የእሥራኤልና ሳውዲ ዓረቢያ መስቀለኛ መንገድ

የእሥራኤልና ሳውዲ ዓረቢያ መስቀለኛ መንገድ

በፈረኦን ደበበ

አንድ ተስፋ ካልታየ በቀር የነበረው ጨለማ አይታወስም እንዲሉ የሰሞኑ መግለጫ ዓለም ትኩረቱን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲያዞር አድርጎታል፡፡ የእሥራኤል ፕሬዝዳንት ለአሜሪካ ህግ መምሪያ ም/ቤት አባላት ያደረጉት ገለጻ በዓለም ህዝብ አዕምሮ ከፍተኛ ተስፋ ጭሯል፡፡ ከሌሎች ዓረብ ሀገራት ጋር የተፈጠረው ወዳጅነት ከሳውዲ ዓረቢያ ጋርም ይጀመራል የሚል ተስፋ አሳድሯል፡፡

በቀጠናው ለዘመናት የነገሰውን ቀውስ፣ መፈናቀልና ግድያ በማስቀረት ሠላምን ያመጣ ይሆን የሚል ጥርጣሬም አሳድሯል፡፡ በሌላ በኩል በእሥራኤልና ፍልስጤሞች መካከል ያለው ግጭት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተካሮ የሚገኝበት ነው፤ አሁን የምንገኝበት ወቅት፡፡ አንዴ በኃይማኖት ልዩነት፣ ሌላ ጊዜ በእሥራኤል ሠፈራ ፕሮግራሞች ከዚያ አለፍ ሲልም በአካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ቀውሶች ምክንያት እየተፋፋመ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ሰሞኑን የተሰማው ወሬ ግን ኃያላን መንግሥታት ለራሳቸው የሚያስቡትን ያህል ትኩረት ተነፍገው ለቆዩ ህዝቦችም የተስፋ ብርሃን የፈነጠቁበትን አጋጣሚ ይዞ ብቅ እንዲል አድርጓል፡፡

ወደ ቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በሳምንታት ጊዜ ልዩነት እየላከች ወዳጅነትን ስትጠይቅ የቆየችው አሜሪካ በእሥራኤልና ሳውዲ ዓረቢያ መካከል ነግሶ የሰነበተውን ውጥረት አሸማግላለሁ ማለቷ ዕድልን ይዞ የመጣ አስመስሏል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1948 እሥራኤል ሀገራዊ ምሥረታዋን ካካሄደች ወዲህ ተቋርጦ የማያውቀውና ነገር ግን፤ አንድም ጊዜ ዘላቂ ሠላም ማምጣት ያልቻለው የአሜሪካ ሽምግልና ውጤታማ መሆኑ ቢያጠራጥርም አሁን እየተፈጠረ ካለው “የብሪክስ” ሀገራት ጥንካሬ አንጻር አሜሪካንን እንቅልፍ የሚነሳ ሁኔታ ተፈጥሯል ለማለት እንችላለን፡፡ የምትይዝ የምትጨብጠውን ያጣች የምትመስለው ሀገር በዓለም ዙሪያ ከወጠነቻቸው ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ወታደራዊ ዓላማዎቿ መካከል እሥራኤልና ሳውዲ ዓረቢያን ለማሸማገል ማሰቧ ለሁለቱ ሀገራት ብቻ ሳይሆን አሜሪካ እራሷም ለችግር ጊዜ መሸሸጊያ እንዲሆናት ያስችላታል፡፡

የዓለም ሀገራት በጎራ መከፋፈሉ ዕውን ወደ መሆን በተቃረበበት በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ በራሷ እግር ከመቆም ይልቅ በሌሎች ላይ መፈናጠጥ የመረጠችበትም ሆኗል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአውሮፓ ሁሉ ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች ምርጫ እያሸነፉ የባይደንን ለዘብተኛ አስተሳሰብ እያሽቀነጠሩ መሆናቸው ነው፡፡ እየተቃረበ ያለው የ2024 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም እንዲሁ፡፡ በሩሲያና ዩከሬን መካከል ያለው ጦርነት፣ የዓለም የገንዘብ ቀውስ እንዲሁም ህብረተሰቡን እያስመረረ ያለው የኑሮ ውድነት ሁሉ አሜሪካ ስታራምድ የነበረውን የባለ[1]ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መርሆ እንዲቃወሙ አነሳስቷቸዋል፡፡

አሜሪካ አሁን የጨዋታ ሜዳ እንድትቀይር ያነሳሳትም ይሄው እንደመሆኑ ትኩረቷን ከሌሎች ይልቅ ጠቃሚና ጠንካራ ወደሆኑ ወዳጆቿ ላይ ብቻ እንድታደርግ አስገድዷታል፡፡ የሰሞንኛ ትኩረት ከሆነችው ቻይና ቀጥሎ ሳውዲ አረቢያ የማድረግ ፍላጎትም አላት፤ ወዳጇ ከሆነችው እሥራኤል ጋር በማጣመር ኢራንን ለመግታት በማሰብ። አፍሪካን እንዲሁ ከወቅታዊ ምርጫዎቿ ያወጣች እስኪመስል፡፡ ሆኖም እሥራኤል በፍልስጤም ላይ እየወሰደች ባለው እርምጃ ጥርስ ነክሳ ያለችው ሳውዲ አረቢያ መቼም ቢሆን ልቧን ለአሜሪካ የምትከፍት አይመስልም፤ እሥራኤልንም ቢሆን አስታጥቃ ለጥቃት የምታነሳሳው አሜሪካ መሆኗ ስለሚታወቅ፡፡

ስለዚህ የሳውዲ ዓረቢያን ልብ መግዛት ማለት ጉም መዝገን መሆኑን የተረዳች አይመስልም፡፡ ባለፈው ዓመት ፕሬዝዳንት ባይደን ላደረጉት ጉብኝት ቀዝቀዝ ያለ አቀባበል አድርጋ በቅርቡ በቻይና አሸማጋይነት ከኢራን ጋር ስምምነት የፈጠረችው ሳውዲ ዓረቢያ በአሜሪካ ላይ ከረር ያለ አቋም እንደያዘች ያሳያል፡፡ ከአሜሪካ ታስገባ በነበረው የጦር መሣሪያ ፈንታ ሰሞኑን የቱርክ ፕሬዝዳንት ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ድሮን ለመግዛት ማሰቧም እንዲሁ፡፡ እነዚህን ነባራዊ ሁኔታዎችን በሚቃረን መልኩ ሰሞኑን የእሥራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ያደረጉት ንግግር ግርምት የሚፈጥር ነው፡፡ እሥራኤል ከሳውዲ አረቢያ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት “ጸሎት እያደረገች ነው” ብለው መናገራቸው ዓለምን አስደንቋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ህጋዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲመሠረት አሜሪካ እያደረገች ያለውን ግፊት ያደነቁት ፕሬዝዳንቱ ይህ ግንኙነትም ለውጥ የሚያመጣ ይሆናል ብለዋል፤ አልጀዚራ እንደዘገበው፡፡ ፓርላማዊ የመንግሥት ሥርዓት በምትከተለው እሥራኤል የይስሙላ ሥልጣን ያላቸው ፕሬዝዳንቱ ስለ እሥራኤልና አሜሪካ ግንኙነት ሲናገሩም በማይናወጥ አቋም ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በሀገራቱ መካከል ሠላማዊ ግንኙነት እንዲመሠረት አሜሪካ እያደረገች ላለው ጥረት “እሥራኤል ታመሰግናለች” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ሳውዲ አረቢያም በአካባቢውና በሙስሊም ሀገራት ታዋቂ ነች ብለዋል፤ ጊዜው እንዲመጣ በመጸለይ ላይ እንገኛለን በማለት፡፡ ውጤቱ በዓለምና በመካከለኛው ምሥራቅ ታሪክ “የባህር ያህል ለውጥ” ሆኖ ይታየኛል በማለትም ተናግረዋል፡፡ እንደ ሄርዞግ አገላለጽ ከሳውዲ አረቢያ ጋር የሚሻሻለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለእሥራኤል እንደ ትልቅ መልክዓ-ምድራዊ ሽልማት እንደሆነ የጠቀሰው የመረጃ ምንጫችን ይህም የጆ ባይደን አስተዳደር በቤንጃሚን ኔታኒያሁ ለሚመራው የቀኝ አክራሪ መንግሥት የሚያመጣው ትሩፋት መሆኑንም ገልጿል፡፡

ባለፈው ወር ሳውዲ ዓረቢያን የጎበኙት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ግን ወዳጅነቱ ያን ያህል በቀላሉ እንደማይሳካ ግልጽ አድርገው ነበር፡፡ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻሻል ለአሜሪካ ተጨባጭ የብሄራዊ ጸጥታ ዋስትና ይሆናል ማለታቸው ተዘግቧል፤ ምንም እንኳ የሚፈጠረው ግንኙነት እንደታሰበው በቀላሉ እንደማይገኝ ባይሸሽጉም፡፡ ይህ ደግሞ ከሌሎች የዓረብ ሀገራት ጋር ከተፈጠረው ወዳጅነት አንጻርም ሲታይ የባይደን አስተዳደርን ዝና የሚያጎድፍ ነው፡፡ እሥራኤል እንደ መንግሥት ከተቋቋመችበት ጊዜ ጀምሮ እውቅና የሰጡት የአረብ ሀገራት ቁጥር እዚህ ግባ ባይባልም በቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጊዜ ግን የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች፣ ባህሬን፣ ሞሮኮ እና የኋላ ኋላ ሱዳንም ወደ ስምምነቱ መግባቷ “አብርሀም አኮርድ” ተብሎ የሚታወቀውን ስምምነት ለመፈረም አስችሏል፡፡ የሳውዲ አረቢያ አቋም ግን አሁንም ባለበት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ሀገሪቱ ለአረብ ሠላም የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደምትደግፍና ይህም በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ስትገልጽ እሥራኤል ከያዘቻቸው የአረብ መሬቶች ለቃ ስትወጣና የፍልስጤሞች ነጻ መንግሥት ሲመሠረት ብቻ ነው ብላለች ፤ አቋሟ ከድሮ ምንም እንዳልተለወጠ ለማሳየት፡፡ የሠላም ጥረቱ በችግር ላይ ላሉ የፍልስጤም ስደተኞች ፍትሀዊ መፍትሄ እንዲሰጥ ሁሉ ሳውዲ ዓረቢያ ስትጠይቅ የፍሊስጤማዊያን መብት ተከራካሪዎች ግን ችግሩን አክረው ማየታቸው ነገሩን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጐታል፡፡ እሥራኤል በኃይል መቆጣጠሯንና የመብት ጥሰት መፈጸሟን በማጉላት፡፡ ተስፋቸውን ወደ ጎን በመተው ሄርዞግም ይህንን ወቀሳ በአጸፋዊ አስተያየት መልሰውታል፡፡

እሥራኤል ከፍልስጤም ጋር ሠላም የምትፈጥርበትን ቀን እየናፈቀች ነው ካሉ በኋላ ነገር ግን፤ በችግሩ ፍልስጤሞችም ተሳታፊ እንዳልሆኑ ተደርጎ መታየት የለበትም ብለዋል፡፡ ፍልስጤሞች በእሥራኤል ላይ የሚፈጽሙት የሽብር ድርጊት ለውጥረቱ አስተዋጽኦ መኖሩንም አስታውቀዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃን በመጥቀስ በዚህ ዓመት ብቻ እስራኤል የገደለቻቸው ፍልስጤሞች ቁጥር 177 እንደሆነ የገለጸው አልጀዚራ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ደግሞ ከዚህ በላይ እንደሆነና 200 ሰዎችን መግደሏን አስታውቋል ከእነዚያ መካከል አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ሽረን አቡ አክሌ እና ታዋቂው ኦማር አሳድን ለአብነት በማንሳት፡፡

ይህ ደግሞ በዓመት 3.8 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ ለእሥራኤል ለምታቀርበው አሜሪካ ብዙም ትርጉም የሰጣት አልሆነም ተብሏል፤ በሁለቱ የሀገሪቱ ም/ቤቶች ጣምራ ድጋፍ እያገኘ ስለቆየ፡፡ ይሁን እንጂ እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስዎች የተባሉ የመብት ተሟጋቾች የእሥራኤል ድርጊት “በወንጀልና በዘር መድሎ ላይ የተመሠረተ” ነው፡፡

የፕሬዝዳንት ሄርዞግ ሀሳብ ከህግ አውጪዎቹ በኩል ከፍተኛ አድናቆት ማግኘቱም ስለ አሜሪካ እና እሥራኤል ግንኙነት ሌላው ማሳያ ነው፡፡ እሥራኤል “ዘረኛ ወይም አፓርታይድ” መንግሥት አይደለችም እያሉም ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፤ ቁጥራቸው ትንሽ ግን በሀገሪቱ አንቱታ ያላቸው ዴሞክራቲክ የም/ቤት አባላት ቢቃወሙትም። በእሥራኤልና ሳውዲ አረቢያ መካከል ያለው ግንኙነት አሁንም ብዙ ሳንካዎች አሉበት፡፡