“ችግርን ፈርተህ የምትሸሸው ከሆነ ወደ ኋላ ይጎትትሃል”

“ችግርን ፈርተህ የምትሸሸው ከሆነ ወደ ኋላ ይጎትትሃል”

በደረሰ አስፋው

“እንዴት እችላለሁ? እያሉ ራስን ደካማ ማድረግ ተገቢ አይደለም። ወደ ትልቁ የህይወት ግባችን ለመድረስ የምናደርገውን ጥረት፣ ትኩረት እና ቁርጠኝነት ይቀንሱታል ወይም ያጠፉታል።

ከዚያ ይልቅ በትልቁ የሕይወት ግብ፣ ስኬታማ ለመሆን በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይበጃል። ከፊታችን ያለው መንገድ ፈታኝ ቢሆንም በሕይወታችን ወሳኝ የሆነውን ውሳኔ መወሰን ግድ ነው፡፡ አይቻልም በተባሉ ቦታዎች አቀበት ቁልቁለቱን እወርድ ነበር፡፡

ይህን ሁሉ ተግዳሮት ማለፍ ባልችል ዛሬ እረኛ ነበርኩ። ፈተናዎችን ማለፍ ካልተቻለ ችግር ውስጥ ይኖራል” ሲል ነው የሀሳቡ ጅማሬ ያደረገው። ወጣት ጥላሁን ሻወል ይባላል፡፡

በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ሶሎቄ ቀበሌ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ በአካባቢው ከአራተኛ ክፍል በኋላ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ወደ ቡኢ ከተማ ሄዶ ነው ትምህርቱን የተከታተለው፡፡ ለአካል ጉዳተኛው ጥላሁን ከወላጆቹ ተለይቶ፣ ቤት ተከራይቶና ምግቡን እያዘጋጀ በመማር ፈታኙን ህይወት ይጋፈጥ ጀመረ፡፡ የአካል ጉዳቱ ያጋጠመው በስምንት ወሩ አክስቱ አዝለውት በመውደቃቸው በእግሩ ላይ በደረሰበት ስብራት ምክንያት ነው፡፡ ጉዳቱ በውል ሳይታወቅ ለረጅም ጊዜ በመቆየቱም ችግሩ ስር ሰደደ፡፡ በእግሩ መንቀሳቀስ እንደጀመረ የታወቀው ጉዳቱ ወደ ወጌሻ ቢወስዱትም ከችግሩ ግን መፈወስ አልቻለም፡፡

ወደ ህክምና ተቋም ከመውስድ ይልቅ ልክፍት እየተባለም ለችግሩ መባባስ ምክንያት ሆነ፡፡ “ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል በተወለደበት የገጠር ቀበሌ የተማረው የብረት ድጋፍ ተገጥሞለት ነው፡፡ የአንድ ሰዓት ተኩል መንገድ እየተጓዘ ስለመማሩም ያስታውሳል። “ጧት ላይ ለቁርስ አንባሻና ጎመን ይዤ እወጣለሁ። አንባሻውን ለሁለት ከፍዬ እንደሳንድዊች አድርጌ እይዘዋለሁ፡፡ ከረጅም ጉዞ በኋላ ጸሃይ ሲወጣ ያዘጋጀሁትን ቁርስ እበላለሁ፡፡ ከጧቱ 11 ሰዓት ተነስቼ 2 ሰዓት እደርስ ነበር፡፡ ከሰዓት 7 ሰዓት ብነሳ 10 ሰዓት ነበር የምደርሰው” ሲል ያለፈበትን የሕይወት ውጣ ውረድ ያወሳል፡፡ ጥላሁን ለችግሩ እልባት ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ቼሻይር የአካል ጉዳተኞች ድጋፍ ማዕከል በመሄድ ጥረት አድርጓል፡፡ ከጊዜ በኋላ በተደረገለት የቀዶ ጥገና ህክምና ተጎድቶ የነበረው እግሩ እንዲቃና በመደረጉ በዱላ በመንቀሳቀስ ይደርስበት የነበረውን እንግልት ታደገለት፡፡

ቤተሰቡ አድጎ እንዲያገለግላቸው እንጂ ተምሮ ለቁም ነገር እንዲደርስ አይፈልጉም ነበር፡፡ አካል ጉዳተኛ ሲሆን ደግሞ ከመንደር ወጥቶ ተምሮ ለቁም ነገር ይደርሳል የሚለው አስተሳሰብ የማይታሰብ በመሆኑ የጥላሁንን ችግር አወሳስቦት እንደነበረ ያስታውሳል። ቼሻየር እንዲማር ወላጅን በአስገዳጅነት ማሰፈረሙ ዛሬ ለደረሰበት ውጤት ባለውለታው እንደሆነም አልዘነጋውም። ከቤተሰብ ተጽዕኖ ወጥቶ በነጻነት ለመማር የሚያስችለውን እድል አገኘ፡፡ የመጀመሪያው ፈተና የጀመረው ከቤተሰቡ ነው፡፡ እንዴት እንጨት ለቅሞ ጋግሮ ይበላል በሚል ወደኋላ ሊያስቀሩት አስበው ነበር፡፡

ችግርን የማሸነፍ ብቸኛው አማራጭ መማር ነው አለ፡፡ “ችግርን ፈርተህ የምትሸሸው ከሆነ ወደ ኋላ ይጎትትሃል” ሲልም ነው የተናገረው። ቤተሰብ ወራሽ ሆኖ እንዲቀመጥ እንጂ ተምሮ እንዲለወጥ አይፈልጉም፡፡ እናትም አግብቶና ወልዶ የቡና አጣጭ እንዲሆን እንጂ ተምሮ እራሱን እንዲለውጥ አይመኙም፡፡ ተምሮ ለቁም ነገር ይደርስ ይሆን የሚለውን የማህበረሰቡም ጥርጣሬ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ተደራራቢ ተጽእኖ ተጋፈጦ በማሸነፉ ዛሬ ላይ ደስተኛ እንደሆነ ነው የሚገልጸው፡፡ ተደራራቢ የሆነው የህይወቱ ፈተና በፈጠረበት የአእምሮ ህመም 7ኛ ክፍል ላይ ትምህርቱን አቋርጦ እንደነበር ያነሳል።

ይህ ጊዜ ከቁጭት ይልቅ እራሱን ለማየት እድል ፈጠረለት፡፡ መፅሃፍትን በማንበብ እና ዘና ሊያደርጉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እራሱ ለራሱ ሀኪም የሆነበትን ጊዜም አልዘነጋውም፡፡ ከህክምናው በተጓዳኝ የደረሰበትን የስነ ልቦና ችግር በራሱ ጥረት መላ አበጅቶለት ከህመሙም ተፈውሶ መማሩን ቀጠለ፡፡ በ12ኛ ክፍል የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናን ከ350 በላይ ውጤት በማምጣት ደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ገባ፡፡ መማር የሚፈልገው የጋዜጠኝነት ትምህርት ቢሆንም አልተሳካለትም፡፡ ምኞቱን እውን ለማድረግ ጎንደር፣ ባህርዳር እና መቀሌ ዩኒቨርስቲዎች ቢሞከርም አልሆነም፡፡ በሶሾሎጂ ትምህርት ክፍል ለ3 ዓመት የሚሰጠውን ትምህርት ተከታትሎ 3 ነጥብ 3 አምጥቶ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቀ፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታው የሚፈትኑት ችግሮች አለቀቁትም፡፡ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግለት አካል አለመኖሩ አንዱ ነው። ትምህርት የለውጥ መሰረት ነው የሚለው አካል ጉዳተኛ ወጣት ጥላሁን ከዩኒቨርሰቲ ትምህርቱ ጎን ለጎን መማር የሚፈልጋቸው ትምህርቶች ቢኖሩም በገንዘብ እጦት መስተጓጎላቸውን ነው የገለጸው፡፡

በዩኒቨርስቲው በነበረው ቆይታ ጾታዊ ፍላጎቶችም ሌላው ፈተናዎቹ ነበሩ፡፡ በ3ኛ አመት ላይ የገጠመውን ጾታዊ ፍቅር በማስታወስ፡፡ 12ኛ ክፍል እያለ አንድ ጓደኛው የአካል ጉዳተኛ በመሆኑ ለፍቅር የመረጣትን እንስት ጠይቆ የተሰጠው ምላሽ ጥላሁንን ይረብሸዋል፡፡ እሱም ቢጠይቅ ተመሳሳይ ምላሽ አገኛለሁ በሚል በትምህርቱ ላይ ተጽእኖ ፈጥሮበት ነበር፡፡ የመመረቂያ ጽሁፍ በሚያዘጋጅበት ጊዜ በመሆኑ ፈተናው የከፋ እንደነበር ያስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጥላሁን ለህመሙ መድሃኒት ማበጀቱ አልቀረም፡፡ ወደ መምህራን ቀርቦ ማወያየት ግድ አለው፡፡ መምህራንም ምላሹ ምንም ይሁን ምን ጠይቅ አሉት፡፡ በምላሹ ምንም ነገር እንዳይሰማው ሙያዊ ምክራቸውን ለገሱት፡፡

በዚህም መጠየቁ አልቀረም በምላሹ ግን ወደራሱ ተመለሰና ህይወቱን ቀና አደረገ፡፡ በዩኒቨርስቲ በርካታ የህይወት ክህሎቶችን መቅሰሙን የሚናገረው ጥላሁን አካል ጉዳተኞች እንደ አካል ጉዳታቸው የራሳቸው ህብረት ነበራቸው፡፡ በጉዳዮቻቸው ላይ ይወያያሉ፡፡ ይህም አቅማቸውንና አስተሳሰባቸውን እንዲያጎለብቱ እንዳገዛቸው ይናገራል፡፡ የዩኒቨርስቲ መመረቂያ ጽሁፉን በራሱ ላይ መስራቱን የገለጸው ጥላሁን “የአካል ጉዳተኞች አገልግሎት በደብረ ብርሃን ከተማ” በሚል፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ለውጥ በቀላሉ አልመጣም ያለ ሲሆን ከራሱም ጋር መነጋገር ለህይወት ለውጥ ሁነኛ መላ እንደሆነለትም ተናግሯል። “አሁን በርካታ ጊዜዬን የማጠፋው ከአካል ጉዳተኞች ጋር በመወያየት አለያም አካል ጉዳተኞችን የሚመለከቱ መጽሃፍትን በማንበብ እና ፊልሞችን በመመልከት ነው፡፡ ይህም ጠቃሚ የህይወት ክህሎት አስጨብጦኛል” ነው ያለው፡፡ ጥላሁን አሁን ላይ በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ፋይናንስ ጽ/ቤት ተቀጥሯል፡፡ ስራ ላይ አምስት አመታትን አስቆጥሯል።

በስራ ተቀጣሪ በመሆኑ በገንዘብ ለውጥ አምጥቸበታለሁ ባይልም ከሱ በታች በገጠር፣ በከተማ፣ በትምህርት ቤቶችና በዩኒቨርስቲዎች ያሉ በርካታ አካል ጉዳተኞች እንዲለውጡ ምክንያት መሆኑን ነው የተናገረው። “እራሴም ብሆን እንደምችል አሳይቻለሁ” ሲልም ተናግሯል፡፡ “የመንግስት መስሪያ ቤት መቀጠሬ እንደምችል አሳይቻለሁ፡፡ ሙሉ አካል ያለው የሚያደርገውን እኔም እችላለሁ ብዬ ውስጤን አሳምኛለሁ፡፡ የመስክ ስራ እሰራለሁ። ሞተርም ማሽከርከር ጀምሬያለሁ። እንዲያውም በቅርቡ የመኪና መንጃ ፈቃድ ለማውጣት አቅጃለሁ” ብሏል፡፡ ወጣቱ አካል ጉዳተኛ ጥላሁን መጽሃፍ ለማሳተም እየተንደረደረ እንደሆነም ነው ያወጋኝ፡፡ የሚያዘጋጀው መጽሃፍም አካል ጉዳተኞችን የተመለከተ ነው፡፡ “እኔ የምኖረውን ጽፌ ለሌሎች ከማስተማር የሚበልጥ ነገር የለም” ሲልም ነው የተናገረው። የመጽሃፉ ዝግጅት 70 በመቶ መድረሱን የጠቆመው ባለታሪካችን ወደፊት ፋውንዴሽን ለማቋቋምም ዕቅድ አለው፡፡

አብዛኛዎቹ አካል ጉዳተኞች ከግንዛቤና ከባህል ተጽእኖ በቤት ውስጥ ታፍነው እንዳሉ ያነሳል፡፡ ችግሩ የማህበረሰቡ ብቻ ሳይሆን የራሱ የአካል ጉዳተኞችም እንደሆነ በመጠቆም፡፡ ለዚህም የሚቋቋመው ፋውንዴሽን አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ በማድረግ ከችግር የሚታደግ እንደሆነም ጠቁሟል፡፡ ኤጀንቶችን ጭምር በማቋቋም አካል ጉዳተኞች ባሉበት አካባቢ አቅም እንዲፈጥሩ የሚቋቁመው ፋውንዴሽን ዋና ዓላማው እንደሆነም ተናግሯል፡፡ “ለፋውንዴሽኑ መቋቋም የራስ ተነሳሽነት ይቀድማል ሌላው ይከተልሃል” ያለ ሲሆን ፋውንዴሽኑ ቢቋቋም የወረዳው ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ጨምሮ ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ሊያደርጉለት እንደሚችሉም ተስፋ አድርጓል። “የተደረገልህን ነገር አጉልተህ የምታሳይ ከሆነ ድጋፍ የሚያደርግልህ አካል ይነሳሳል” ነው ያለው፡፡ የሚለምን አካል ጉዳተኛን ይቃወማል።

“ሰው ፊት ቆመህ መለመንን የመሰለ አስከፊ ነገር ካወክ መስራት ያቅተዋል ብለህ ታስባለህ? ሲል ይጠይቃል፡፡ ይህንን የሚቋቋም ማንነት ያለው ሰው ሰርቶ መለወጥ የመሰለውንም ቀላል ነገር ይቋቋማል፡፡ ሁሉም ሰው ይህን ይቀበላል ለማለት ሊከብድ ቢችልም አካል ጉዳተኞች ግን ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉም መቀበል አለባቸው። እራሳቸውን ለልመና የሚያዘጋጁ አካላት የማይሰጥ አካል ባይኖር ምን ሊሆኑ ነው?” ሲልም መልሶ ሀሳቡን በጥያቄ ቋጭቷል፡፡

የሀይማኖት ተቋማት፣ ምጽዋት ሰጪ ግለሰቦችም ሆነ የእምነቱ መሪዎች ምጽዋት ከመስጠት ይልቅ መስራት እንደሚችሉ ማስተማር እንደሚገባም ሀሳቡን ሰጥቷል፡፡ እራሳቸውን የሚችሉበትን ማስተማር እንጂ ከንፈር እየመጠጡ ምጽዋት መስጠት ዘላቂ መፍትሄን እንደማያመጣ በማሳሰብ “ሰጪው ያለቀበት እለት ለማኙ ምን ሊሆን ነው?” ሲልም መልዕክቱን በማስተላለፍ ሃሳቡን ቋጭቷል፡፡