ያደሩ ችግሮችና አዳዲስ ፍላጎቶችን ማዕከል ያደረጉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ

ያደሩ ችግሮችና አዳዲስ ፍላጎቶችን ማዕከል ያደረጉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የኮንታ ዞን ሽግግር ምክር ቤት 4ተኛ ዙር 7ተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 20ኛ መደበኛ ጉባኤ ተካሂዷል፡፡

ጉባኤዉን በንግግር የከፈቱት የዞኑ ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ብረሃኑ አቱሞ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዋነኛ ትኩረት በመሆኑ ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት ጥረት ማደረጉን ገልፀዋል።

ለሀገሪቷ ብልጽግና ሰላም አስፈላጊ እንደሆነና ሰላሟን የማይፈልጉ የፀረ ሠላም ኃይሎችን ድርጊት በምክር ቤቱ አባል ስም አውግዘዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነጋ አበራ ለምክር ቤቱ አባላት የ2015 በጀት አመት የዞኑን አስፈፃም መስሪያ ቤቶች የሥራ ሪፖርትና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አቅርበው ውይይት ተደርጓል።

ዋና አስተዳዳሪው እየተካሄደ ያለው ለውጥ ውጤታማ፣ ዘላቂና ተቋማዊ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ሠላምና ደህንነት ተግባራትን አብራርተዋል።

የግብርና ቴክኖሎጅን ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የተቻለ ቢሆንም በትንሽ ማሳ የተሻለ ምርት የማምረት አስተሳሰብ ሊዳብር እንደሚገባ የምክር ቤቱ አባላት በስፋት መክረዋል።

የህዝቡን መሠረታዊ የመልማት ጥያቄ ለመፍታት በሚያስችል መልኩ የገቢ አማራጮችን ተጠቅሞ ከመሰብሰብ አኳያ ጉድለት ያለበት ስለሆነ የምክር ቤቱ አባላት ተገቢ እገዛ መደረግ እንዳለበት ውይይት ተደርጓል።

የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2015 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርትና የ2016 በጀት አመት ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎ በሙሉ ድምጽ ፀድቋል።

የዞኑ 2016 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድና የዞኑ አጠቃላይ አመታዊ በጀት 5 መቶ 99 ሚሊየን 8 መቶ 25 ሺህ 21 ብር ቀርቦ ውይይት ተደርጎ በጉባኤው ጸድቋል።

በጉባኤው የተገኙት የምክር ቤት አባል ወ/ሮ እቴነሽ በቀለ በተጠናቀቀው በጀት አመት በምክር ቤቱ አባላትና ቋሚ ኮሚቴዎች የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ ተናግረዋል።

በመጨረሻም በክልል መንግስትና በዞኑ በጀት እየተገነቡ ያሉ የተለያዩ ተቋማትና ፕሮጀክቶች በምክር ቤቱ አባላት የተጎበኙ ሲሆን አረንጓዴ አሻራ የማኖር መርሀ-ግብርም ተከናውኗል።

ዘጋቢ፡ አብዮት እሸቱ – ከዋካ ጣቢያችን