“ሰዎችን ከሰዎች መለየት የሙያው ስነ- ምግባር አይፈቅድም” – ዶክተር ግላንዴ ጊሎ

“ሰዎችን ከሰዎች መለየት የሙያው ስነ- ምግባር አይፈቅድም” – ዶክተር ግላንዴ ጊሎ

የንጋት እንግዳችን በሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል የጽንስና ማህፀን እስፔሻሊስት ሀኪም እና የተቋሙ ሜዲካል ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ዶክተር ግላንዴ ጊሎ ይባላሉ፡፡ የግል ሕይወታቸው፣ የሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የእናቶች፣ የጨቅላ ህፃናት እና የጽኑ ህሙማን ህክምና ምን ይመስላል በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

በገነት ደጉ

ንጋት፡- እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ ስለሆኑ በጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ዶክተር ግላንዴ፡- እኔም እድሉ ስለተሰጠኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- እራስዎን ያስተዋውቁን?

ዶክተር፡- ዶክተር ግላንዴ ጊሎ እባላለሁ። በጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ ልዩ ስሙ ሜላ ካይሻ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነው ተወልጄ ያደኩት። በ1987 ዓ.ም የቄስ ትምህርት ቤት ነበር ትምህርቴን የጀመርኩት፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ስገባ ቁጥር እና ፊደል ቆጥሬ ነበር ትምህርቴን የጀመርኩት፡፡

ስለሆነም 1ኛ ክፍል ስገባ ትምህርት አልከበደኝም፡፡ በወቅቱ በግማሽ መንፈቀ ዓመት አንድ ክፍል፣ በዓመት ሁለት ክፍል በማለፌ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አራት ዓመት ብቻ ነበር የቆየሁት፡፡

የ8ኛ ክፍል ትምህርቴን ያጠናቀኩት አርባ ምንጭ ከተማ ነው፡፡ በወቅቱም በዞኑ ካሉት ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት ነበር ያመጣሁት፡፡

ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ወንድሜ ጋር በመሄድ አርባ ምንጭ፣ ጫሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተልኩት፡፡ ከዚያ በኋላ የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን ደግሞ ሲቀላ መሰናዶ ትምህርት ቤት በመማር በ1996 ዓ.ም ካሉት ተማሪዎች የተሻለ ውጤት በማምጣት ትምህርቴን አጠናቀቅኩ፡፡

በወቅቱ የተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ክፍል ተማሪ ነበርኩ፡፡ ትምህርቴን ያጠናቀቅኩት ከሁለቱም የትምህርት ክፍሎች ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ነበር። በትምህርቴ ጥሩ የሚባል እና ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ፡፡

ከ1997 ዓ.ም እስከ 2003 ዓ.ም መስከረም ድረስ በጅማ ዩኒቨርሲቲ በህክምናው የትምህርት ዘርፍ ተከታትዬ መስከረም 29/2003 ዓ.ም በጥሩ ውጤት በዶክትሬት ተመረኩኝ፡፡

በዚህም እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ በሳውላ ሆስፒታል በተለያዩ ኃላፊነቶችና በሜዲካል ዳይሬክተርነት ለአራት ዓመት ተኩል ካገለገልኩ በኋላ ለእስፔሻሊቲ ትምህርት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨረሲቲ የፅንስና ማህፀን እስፔሻሊቲ ህክምናን ተቀላቀልኩ፡፡ ትምህርቴንም በጥሩ ሁኔታ ተከታትዬ በ2013 ዓ.ም መግቢያ ላይ ተመረኩኝ፡፡

ከተመረኩኝ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሳውላ ሆስፒታል እያገለገልኩ እገኛለሁ። በአሁኑ ሰዓት በሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር በመሆን የጽንስና ማህፀን እስፔሻሊስት ሆኜ እያገለገልኩ ነው፡፡

ንጋት፡- የሳውላ ሆስፒታል ለውጥ ለማምጣት እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት እንዴት ይገለፃሉ?

ዶክተር፡- ሆስፒታሉ በ2000 ዓ.ም ነበር የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በመሆን የተቋቋመው፡፡ በወቅቱ አንድ ጠቅላላ ሀኪም እና የአስተዳደር ሰራተኞችን ጨምሮ በ12 ሰራተኞች ብቻ ነበር ስራ የጀመረው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ነበር፡፡

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አጠቃላይ ሆስፒታል አድጓል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሆስፒታሉ ይታከማል ተብሎ የሚታሰበው የህዝብ ቁጥር ወደ 1.5 ሚሊየን ይጠጋል። ከለውጥ ስራዎች ጋር ተያይዞ ከመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ወደ አጠቃላይ ሆስፒታል ሲያድግ ሁሉም ነገር ተሟልቶለት አይደለም፡፡

በአብዛኛው የስም ለውጥ ብቻ ነበር የተደረገለት፡፡ አሁን ላይ የህንፃ ግንባታ፣ ክፍሎችን የማስፋፋት ስራዎች ብሎም በፊት ያልነበሩ የስራ ክፍሎችን የማካተትና የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በተለይም በፈውስ ህክምና እና የውስጥ ደዌ ህክምና በተለያዩ ክፍሎች፣ ተኝቶ እና ተመላላሽ ህክምና እና የጽኑ ህሙማን ክፍልን ጨምሮ በርካታ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ በተጨማሪም የቲቢ እና የኤች.አይ.ቪ.ኤድስ ህክምና በተደራጀ አገልግሎት እየተሰጠ ነው። እንዲሁም የቀዶ ህክምና እና የጨቅላ ህፃናት ህክምናም በተሟላ መልኩ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በተለይ ለሴቶች የማህፀን እና የጽንስ ህክምናን ጨምሮ በርካታ የስራ ክፍሎችን በውስጡ ይዟል፡፡

ባለን አቅም እየሰራን ነው፡፡ ሆስፒታሉም ከቀድሞው እጅግ ለውጥ በማምጣት ላይ ይገኛል፡፡ ምናልባት የተጀመሩ ህንፃዎች አልቀው ወደ ስራ ሲገቡ ተጨማሪ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ እንሰጣለን የሚል እምነት አለኝ፡፡

ንጋት፡- የማህፀን በር ካንሰርና ሌሎች በሽታዎችን ቅድመ መከላከል ላይ የተሰሩ ስራዎች ምን ይመስላሉ?

ዶክተር፡- ከካንሰር በሽታ ጋር ተያይዞ በተለይ በኢትዮጵያ የካንሰር በሽታ ህመሙ ከፍ ካለ በኋላ ነው የሚታወቀው፡፡ ብዙ ሰዎች ምልክቱን አያውቁትም፡፡ ሰዎች ምልክቶችን አውቀው ቀድመው መከላከል እንዲቻል የማስተማር ስራዎች ይሰራሉ፡፡ በዚህም በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች በተሻለ መልኩ ግንዛቤ እየተፈጠረላቸው ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር በተለይም የሴቶች የማህፀን በር ካንሰር የመለየት ስራ በሆስፒታሉ ይሰጣል፡፡ ካንሰር የሚመስል ነገር ካለደረጃውን መሰረት ያደረገ ህክምና እዛው ይሰጣል፡፡

ከዚህ ውጪ በቀዶ ህክምና መውጣት የሚችለውን ካንሰር ደረጃው ዝቅ ያለ መሆኑ ይታሰባል፡፡ ስለዚህም በቀዶ ጥገና በማውጣት ለምርመራ ይላካል፡፡ በዚህም የስነ- ደዌ ስፔሻሊስት በተቋሙ አለን፡፡

ከዚህ ሌላ የአልትራ ሳውንድ ምርመራ ይደረጋል፡፡ ወይም የቅድመ መከላከያ ህክምና ቀድመው ከመጡ ይሰጣቸዋል፡፡ በተለይ የማህፀን በር ካንሰር ክትባትም አለው፡፡ ከጡት ካንሰር ጋር ተያይዞ በተለይም ሴቶች ማንኛውም የጡት እባጭ ሲገጥማቸው በእስፔሻሊስት መመርመር አለባቸው፡፡

ህብረተሰቡም እንደ በፊቱ አይደለም። ሴቶች ጡታቸው ላይ የተለየ ነገር ሲያዩ ይመጣሉ፡፡ ከወትሮው የተሻለ ግንዛቤ አላቸው፡፡ እኛም ናሙና በመውሰድ፣ በስነ- ደዌ እስፔሻሊስት እንዲረጋገጥ የማድረግ ስራዎችን በመስራት ደረጃው ከፍ ሳይል እንዲታከሙ ይደረጋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ካንሰር ያልሆኑ በሽታዎችን በማስተማር የምናልፋቸው በርካታ ናቸው። የጡት ካንሰር ጥሩነቱ በጡት ላይ የሚታይ ስለሆነ በግል ምርመራ የመታወቅ ዕድል አለው፡፡ ሴት እህቶቻችን መስተዋት ፊት ቆመው ሁለቱን ጡቶቻቸውን እያነፃፀሩ ከበፊቱ የተለየ ነገር ካጋጠማቸው ወደ ሆስፒታሉ በመምጣት መታከም እንዲችሉ ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ ደረጃው ከፍ ካለ ደግሞ ከፍ ባለ ሆስፒታል ህክምና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡

ንጋት፡- የእናቶችና የጨቅላ ህፃናት ህክምናስ ምን ይመስላል?

ዶክተር፡- በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሲገለጽ የእናቶች የማዋለጃ ሂደት ነው፡፡ ተገልጋዮች ከመጡ ስራችን ማዋለድ ብቻ ነበር፡፡ ምንም ዓይነት ክትትልና ሌሎች አገልግሎቶች ሳይሰጡ የማዋለድ አገልግሎት ነበር የሚሰጠው፡፡ በወቅቱም የስራ ሂደቱ የአዋላጅ ኬዝ ቲም ተብሎ ተጠቅሶ ነበር፡፡

አሁን ላይ ግን የጽንስና ማህፀን ህክምና ዘርፍ ተብሎ ተለይቶ የማህፀን ህክምና ለብቻ ከጽንስ ጋር ተያይዞ ክትትልና ከወሊድ በኋላ ያለውን አገልግሎት በተደራጀ ሁኔታ ይሰጣል፡፡

በተለይ የእናቶችን አገልግሎት በተመለከተ የእርግዝና ክትትል ደካማ ነው። ምክንያቱም ብዙ እናቶች ለወሊድ ሲመጡ ክትትል የላቸውም፡፡ ክትትል ያደረጉበት ማስረጃ ቢኖርም ከደረጃው በታች ነው።

እናቶች ምጥ ከያዛቸው በኋላ ይመጣሉ። በዚህም እንቸገራለን፡፡ ከዚያ ውጪ ከወሊድ ጋር ተያይዞ እንደ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ወሊድ በጣም ጤናማ ነው፡፡ በማህፀን መውለድ የምትችል ሴትና መውለድ የማትችል ሴት እራሱ ያሳያል፡፡ የእኛ ሰው ”ቤቱ ሞክሮ ጤና ኬላ ላይ ሞክሮ” እምቢ ሲል እኛ ጋር ሲመጡ ልጅ ታፍኖና ማህፀናቸው ፈንድቶ የሚመጡበት አጋጣሚዎች በርካቶች ናቸው፡፡

በተለይም ማዳንና መከላከል የሚቻሉ ነገሮች ተበላሽተው ይመጣሉ፡፡ ስለሆነም ጠንካራ ስራ ይፈልጋል፡፡ ሆስፒታል ከሄዱ ኦፕራሲዮን ያደርጋሉ የሚለው የተሳሳተ እሳቤ በህብረተሰቡ ዘንድ በስፋት አለ፡፡ ሚዲያው ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥሩ አማራጭ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር በቀጣይ ጠንከር ያሉ ስራዎችን መስራት ይፈልጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

በሆስፒታሉ ያለ ቀዶ ህክምና የሚገለገሉ በርካታ ጤናማ እናቶች አሉ፡፡ ነገር ግን በምጥ የማትወልድ እናት እያየን እናትም ይሁን ህፃናት መጐዳት ስለሌለባቸው ቀዶ ጥገና አማራጭ ነው፡፡

ብዙውን ጊዜ ለፌስቱላ የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ እንደ ችግር የደም ባንክ ችግር አለ፡፡ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ የክልሉን ጤና ቢሮ በማስፈቀድ የግንባታ ስራው ተጠናቋል፡፡ ክልሉ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ፈጥኖ ወደ ስራ ከመግባት አኳያ ውስንነቶች አሉበት፡፡ በተለይም ከደም ጋር ተያይዞ በርካታ ስራዎችን መስራትን ይጠይቃል፡፡

ከዚህ ባለፈ ከእናቶች ክትትል ጋር ተያይዞ ሁለት ችግሮች ተለይተዋል፡፡ የመጀመሪያው ህዝቡ እራሱ የአመለካከት ክፍተት አለበት። ከዚህም ጋር ተያይዞ የክትትልን ጠቀሜታ ከማሳወቅ አንፃር ይዘናጋል፡፡ ሌላው ከሆስፒታል በታች ያሉ ጤና ጣቢያዎች ላይ ያሉ ባለሙያዎች ታካሚዎችን በፍጥነት ወደ ሚመለከተው የህክምና ተቋም አለማስተላለፍ ብሎም ማዘግየቶች በስፋት ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማለፍ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡

ንጋት፡- ከአቻ ተቋማት ጋር ያለው የልምድ ልውውጥ ምን ይመስላል?

ዶክተር፡- ከአቻ ተቋማት ጋር ያለው የልምድ ልውውጥ በተቋሙ በሁለት መንገድ ይገለፃል፡፡ ይህም ወደ ታች ወርዶ መደገፍና ወደ ሌላ ተቋማት ወጥቶ ልምድ መውሰድ ናቸው፡፡ በተለይ ከአቻ ሆስፒታሎች ጋር በአቅራቢያ ከሚገኙ አርባ ምንጭ እና ቡታጅራ ሆስፒታል ወጥተን እንደግፋለን፤ ከእነርሱም ልምድ እንወስዳለን፡፡ ድጋፍ ከማድረግ አንፃር ደግሞ የላሀ የመጀመሪያ ሆስፒታል፣ የባስኬቶ ሆስፒታል እና የሳውላ ከተማ ጤና ጣቢያ በእኛ ስር ይደገፋሉ፡፡ ንጋት፡- አገልግሎቱን እኩል ለህብረተሰቡ ከማድረስ አንፃር ምን ምን ስራዎችን እየሰራችሁ ነው?

ዶክተር፡- አልፎ አልፎ ችግሮች ይኖሩ ይሆናል፡፡ እኔ እስከገባኝ ድረስ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ባለሙያን ከታካሚ ጋር ለማገናኘት ቀንም ይሁን ማታ ቅዳሜንና እሁድን ጨምሮ ይሰራል፡፡ ከዚህ ውጪ ሰው አይቶ ማከም፣ ሰዓት ማሳለፍ እና ታካሚ እያለ ከስራ ቦታ መጥፋት ከሞላ ጎደል ይሻላል፤ ነገር ግን ችግሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡

በርግጥ ቀጣይ ላይ የሚጠብቁን ስራዎች አሉ፡፡ በአብዛኛው በአንድ መንፈስ የመስራት ዝንባሌዎች የተሻሉ ናቸው፡፡ በጤና ሙያ ሰዎችን ከሰዎች መለየት የሙያው ስነ-ምግባር አይፈቅድም፡፡ ማንም የታመመ ሰው ለእኛ እኩል ነው፡፡ ከዚህም አንፃር የተሻለ ነገር አለ ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ አልፎ አልፎ አንድ ባለሙያ ተረኛን ተክቶ እስኪወጣ ድረስ ያሉ ክፍተቶች ይኖራሉ፡፡

ንጋት፡- ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ መረጃን ከማዘመን አንፃር ምን እየተሰራ ነው?

ዶክተር፡- የአቻ ተቋማት ልምድ የሚጠቅመው ለእንደነዚህ ዓይነት ስራዎች ነው፡፡ በቅርቡ ወደ ወራቤ እና ቡታጅራ ሆስፒታል ለልምድ ልውውጥ በወጣንባቸው አጋጣሚዎች ሎካል ኔት ወርክ የሚጠቀሙትን በማየት ቀምረን ወደ ራሳችን አም ጥተናል፡፡

የሆስፒታሉ ህንፃዎች የተገነቡት ተራርቀው በመሆኑ ለኔት ወርክ ስራ አይመችም፡፡ ይህንንም ችግር ለመፍታት በአዲሱ በጀት እቅድ ተይዟል፡፡ ችግሩም ተለይቷል፡፡ በተለይም አሁን ካለው የወረቀትና የቀለም ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ስራዎችን ወደ ኮምፒዩተር መቀየር አማራጭ የሌለው ነው። ለዚህም ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ በቂ ኮምፒዩተሮች ተገዝተው የሰርቨር ዝርጋታ ስራዎችን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር የምንሰራቸው ስራዎች እያከናወንን እንገኛለን።

ንጋት፡- በተቋሙ እንደ ችግር የሚገለፀው ምንድነው? የወሰዳችኋቸው የመፍትሔ እርምጃዎችስ ምንድናቸው?

ዶክተር፡- ችግሮችን ውጫዊ እና ውስጣዊ አድርጎ ማየቱ ጥሩ ነው፡፡ ውጫዊ ችግሮችን ቀድሞ ማንሳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ለውስጣዊው ችግር መነሻ ስለሆኑ፡፡

ውስጣዊ ችግሮች ብዬ የማነሳቸው ዞናችን ገና አዲስ የተደራጀ ዞን ነው፡፡ ስለሆነም የፋይናንሰ እና የመሰረተ ልማት ችግሮች አሉበት፡፡ በተለይም መንገድ ለጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ትርጉም አለው፡፡ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ቀርበው ከመንግስት ጋር እንዳይሰሩ ከሚያደርጉ ነገሮች ዋነኛው መንገድ ነው፡፡ ውስጣዊ ችግሮችን ስንመለከት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የውሃ እጥረት ይስተዋላል፡፡ የደም ባንኩ ያለበት ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡

የውሃውን ችግር ለመፍታት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሳውላ ካምፓስ የከርሰ ምድር ውሃ እራሱ አስቆፍሮ እየተጠቀመ ነው፡፡ ከዚያም በመጥለፍ ለእጥበትና ለተለያዩ አገልግሎቶች ፓምፕ በማድረግ በቀን ሁለት ጊዜ እየተጠቀምን ነው፡፡

መንግስትም በዋን ዋሽ የወሰደው የመፍትሄ እርምጃ በቅርብ ቀን ወደ ስራ እንደሚገባ ነው የተነገረን፡፡ ችግሩም ይቀረፋል የሚል እምነት አለን፡፡

ሆስፒታሉ እንደ ሆስፒታል በተለይም ከክፍሎች ጥበት ጋር ተያይዞ ህሙማንን በአግባቡ ለማስተናገድ መቸገር ይታያል፡፡

በዚህም የክልሉ መንግስትና የዞኑ መንግስት በቅንጅት በመስራት አሁን ላይ ነው፡፡ የመጨረሻው የማጠናቀቂያ ስራ ብቻ ይቀረዋል፡፡

የመድሀኒት እጥረት ይስተዋላል፡፡ በቅድሚያ ያነሳሁት የመንገድ ችግር ቢቀረፍ እነዚህ ችግሮች ይፈታሉ፡፡

በአካባቢው የባለ ሁለት እግር ሞተር ሳይክል አደጋዎች ይበዛሉ፡፡ በየጊዜው ሪፈር ወደ ወላይታ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ይላካል፡፡ ችግሮች በርካታ ቢሆኑም ለመፍታት ግን ጥረት ተደርጓል፡፡ በቅርብ ቀን ግን ለውጥ ይኖራል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ንጋት፡- የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለዎት?

ዶክተር፡- ምናልባት የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ የፋይናንስ እጥረቶች እንደተጠበቁ ሆነው የሚሰጡ ቀና ምላሾች አሉ፡፡ በዚህም ሰዓት በጽኑ ህሙማን ክፍል ማሽን ላይ ያሉ ሰዎች አሉ፡፡ የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ማግኘት ያለበት ተቋም ነው፡፡ በዚህም በጣም ትኩረት ይፈልጋል፡፡ የግብዓት አቅርቦቱም ወጣ ብለን ለመግዛት የመሰረተ ልማት ችግሮች አሉና ከወትሮው በበለጠ ሆስፒታሉ በገንዘብ ሊደገፍ ይገባል እላለሁ፡፡

ከዚህም ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ የምለው የሚያሳድገውም የሚጠቀመውም ማህበረሰቡ በመሆኑ ህዝቡ ከጎናችን መሆን አለበት የሚል መልዕክት አለኝ፡፡

ንጋት፡- ስለነበረን ቆይታ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

ዶክተር፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡