ከ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ልማታዊ ባለሀብቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ

ከ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ልማታዊ ባለሀብቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 10/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በ2015 በጀት ዓመት ከ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ልማታዊ ባለሀብቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል።

ክልሉ በቀጣይ 2016 በጀት ዓመት ከ 3 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ለማስመዘገብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ሚና የጎላ በመሆኑ እየተሰራበት እንደሚገኝም የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከበደ ተስፋዬ ተናግረዋል።

ኢንቨስትመንት ለሀገር እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የላቀና ኢኮኖሚን የሚያረጋጋ በመሆኑ ከ32 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ተዘጋጅተው 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ካፒታል ያሰመዘገቡ 141 ፕሮጀክቶች ወደ ስራ መግባታቸውን ኃላፊው ገልፀዋል።

ፕሮጀክቶቹ በአከባቢው ለ79 ሺህ 335 ሰዎች ጊዜያዊና ለ2ሺህ 892 ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድልን በመፍጠር 3 ሺህ 599 አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማደረጉን አቶ ከበደ አውስተው የክትትልና ድጋፍ ስራ በማከናወን ከማስጠንቀቂያ እስከ መሬት ባንክ ያልለሙት መሬቶችን ገቢ የማደረግ እረምጃ ተወስዷል ብለዋል።

ልማታዊ ባለሀብትን ከማበረታታት አኳያ መንግስት የተለያዩ አዋጆችና ደንቦችን እያሻሻለ ከመሆኑም ባሻገር 25 በመቶ ካፒታል በማስመዘገብ እና 75 በመቶ ብድር እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ እንደሚገኝ ኃላፊው ገልፀዋል።

በቀጣይ በጀት ዓመት በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከ 3 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል አዲስ ከሚመጡ ባለሀብቶች ለማስመዘገብ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አቶ ከበደ ጠቁመዋል።

ክልሉ ለልማት ያለው አቅም ከፍተኛ በመሆኑ በተለያዩ ዘርፎች ልማታዊ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ ከርዕሰ መስተዳደር ጀምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኝም ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን