የደቡብ ሱዳናዊያን ሌላው ፈተና

የደቡብ ሱዳናዊያን ሌላው ፈተና

በፈርኦን ደበበ

ከረጅም ጊዜ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ነጻነት መቀዳጀቷ ተስፋዋን አለምልሞት ነበር። ሠላም ነግሶ የዜጎች ማህበራዊ ህይወትም ይሻሻላል የሚል ተስፋ ተፈጥሮ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ተስፋዎች እውን መሆን አልቻሉም፡፡

በየጊዜው የሚወጡ ዘገባዎችም ሲያሳዩ የቆዩት ይህንን ነው፡፡ ድህነት፣ በተለያዩ ፖለቲካ ኃይሎች መካከል የሚፈጠር ግጭት እንዲሁም የምግብ እጥረት የህዝቡን ኑሮ ሲፈታተኑ ቆይተዋል፡፡ እያገባደድን ባለው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮችም እንዲሁ፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ሀገሪቱን ከሰሜን በኩል በሚያዋስናት ሱዳን የተከሰተው ጦርነት ችግሯን አባብሶባታል፡፡

አስቀድሞ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ወደ ሱዳን በስደት መልክ የሄዱ ሲሆን አሁን ጦርነቱን ሸሽተው መምጣታቸው አገልግሎት አሰጣጡን አወሳስቦታል፡፡ ዳዴ በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኘው የኑሮ ዘይቤ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲገባ እያደረገው ይገኛል፡፡ ዓለም ትኩረቱን ዋና ዋና ግጭቶች ባሉባቸው ቦታዎች ላይ ባደረገበት በአሁኑ ጊዜ ሁኔታው ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ማንም መገመት ይችላል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰሞኑን ያወጣው መግለጫም “ሀገሪቱን አትርሷት” የሚል መልዕክት ያለው ነው፡፡ ሀገሪቱ ነጻነቷን ለማግኘት የተከፈለው መስዋዕትነት መና እንደቀረ አሳይቷል በሚል መንደርደሪያ ሀሳብ ድርጅቱ መግለጫ ሲያወጣ ይህም ቢሆን የሚሰጣትን ትኩረት ሊያሳጣ አይገባም ብሏል የሀገሪቱ የተባበሩት መንግሥታት ተወካይን በመጥቀስ አፍሪካ ኒውስ እንደዘገበው፡፡

ከሱዳን ነጻነቷን ከተቀዳጀችበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ወዲህ ሀገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት ተዘፍቃ እንደቆየችና በዚህ መነሻም እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2018 400 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ለሞትና እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩት ለመፈናቀል መዳረጋቸውን ጠቅሷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2018 የተፈረመው የሠላም ስምምነት ግን በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና በተፎካካሪያቸው ሪክ ማቻር መካከል ሠላም እንዲወርድ አስችሏል ብሏል፤ የሥልጣን መጋራት መርሆን መነሻ በማድረግ፡፡ ይህ ከሆነ በኋላም ቢሆን ግጭትን በሚቀሰቅሱ ታጣቂዎች አማካይነት ውጥረቶች ሲከሰቱ መቆየታቸውን አስታውቆ ችግሩ በዓለም ላይ ለጋ ዕድሜ ባለቤት በሆነችው ሀገር ላይ ያስከተለውን ጫና ጠቅሷል፡፡

በዚህ ላይ የተጠቀሱት ኒኮላስ ሀይሰን ናቸው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ሱዳን ሠላም ተልዕኮ አስፈጻሚ ለጸጥታው ጥበቃ ም/ቤት ተናግረዋል እንደተባለው ላለፉት ሁለት ወራት በሱዳን ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ተጽዕኖ መፍጠሩን አስታውቀው ካስከተሏቸው በርካታ ችግሮች መካከል ምጣኔ ሀብትና ጸጥታ ቅድሚያ ይወስዳሉ ብለዋል፡፡ ካለፈው ሚያዚያ አጋማሽ ጀምሮ 117 ሺህ የሚደርሱ ሴቶች፣ ህጻናትና ወንዶች ድንበር አቋርጠው ከሱዳን ወደ ደቡብ ሱዳን መግባታቸውን አስታውቀው ከእነዚህ ውስጥም 93 በመቶ የሚሆኑት ጦርነቱን በመሸሽ ከሱዳን የተመለሱ ደቡብ ሱዳናዊያን ናቸው ብለዋል፤ እነሱን ለማስተናገድ መንግሥትና ሰብአዊ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ያላቸውን ውሱን አቅም በመጥቀስ።

ከዚህ የተነሳ በተለይ በድንበር ላይ ከፍተኛ መጨናነቅ መኖሩን ጠቅሰው ግጭቱ በምጣኔ ሀብቱ ላይ ያሳደረው ጫና ትልቅ ተጽዕኖ ፈጥሯል ብለዋል በተለይ ከሱዳን የሚገቡ ምርቶች መቋረጣቸውን በማውሳት፡፡ ከፖለቲካ እንጻርም ቢሆን ጦርነቱ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሀገሪቱ የሚሰጠውን ትኩረት እንዳሳነሰ ጠቅሰው አሁን በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ለምትገኘው ሀገር አስፈላጊ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በሱዳን ሠላምን ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀው ከዚህ በተጨማሪ ለደቡብ ሱዳን ስለሚያስፈልገው የሠላም ሂደትም ጠይቀዋል።

አሁን የምንገኝበት ጊዜ ዓይናችንን ከደቡብ ሱዳን የምንነቅልበት አይደለም ያሉት የተልዕኮ አስተባባሪው ከደቡብ ሱዳን የቀሰምነው ልምድም ምን ያህል በከፍተኛ ተጋድሎ የተገኘው ድል በአጭር ጊዜ ሲከሽፍ መመልከት መቻላችን ነው ብለዋል። በግጭት አባባሽ ምክንያቶችና አቀጣጣዮች መነሻ ሊወሰዱ ስለሚገቡ እርምጃዎችም በማውሳት። ውሱን የሆኑ ሀብቶችን ለማግኘት ተብሎ በሚደረጉ ሽሚያዎች መነሻ ሰዎች መፈናቀላቸውን አስታውቀው ለዚህም በተለይ ማንነትን መሠረት አድርገው የሚነሱ ችግሮችን ጠቅሰዋል ከድህነት አስቀድሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ የጥላቻ ገጽታዎችና የጦር መሣሪያ ሥርጭትን መግታት እንደሚገባ በማስታወቅ።ከዚህ በተጨማሪ አፍሪካ ኒውስ የተባለው የመረጃ ምንጭ የአየር ንብረት ለውጥ ስለሚያስከትለው ጫናም የገለጸ ሲሆን ረሀብን አባብሶታል ብሏል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራምን ጠቅሶ እንደዘገበው አስቀድሞ እራሳቸውን መመገብ የሚችሉት ሁሉ ችግር ውስጥ መግባታቸውን የገለጹት አስተባባሪው የዓለም ምግብ ፕሮግራምም ችግሩን እንደ ሥጋት ያየዋል ብለዋል አየር ንብረት ለውጡ ያስከተላቸው ልዩ ልዩ ችግሮችን በማውሳት፡፡ ከዚህ ጋር የሚታየው ሌላው ችግር የጎርፍ አደጋ ሲሆን ለአራት ዓመታት በተለይ በንቱ በተባለችው አካባቢ ያስከተለው የመሬት መደርመስ፣ ግጦሽ መሬቶች ላይ ያስከተለው መሸርሸር እና ከሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን አስታውቋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የአቅርቦት መሥመሮችን እንዲዘጋ አድርጓል ያለው የመረጃ ምንጫችን እነዚህ አስጨናቂ ሁኔታዎች ተደራርበው ድርቁን አባብሰውታል ብሏል፡፡ ከ2/3ኛው ህዝብ በላይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ጠቅሶ ቁጥሩ ሀገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት በነበረችበት ጊዜ ያጋጠማትን ሁሉ የሚበልጥ ነውም ብሏል፡፡

የምግብና ነዳጅ ዋጋ ያስከተለው ተጽዕኖም ከዚህ ጋር አብሮ የሚታይ ነው፡፡ ችግሩን ለመከላከል የዓለም ምግብ ፕሮግራም 567 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ አስቸኳይ እርዳታ ይፋ እንዳደረገ ገልጾ ይህም ለቀጣይ 6 ሳምንታት የሚያገለግል ነው ብሏል፡፡ መንግሥታትም ከህይወት ማዳን በተጨማሪ ህይወትን በረጅም ጊዜ መቀየር በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ማተኮር እንደሚገባው በማስታወቅ፡፡ አዎን አፍሪካ እና አጠቃላይ የዓለም ህዝቦች ያሳለፏቸው የኑሮ ገጽታዎችን ከተመለከትን እንኳን ደቡብ ሱዳን ሌሎች በፖለቲካና በምጣኔ ሀብት እራሳቸውን ያደራጁ ሀገራትንም ወደ ቀውስ ውስጥ ከቷል። በተለይ በደቡብ አፍሪካ፣ ኬኒያና በናይጀሪያ አሁን እየታየ ላለው አዝማሚያ ከኑሮ ውድነት ውጭ ሌላ ምንም ማሳያ አይኖረውም፡፡ በሩሲያና ዩክሬን መካከል ካለው ጦርነት ጋርም ካስተያየነው ችግሩ እየከፋ እንጂ ምንም መሻሻል አያሳይም ምክንያቱም ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ያደረገችውን ስምምነት ለቃ በመውጣቷ ምክንያት የግብርና ምርቶች ሥርጭት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለቀነስ እና እንደ ህንድ ያሉ ሀገራትም የስንዴ ምርት ወደ ውጭ ላለመላክ ስለወሰኑ፡፡

ሁኔታውን ከደቡብ ሱዳን ጋር ስናያይዘው በተለይ ሀገሪቱ ከውስጥም ከውጭም ብዙ ፈተናዎች ያሉባት መሆኑ አሳዛኝ ያደርገዋል። ሀገራዊ ሠላምና መረጋጋት ማምጣት ተስኗት በቆየችበት ጊዜ ተጨማሪ የጎረቤትና ዓለም አቀፋዊ ቀውሶች አጋጥመዋታል፡፡

ስለሆነም ችግሮቿን መቅረፍ አሁንም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጥረት ይጠይቃል ምክንያቱም የችግሩ የአጭር ጊዜ አባባሽ ሁኔታ በሱዳን ያለው ጦርነት እንደመሆኑ፡፡ መንግሥት የህብረተሰቡን ህይወት በዘላቂነት ለማሻሻል ከሚያወጧቸው ፖሊሲዎች በተጨማሪ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ድጋፎችም ሊጠናከሩ ይገባል፡፡