የእውቀት ማዕድ

የእውቀት ማዕድ

በአንዱዓለም ሰለሞን

ለስራ ጉዳይ ወደ ዱራሜ ከተማ ባመራሁበት ወቅት ስለታዘብኩት አንድ ነገር ላወጋችሁ አስቤ እነሆ ብዕሬን አነሳሁ። የምሳ ሰዓት ላይ በእግሬ እየተጓዝኩ ሳለ አንድ ነገር ትኩረቴን ሳበው፡፡

በከተማዋ ከሚገኘው የህዝብ ቤተ-መጽሀፍት ቤት ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ተጠቃሚዎች እየወጡ ነበር፡፡ ለአፍታ ባለሁበት ቆሜ ሁኔታውን ስታዘብ ቆየሁና ወደ ቅጥር ጊቢው ዘለቅሁ፡፡ ከዚያም ወደ ቤተ መጽሀፍት ቤቱ ገባሁ፡፡ የቤተ መጽሀፍቱ አስተባባሪ በሩን ዘግተው ሊወጡ ሲል በመድረሴ ብዙም ላቆያቸው እንደማልችል ገብቶኛል።

ብቻ ግን የቤተ መጽሀፍቱን የአገልግሎት አሰጣጥ በተመለከተ ለመቃኘትና አንዳንድ አስተያየቶችን ለመውሰድ ማሰቤን በመንገር ከሰዓት ይመቻቸው እንደሆነ ጠየኳቸው፡፡ ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ በሀሳቤ ተስማሙ፡፡

ከመጽሀፍት ቤቱ ወጥቼ ስሄድ ይህን እያሰብኩ ነበር፤ የልጅነት ትዝታዬን፡፡ እንዲህ ዓይነት ቤተ መጽሀፍት በአንድ ከተማ መኖሩ የሚሰጠው ጠቀሜታ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። በልጅነቴ ትዝ ከሚሉኝ ነገሮች አንዱ በተለይም በክረምት ወቅት ከጓደኞቼ ጋር በህዝብ ቤተ መጽሀፍት የምናሳልፈው ጊዜ ነው።

ተጠርዘው ከተቀመጡ ብዙ ጊዜ የሆናቸውን ጋዜጦች አቧራ እያራገፍን እናነብ፣ ያገኘናቸውን ቁም ነገሮችም በማስታወሻችን እንመዘግብ ነበር፡፡ በቤተ መጽሀፉ ካገኘነው ቁም ነገር ባሻገር ታዲያ በልጅነታችን ለመጽሀፍ በጎ አመለካከት እንዲኖረን አድርጎናል፡፡

ከሰዓት በኋላ ወደ ቤተ መጽሀፍቱ የእውቀት ማዕድ አመራሁ፡፡ ከቦታው ስደርስም ወደ ውስጥ ዘልቄ ከአስተባባሪው ጋር በመሆን ቅኝቴን ጀመርኩ፡፡ የቤተ መጽሀፍት ቤቱ ቅጥር ጊቢ ብዙም ሰፊ ባይባልም ጽዱና ለዐይን ማራኪ ነው፡፡

የቤቱ ብርሀን ለንባብ ተስማሚ ከመሆኑ ባሻገር ስፋቱ በርካታ ተገልጋዮችን ለመያዝ የሚያስችል መሆኑን ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ መቀመጫዎቹም ለተገልጋይ ምቹ ናቸው፡፡ በመጽሀፍት መደርደሪያዎቹ ላይ የተለያዩ መጽሀፍት በአይነት በአይነቱ ተደርድረው ይታያሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር መጽሀፍት ያልተሰደረባቸው ባዶ መደርደሪያዎችንም ተመልክቻለሁ፡፡ እነዚህ ደግሞ በቀጣይ ለሚመጡ መጽሀፍት (በግዢም ሆነ በልገሳ) ተዘጋጅተው የተቀመጡ ናቸው። ለአብነት በቅርቡ ከኢትዮጵያ ቤተ መጽሀፍት ኤጀንሲ አንድ ሺህ መጽሀፍትን በስጦታ ማግኘታቸውን የቤተ መጽሀፍቱ አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ዮሀንስ ነግረውኛል፡፡

ከመጽሀፍቱ ባሻገር ለዲጂታል ላይብራሪ መገልገያ የሚውሉ 40 ኮምፒውተሮች በቤተ መጽሀፍቱ ይገኛሉ። ቤተ መጽሀፍቱ ከ1999 ዓ/ም ጀምሮ ለከተማው ህብረተሰብ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ለአስራ አንድ ዓመታት በአስተባባሪነት ያገለገሉት አቶ ሳሙኤል በርካታ ሰዎችን ተጠቃሚ ስለማድረጉ ምስክር ናቸው፡፡ በርካታ ወጣቶችና ተማሪዎች በቤተ መጽሀፍቱ በመገልገል በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ማምጣት ችለዋል፡፡ በርካታ ሰዎችም እውቀት ለመገብየት መጽሀፍትን ፈልገው መጥተው ከዕውቀት ማዕድ ተቋድሰዋል፡፡

ይህን ማየት ደግሞ ለእሳቸውና አብረዋቸው ለሚሰሩ ሰራተኞች የሚያስደስታቸው ነገር ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም ቤተ መጽሀፍቱ ከዚህ በተሻለ ትኩረት ቢሰጠው፣ እነሱም የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ስልጠና ቢያገኙ (በተለይም ደግሞ ዲጂታል ላይብራሪ አጠቃቀምን በተመለከተ) ጥሩ መሆኑን ሀሳባቸውን አጋርተውኛል፡፡ ይህንን የአስተባባሪውን አስተያየት እያደመጥኩ የማደርገውን ቅኝት ቀጥያለሁ፡፡ ቤተ መጽሀፍቱ በመጽሀፍት ረገድ በብዛት፣ በዓይነትና በስብጥር ረገድ ጥሩ የሚባል ይዘት እንዳለው አይቻለሁ። ለመጽሀፍቱ የሚደረገውም ጥንቃቄ እንዲሁ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

ብዙ ያገለገሉ መጽሀፍት በአግባቡ ተጠግነው መልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለዚህ በተዘጋጀ ክፍል ውስጥ እድሳቱ በጥንቃቄ ይከወናል፡፡ ከራሴ ምልከታ ባሻገርም የተወሰኑ ተገልጋዮችን ለማነጋገር ሞክሬያለሁ፡፡ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነና ከስምንተኛ ክፍል ጀምሮ በቤተ መጽሀፍቱ መገልገል እንደጀመረ የነገረኝ ወጣት እንደገለጸልኝ ገበያ ላይ የሚውሉ አዳዲስ መጽሀፍትን ገዝቶ ከማቅረብ ረገድ ትኩረት ቢሰጠው መልካም ነው የሚለውን ሀሳቡን አጋርቶኛል፡፡ ከመጽሀፍቱና ካነሳኋቸው ሌሎች ጉዳዮች ባሻገር የታዘብኩት ነገር ቢኖር ቤተ መጽሀፍቱ ያለበት አካባቢ ለድምጽ ብክለት የተጋለጠ መሆኑን ነው፡፡

የቤተ መጽሀፍቱን አገልግሎት አሰጣጥ በተመለከተ አስተያየቷን እንድትሰጠኝ የጠየኳት የዱራሜ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ “የጸጥታ ችግር አለ” ስትል ገልጻልኛለች፤ ከውጪ የሚሰሙ፣ በተለይም ደግሞ ድምጻቸው ከፍ ብሎ የሚለቀቁ ሙዚቃዎች (መንፈሳዊ መዝሙሮች) ውስጥ ድረስ እንደሚሰሙ በመጠቆም፡፡ ለአንድ ሀገር እድገት የተማረ የሰው ሀይል የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ከትምህርት ባሻገር እውቀቱን በንባብ የገነባ ትውልድ ነገሮችን በጥልቀት ለመመርመር፣ ምክንያታዊና ሚዛናዊ ሆኖ መመልከት ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የህዝብ መጽሀፍት ቤቶች ሚና ቀላል ግምት የሚሰጠው አይሆንም። አሁን ያለንበት ዘመን በተለይም ደግሞ ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ (ሶሻል ሚዲያን ከመጠቀም) ንባብ ባህል ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለማምጣቱ ከብዙዎች የሚነሳ ሀሳብ ነው፡፡

አንዳንዶች ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው በሀገራችን ጨርሶ የንባብ ባህል እንደሌለ አድርገው የሚናገሩም አልታጡም፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ ገዢ ሀሳብ ሊሆን አይችልም፡፡ ለምን ቢሉ ኢትዮጵያ የራሷ የፊደል ገበታ ያላትና ይህም በዓለም ላይ ካሉ ጥቂት ሀገራት አንዷ መሆኗን ልብ ይሏል፡፡ ብዙዎች ዐይናቸውን የጣሉባቸው፣ እኛ ግን ገና አሁንም ያልመረመርናቸው በርካታ የብራና መጽሀፍት መኖራቸውን ላስተዋለ ይህ ዓይነቱ ምልከታ ውሀ የማይቋጥር መሆኑን ለመረዳት አያዳግተውም፡፡ በዚህ ረገድ ቤተ መጽሀፍቱ የሚሰጠውን አገልግሎት የተሟላ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ቢያበረክቱ መልካም ነው እላለሁ፡፡