የገዜ ጎፋ ወረዳና ቡልቂ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ክፍሎች በልማትና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ከህዝብ ተወካዮችና ከክልል ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያዩ

የገዜ ጎፋ ወረዳና ቡልቂ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ክፍሎች በልማትና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ከህዝብ ተወካዮችና ከክልል ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያዩ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 24/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን የገዜ ጎፋ ወረዳ እና ቡልቂ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በልማትና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ከህዝብ ተወካዮችና ከክልል ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት አካሂደዋል።

የውይይት መድረኩን በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጂጌ፣ የደቡብ ብልፅግና ፓርቲ የሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይነህ ባህሩ  እና የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌትነት በጋሻዉ በጋራ መርተዋል።

በውይይት መድረኩ በገዜ ጎፋ ወረዳ እና በቡልቂ ከተማ አስተዳደር የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፈቱ መሆናቸው ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ተሳታፊዎች እንደ ችግር ካነሷቸው መካከል የመንገድ፣ የመብራት፣ የትምህርት እና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ውስንነት መኖር፣ የወጣቶች ስራ አጥነት እንዲሁም የኑሮ ወድነት መፍትሔ እንዲበጅለት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌትነት በጋሻው የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ህዝቡ ከመረጠው ተወካይ ጋር በየጊዜው የሚያደርገው ውይይት ፋይዳው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

አስተዳዳሪው አክለውም የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመፍታት የዞኑ አስተዳደር በትኩረት እንደሚሠራ አንስተዋል።

የደቡብ ብልፅግና ፓርቲ የሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይነህ ባህሩ በበኩላቸው፥  የመራጩን ህዝብ ጥያቄና ፍላጎት ደረጃ በደረጃ ለሟሟላት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለመፍታት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጂጌ በበኩላቸው፥ በአከባቢው የሚታየውን የመንገድ ተደራሽነት ችግር ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በልዩ ቅንጅት እንደሚሩ አስታውሰዋል።

በአከባቢው የሚስተዋለውን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግር በአጭር እና በረጅም ጊዜ ዕቅድ ለመፍታትና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ሰለባ ከመሆን በመቆጠብ ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የገዜ ጎፋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ምስክር ምትኩ እና የቡልቂ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታደለ ሰለሞን እንደገለፁት፥ በአከባቢው የሚታየውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመፍታት የአርሶአደሩን ምርታማነት በሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችና አሰራሮች ላይ በማተኮርና አከባቢውን የሌማት ትሩፋት ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች የገዜ ጎፋ ወረዳና የቡልቂ ከተማ አመራሮች፣ ወጣቶች ሴቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን