የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ፋይዳ

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ፋይዳ

በደረጀ ጥላሁን

እንደ ሃገር ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል በግብርና ሥራ የሚተዳደር በመሆኑ በዘርፉ የሚመረቱ ምርቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ያስችል ዘንድ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መቋቋሙን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከዚህ አኳያ በግብርናው ዘርፍ የሚመረተውን ምርት እሴት በመጨመር ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር የሥራ እድል መፍጠር፣ ወደ ውጪ ገበያ በማቅረብ ምንዛሪ ማግኘት እንዲሁም ከውጪ የሚገባውን ምርት መተካት እንዲቻል ታሳቢ ተደርጓል፡፡

ፓርኮቹ ሀገሪቱ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት ለመጨመር የምታደርገውን ጥረት የሚደግፉ ናቸው፡፡ ለዚህም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የማምረቻ አካባቢዎች፣ ዘመናዊ የግብርና ማሳዎች፣ የዕውቀትና የምርምር ማዕከሎች፣ የግብርና መሠረተ ልማቶች፣ የምርት ማሰባሰቢያ ጣቢያዎች፣ እና የግብርና ምርቶች ሽያጭ መሠረተ ልማቶች ይኖራቸዋል፡፡

ከዚህ ሌላ መጋዘኖች፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የማበጠሪያ፣ ደረጃ ማውጫ፣ የኤክስቴሽን አገልግሎት፣ የቅድመ-ማቀነባበር ሥራዎች እና የአነስተኛ ብድር አገልግሎቶች እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡

የደቡብ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ናትናኤል ሚሊዮን ይህን አላማ ለማሳካት የደቡብ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በምክር ቤት ደንብ ቁጥር 147/2008 መቋቋሙን እና ሲሆን ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ በርካታ ሥራዎች ማከናወኑን ይጠቅሳሉ፡ ፡ በዚህም በፓይለት ደረጃ ይለሙ ከነበሩ አራት ፓርኮች አንዱ የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ሲሆን በውስጡ ስድስት የገጠር ሽግግር ማእከላት አሉት፡፡

ይሁን እንጂ በክልል አደረጃጀት ምክንያት ፓርኩና ሁለት የገጠር ሽግግር ማእከላት ወደ ሲዳማ ሲገቡ ሌሎቹ ማእከላት በጌዴኦ ዞን በዲላ፣ ይርጋጨፌ እና ቡሌ ላይ ይገኛሉ፡፡ የዲላ ገጠር ሽግግር ማእከል ቀድሞ ከነበረበት አደረጃጀት አንፃር አስተዳደሩ የተለያየ በመሆኑ በጥናት ተለይተው የነበሩ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የገጠር ሽግግር ማእከላት የግብርና ግብአቶችን በመሰብሰብ ደረጃ ይሰጣቸዋል የሚሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፡፡ ለምሳሌ ቡናን ከአርሶ አደሩ በመሰብሰብ ደረጃ እንዲወጣለት አድርጎ ለኤክስፖርት፣ ለኢንዱስትሪ ፓርክና እንዲሁም የማቀነባበር እና ከፊል የማቀነባበር ሥራዎች ይሰሩበታል።

ከዚህ አኳያ የዲላው የገጠር ሽግግር ማእከል ሥራ ተጠናቆ የባለሀብቶች ምልመላ ተደርጓል፡፡ ለዚህም 14 የሚሆኑ ባለሀብቶች ለመስራት ፈቃደኛ ሆነው መቅረባቸውንና፡፡ ከነዚህም ስድስቱ የውል ስምምነት የፈጸሙ ሲሆን ህጋዊ ሆነው ሥራ ለመጀመር የማሽን ግዢ ሂደት ላይ ያሉ ናቸው ብለዋል፡፡ ከነዚህ አንዱ ደግሞ የማሽን ተከላው የሙከራ ምርት ማምረት ጀምሯል፡፡ ሌሎችም በሚቀጥሉት ወራት ወደ ስራ እንደሚገቡ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንደነገሩን ከሆነ በአቮካዶ ዘይት ፋብሪካ ምርት ወቅት የሚወጣውን ተረፈ ምርት የማዘጋጃና መቀበያ ሥፍራ የተዘጋጀ ሲሆን ይህም ከብቶችን ለማደልብ የሚረዳ ነው፡፡ የአንዱ ተረፈ ምርት ለሌላው ግብአት እንዲሆን እንደሚደረግና ከዚህ የሚያልፈው ደግሞ በግቢው እና በአቅራቢያው በሚገኙ የእርሻ ማሳዎች ላይ በማዳበሪያነት መጠቀም ይቻላል ብለዋል፡፡

በክልሉ ሌላው የሚሰራው በአነስተኛና መካከለኛ ማንፋክቸሪንግ ልማት ላይ ነው፡፡ በ17 ከተሞች ባሉ 31 ሳይቶች ላይ የአነስተኛና መካከለኛ ማንፋክቸሪንግ ሼዶች በማዘጋጀት ትላልቅ ኩባኒያዎች እየሰሩ ነው የሚሉት አቶ ናትናኤል፡፡ አሁን ላይ በክልሉ ተሰርቶ የማያውቁ ምርቶች በተለያዩ ኩባኒያዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ የሚስማር፣ ፈሳሽና ደረቅ ሳሙና ከነዚህ ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

እንዲሁም ወልቂጤ ላይ ከውጪ የሚገቡትን የሚተኩ የእርሻ መሳሪያዎች እየተመረቱ መሆኑን ጠቁመው የትራክተር ማረሻ፣ የጤፍ መውቂያ፣ የእንሰት መቁረጫ ማሽኖችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ የሲሚንቶ ማቡኪያ /ሚክሰር/ እንዲሁም የወረቀት፣ ሶፍት እና ፕላስቲክ ማምረቻ ፋብሪካዎችም አሉ፡፡ የፕላስቲክ ጥሬ እቃ ከውጪ በማስመጣትና መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል የሚመረት ሲሆን በዚህም በርካታ የሥራ እድል እየተፈጠረ ይገኛል ብለዋል፡፡

በማኒፋክቸሪንግ ዘርፉ በሚሰራው ስራ የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት፡፡ ለማሳያነትም የአቡካዶ ዘይት ማምረቻ ኩባኒያ በቀን ከ5 እስከ 7 ቶን /70 ሺህ ኪሎ ግራም/ ምርት እንደሚፈልግ ጠቅሰዋል፡፡ ይህን ለመሰብሰብ በርካታ አምራች የሰው ሀይል ያስፈልጋል፡፡ በሙሉ አቅም ሲሰራ በቀን 72 ቶን በማምረት 4 ሺህ 300ሊትር ዘይት ያስገኛል፡፡ ይህም በርካታ አርሶ አደሮችን ከፋብሪካው ጋር ማስተሳሰር ያስችላል ማለት ነው፡፡ በቡናም እንዲሁ በርካታ ሰዎችን ማሳተፍ እንደሚቻል ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የገለጹት፡፡

ቀደም ሲል አርሶ አደሮች ከፍራፍሬ የሚያገኙት ጥቅም አነስተኛ ሲሆን ደላላው ግን ይበልጥ ተጠቃሚ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን አርሶ አደሩ እራሱ አምርቶ ለቅሞና አቅርቦ በመሸጡ ተጠቃሚ ሆኗል ይላሉ። ከይርጋለም ቀጥሎ ዲላ ዘይቱ መመረት የጀመረ ሲሆን በቀጣይም አምራቾች እየበዙ ሲመጡ ተጠቃሚነቱ እየጨመረ ስለሚሄድ የሥራ እድል ፈጠራውም የዚያኑ ያህል እንደሚጨምር አብራርተዋል፡፡

በይርጋለም የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ሳንቫዶ የአቡካዶ ዘይት አምራች ድርጅት የፕሮዳክሽን እና ቴክኒካል ሥራ አስኪያጅ ወ/ሪት አበዛሽ አስናቀ እንደገለጹት ድርጅቱ የሚያመርተውን የአቮካዶ ዘይት በራሱ ምልክት ወደ ውጪ በመላክ ገቢ እያስገኘ ይገኛል ብለዋል፡፡ በድፍድፍ መልክ የሚላከውን ዘይት በቀጣይ እዚሁ ተጣርቶ ለፈላጊ ሀገራት የሚቀርብበት ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሚገኝና ይህ ሲሆን ደግሞ ገቢው እንደሚጨምር አመላክተዋል፡፡

ወ/ሪት አበዛሽ እንደሚሉት ሀገራችን በተለይ በግብርናው ዘርፍ ያልተሰራ ሥራ ያለ ሲሆን ባለሀብቶች በሌሎች ከግብርና ጋር ተያያዥነት ባላቸው ሥራዎች ቢሰሩ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ በይርጋለም አካባቢ እንኳ አናናስ፣ አፕልና ሌሎች ፍራፍሬዎች የሚገኙበት አካባቢ በመሆኑ መጠቀም ይቻላል፡፡ ስራው ገና ያልተነካና ጅምር በመሆኑ ባለሀብቶች በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ቡና እና ሌሎችም ላይ እሴት በመጨመርና በማቀነባበር ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2019 ሥራ የጀመረው የሳንቫዶ የአቮካዶ ዘይት አምራች ድርጅት 105 ቋሚና ከ150 በላይ ጊዚያዊ ሰራተኞች እንዳሉት የገለጹት ሥራ አስኪያጇ ኢትዮጵያ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር በምታደርገው እንቅስቃሴ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡