ሰውና ተፈጥሮ የታረቁበት

ሰውና ተፈጥሮ የታረቁበት

በይበልጣል ጫኔ

አንድም አዲስ ነገር ፍለጋ÷ አሊያም የተሻለ ከባቢን በመሻት÷ የሰው ልጅ ህይወት በመጓዝ ላይ የተመሰረተ ነው። መጓዝ፣ መሄድ፣ መድረስ፣ መመለስ፣ እንደገና ደግሞ መሄድ … “አያልቅም ይህ ጉዞ …” እንዲል÷ ገጣሚ እና ሰዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ። እኛም እንጓዛለን።

በተጓዥ ተከታይ አምዳችን በኩልም ያየነውን እናሳያችኋለን። የዛሬው ተጓዥ ተከታይ አምዳችን÷ ምድረ ገነት ወደሆነው ዳውሮ አካባቢ ነው ትኩረቱን ያደረገው። ዳውሮ ሃላላ ኬላ። መነሻውን ከሃገራችን ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ አድርጎ÷ ወደ ዳውሮ ዞን ሃላላ ኬላ ሪዞርት መጓዝ የፈለገ ሰው÷ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም ይችላል። ለአብነትም ሀገሩን እየጎበኘ÷ ከተሞቿን እና ህዝቦቿን እየቃኘ መሄድ ለወደደ÷ ከአዲስ አበባ ዳውሮ ድረስ በመኪና መጓዝ ይችላል። ረዥም መንገድ በመኪና መጓዝ የሚሰለቸው ደግሞ÷ በአውሮፕላን በመጓዝ መንገዱን ማሳጠር ይችላል።

በዚህኛው አማራጭ ደግሞ እንደየምርጫው ከአዲስ አበባ አርባ ምንጭ፣ ከአዲስ አበባ ጅማ÷ አሊያም ከአዲስ አበባ ሃዋሳ በአውሮፕላን ተጉዞ÷ ቀሪውን መንገድ በመኪና ሊቀጥል ይችላል። በነገራችን ላይ “ይኼ ሁሉ አማራጭ አይመቸኝም። ምቾቴ ሳይጓደል÷ ጊዜዬንም ሳላባክን ቦታው ላይ መድረስ እፈልጋለሁ” የሚል ሀገር ጎብኚ ቢኖር÷ ለእርሱም አማራጭ አለ። የግል ሂሊኮፍተሩን ይዞ ወደ ስፍራው ቢያቀና ሁለት ሂሊኮፍተር ማሳረፍ የሚችል የተሰናዳ ቦታ አለው።

ሁሉ እንደመሻቱ መረጃ ያገኝ ዘንድ ያሉትን አማራጮች ለመጠቆም ያክል እንጂ ከላይ ያለውን ሃሳብ ማስፈሬ÷ የኛ መነሻ ሃዋሳ ናት። ሃዋሳ÷ በየጊዜው ውበቷ የሚጨምር ሰላማዊት ከተማ ናት። አሁን ደግሞ በተለየ መልኩ ዲዛይን የተደረገው መግቢያ በሯ፣ በዋና መንገዶች ግራና ቀኝ ያሉ የእግረኛ መንገዶቿን ለማስዋብ የተሰሩ ስራዎች፣ ታቦር ተራራን የማስዋብ ፕሮጀክቷ እና መሰል የከተማ ልማት እንቅስቃሴዎቿ ከተማዋን ዘወትር አዲስ ነገር የሚታይባት አድርገዋታል።

መነሻችን ሃዋሳ ናት አላልኳችሁም?÷ መቼም ከሃዋሳ የተነሳ ሰው አንዳች ድካም ሳይሰማው ነው÷ ወላይታ ሶዶ የሚደርሰው። በአስፋልት መንገዱ አዲስነት ላይ የትራፊክ መጨናነቅ አለመኖሩ ተደምሮ÷ ጉዞን ምቹ እና ቀላል የማድረግ ባህሪ አለው። በተለይም የስጋ ወዳጅ ለሆነ ሰው÷ ረፋድ ላይ ወላይታ ሶዶ መገኘት የተለየ ድባብ አለው። ቢያሻው ጥሬ ስጋ በስድስት ዓይነት ዳጣ(ማባያ)÷ አሊያም ቀልቡ የወደደውን ዓይነት ሌላ ምግብ ተመግቦ መንገዱን መቀጠል ይችላል። ከወላይታ ሶዶ ቀጥሎ የኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ዋና ከተማ በሌ እስኪደረስ ድረስ÷ በመንገድ ግራና ቀኝ የሚታዩ አነስተኛ የገጠር መንደሮች፣ በልዩ ልዩ ሰብል የተሸፈኑ የገበሬ ማሳዎች፣ አረንጓዴ ስጋጃ የለበሱ ተራራዎች፣ በአረንጓዴ ቅጠሎቻቸው ፍሬያቸውን ያስጠለሉ የማንጎ እና ሌሎች የፍራፍሬ ዛፎች በስፋት ይታያሉ።

የነዚህ ፍራፍሬ ውጤትም ሶርቶ በምትባለው የገጠር ቀበሌ ላይ ጎልቶ ይታያል። በዚህ ስፍራ ከጓሮ የተለቀሙ ትኩስ የማንጎ፣ ፓፓያ እና መሰል ፍራፍሬዎች እንደልብ ይገኛሉ። ከበሌ ከተማ ወረድ ብሎ÷ በጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ አማካኝነት የተፈጠረ ትልቅ ሰው ሰራሽ ኃይቅ አለ። ከዓመታት በፊት በኪንዶ ኮይሻ በኩል÷ ወላይታ ከዳውሮ ጋር የሚገናኝበት የብረት ድልድይ ነበረ። ይኼ ሰው ሰራሽ ኃይቅ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ድልድዩ በውሃ ተውጧል። የአካባቢው ነዋሪዎችም የቀደመ ቅርብ መንገዳቸውን ፍለጋ በድልድዩ ፈንታ ሞተር ጀልባ ይጠቀማሉ። ከሩቅ ስፍራ የሚመጡ ተጓዦች ግን በአብዛኛው ይህንን ሃይቅ ዞረው ነው ወደ ዳውሮ የሚጓዙት።

በነገራችን ላይ÷ በስራ አጋጣሚ ሀገር ውስጥ የሚገኙ በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ሃይቆችን የማየት ዕድሉ ነበረኝ። እንደ ጊቤ 3 ሰው ሰራሽ ኃይቅ የገነነ በሰው እጅ የተሰራ ውበት ያለው ኃይቅ ግን እስከዛሬ አልገጠመኝም። ከዚህ ስፍራ ተጉዘን ጥቂት የገጠር ቀበሌዎችን አቋርጠን ነው እንግዲህ÷ ዳውሮ ዞን ሃላላ ኬላ ሪዞርትን የምናገኘው። ዳውሮ አስገራሚ መልክዓ ምድር የታደለ ድንቅ ምድር ነው። ተራሮች ለአንዳች የጋራ ጉዳያቸው ከያሉበት ተሰባስበው እዚሁ የቀሩ ይመስላሉ÷ ልብ ብሎ ለሚያያቸው። በዚያው ልክ ተራሮቹን የከበባቸው አረንጓዴ ተፈጥሮ÷ ከተማ ለምኔ የሚያሰኝ የዓይን ምግብ ነው።

ለዘመናት አብረዋቸው የኖሩት ቡራቶ፣ ሲሊሶ እና መሰል ቅቤ የጠገቡ የባህል ምግቦቻቸው÷ ህዝቡ ሰጥቶ የማያልቅበት እንደሆነ አፍ አውጥተው ይናገራሉ። ለወትሮው ሰው እና ተፈጥሮ ሲጣላ ነው ዘመናትን ያሳለፈው። የሰው ልጅ በደረሰበት ሁሉ አንድም ለመኖሪያው ሲቀጥልም የእርሻ መሬት ፍለጋ ተፈጥሮን ሲጎዳ ነው ዘመን የተቆጠረው። አሁን ግን ነገሮች እየተለወጡ ይመስላል። ለዚህ ደግሞ በድንቅ ተፈጥሮ መካከል የሚገኘው ሃላላ ኬላ ሪዞርት አንዱ ማሳያ ነው። ሪዞርቱ የተሰራበት ጥራት እጅጉን ይገርማል። ተፈጥሮ ሳይጎዳ÷ ባለበት ሁኔታ በዚህ ልክ ማዘመን መቻሉም የሚደነቅ ነው። በእርግጥም በዚህ ስፍራ ለአንድ ቀን አይቼው ልመለስ ብሎ የተገኘ ሰው÷ በትንሹ ሦስት እና አራት ቀናት እንዲቆይ ይገደዳል። በተለያየ ጊዜ ቦታውን የረገጡ ሰዎች የሚነግሩንም ይህንን እውነት ነው።

የእንግዳ ማረፊያዎቹና መኝታ ክፍሎቹ፣ መመገቢያ ስፍራዎቹ፣ ከቤት ውጪ ያሉት መናፈሻዎች፣ የዋና ገንዳዎች፣ ሙዚየሙ፣ ሳይክል መጋለቢያ ስፍራው እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ቦታዎቹ ሲበዛ ንፁህ እና ዘመናዊ ናቸው። እዚህ ስፍራ የደረሰ ሰው÷ ቢችል ወደ ማህበረሰቡ ጎራ ብሎ ባህሉን እና አኗኗሩን ቢመለከት መልካም ነው። በጊዜ ማጣት÷ አሊያም በአንዳች የተለየ ምክንያት ይህንን ማድረግ ባይችል ግን የሃላላ ኬላ ሪዞርት ሙዚየም ውስጥ ዳውሮን በድርበቡ ሊያያት ይችላል። ዳውሮ ተነስቶ÷ ዲንካ ሊዘነጋ አይችልም።

ዲንካ በጣም ረዥም የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያ ነው። ረዥም ቀርከሃ ከቀንድ ጋር ተጣምሮ ነው አስገምጋሚ ድምፅ የሚያወጣው። እንደቁመቱ እና እንደ አጨዋወት ስልቱ ዲንካ አምስት ዓይነት ድምፅ ያወጣል። ሌላኛው የሙዚቃ መሳሪያ ደግሞ ከበሮ ነው። ከበሮ በዳውሮዎች ስልተ ምት ሰባት ዓይነት ሪትም አለው። የዲንካውንም ጨዋታ የሚመራው ከበሮው ነው። ታድያ ይኼ ሁሉ በሙዚየሙ ውስጥ በክብር ተቀምጦ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ የዳውሮዎች አልባሳት፣ የማብሰያ እና የመመገቢያ ቁሳቁሶች እንዲሁም ልዩ ልዩ የቤት ውስጥ ባህላዊ መገልገያዎች ሙዚየሙ ውስጥ በክብር ተቀምጠው÷ ስለ ህዝቡ አኗኗር ወግ እና ባህል በመመስከር ላይ ይገኛሉ።

ሃላላ ኬላ ሪዞርትን በምሽት መመልከት÷ ከቀኑ እጅግ የተለየ ድባብ አለው። ውድቅት ሲሆን÷ በምድሪቱ ላይ ጨለማ ሲሰለጥን ይህንን ስፍራ ላስተዋለው÷ በልዩ ጥበብ ስፍራውን ያስዋቡት ቄንጠኛ መብራቶች ከህንፃዎቹ ውበት ጋር ተዳምረው÷ በተራሮች መካከል የተበተኑ ከዋክብት ይመስላሉ። ሃላላ ኬላ ሪዞርት እጅግ ውጤታማ ስራ ነው። ወንጪ፣ ጎርጎራ እና መሰል ፐሮጀክቶች ሲጠናቀቁ÷ ለሀገራችን ቱሪዝም ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ የጎላ ነው።