የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር በልማትና በመልካም አስተዳደር ዙርያ ተወያዩ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር በልማትና በመልካም አስተዳደር ዙርያ ተወያዩ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር በልማትና በመልካም አስተዳደር ዙርያ ተወያይተዋል።

የውይይት መድረኩን የመሩት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስተር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፣ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ በፍትህ ሚኒስቴር የፍትህና ሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘካሪያስ ኢርኮላ እና የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌትነት በጋሻው ናቸው፡፡

የአከባቢው ማህበረሰብ ካነሳቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የሶዶ-ሳውላ መንገድ ግንባታ መቋረጥ፣ በአርባምንጭ ዩኒቨረሲቲ የሳውላ ካምፓስ ደረጃ አለማሻሻል፣ የኑሮ ውድነት እየተባባሰ መምጣት፣ የስራ አጥነት ችግር፣ የመስኖ ፕሮጀክት ታቅዶ አለመከናወን፣ የሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥ በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን ለአብነት የተነሱ ጥያቄዎች ናቸው።

ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌትነት በጋሻው፥ በዞኑ የሚስተዋሉ የመሠረተ-ልማት ችግሮችን ለመፍታት አስተዳደሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ በዚህም አበረታች ውጤት ማምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ጊዜያትም የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ በፍትህ ሚኒስቴር የፍትህና ሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘካሪያስ እርኮላ በበኩላቸው፥ በአከባቢው ከጊዜ ወደ ጊዜ የልማት ሥራዎች እያደጉ መምጣቸውን ገልጸው፥ የሶዶ-ሣውላ መንገድ ከተቋረጠበት በአዲስ ኮንትራት ለማስጀመር ከፍተኛ ጥረት እየተደረ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጂጌ በበኩላቸው፥ ከመራጩ ህብረተሰብ ጋር በየጊዜው የሚደረጉ ውይይቶች የህዝብን ፍላጎት ማዳመጥና በጥያቄቸው መሠረት ምላሽ የመስጠት ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የሶዶ-ዲንኬ-ሣውላ-ሸፊቴ መንገድን በከፍተኛ ክትትል እና ቁጥጥር እየተከታተሉ እንደነበር በመግለፅ BUCG ተቋራጭ ከገጠመው የፋይናንስ ቀውስ ጋር ተያይዞ ውሉ መቋረጡን ገልጸው በአዲስ ተቋራጭ በአዲሱ በጀት ዓመት መስከረም ወር ላይ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በአዲስ መልክ መጀመሩ ተጨማሪ ዕድሎችን የያዘ መሆኑን ተናግረው ቀድሞ ከነበረው ዕቅድ ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚሠሩለት ተናግረው፥ በቀጣይ ህብረተሰቡ ልማቱ እንዲፋጠን ከመንግሥት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ትብብር እንንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በመድረኩ የተለያዩ የፌደራል እና የክልል ምክር ቤት ተወካዮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን