ስለመሆኑም ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ታዲያ የክልሉ መንግስት ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም 2 የድልድይ ግንባታዎች የተከናወኑ ሲሆን ዞኑም መሰል የግንባታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡ ህዝብን እና አመራርን በማቀራረብ አብሮ እዲሰሩ በማድረግ በከተማዋ የሚስተዋለውን የመሰረተ ልማት እና ሌሎችንም ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ ይገኛሉ፡፡ “ኢትዮጵያ በዕድገት ጎዳና ውስጥ ሆና ከፍተኛ ውጤቶች እየተመዘገቡ ቢሆንም በዛው ልክ ከባድ ፈተናዎች እየገጠሟት ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ፈተናውን መወጣት የምንችል እንደሆነ እረዳለሁ” ሲሉ ከንቲባው ይደመጣሉ፡፡

“ችግሮችን በጋራ በመስራት መወጣት እና ማለፍ እንድንችል ያሉንን የተፈጥሮ ጸጋዎች በአግባቡ ካልተጠቀምን የሚደበዝዙ በመሆናቸው ለሁሉም የወል እውነት የሆነው መልካሙን አብዝቶ በመጠቀም የሚያለያዩንን በማጥበብ መስራት የሁላችንም ድርሻ መሆን አለበት“ ሲሉ ምክረ ሀሳባቸውን ይለግሳሉ፡፡