ህገወጥ የንግድ ስርዓትን ለመከላከል በቅንጅት መስራት እንዲሚያስፈልግ ተገለጸ

“በአርባምንጭ ከተማ ሴቻ አስፓልቱን ተከትለህ አልፎ አልፎ ያሉትን ሱቆች ተመልከታቸው፤ በሙሉ ጫማ ቤቶች ናቸው፡፡ እንዴት ሊሆን ይችላል? አንዳንድ እቃዎች ያላቸውን ዋጋ ተመልከት፤ አንድ ዓይነት የንግድ ምልክት፣ የምርት ስምና የተመረተበት አገር ያው ነው። ነገር ግን በአንዳንድ ቦታና መንገድ ላይ የዋጋ ልዩነት አላቸው። ይህን ያየ ገዢ በአነስተኛ ዋጋ ካገኘው ይገዛል። ይህን ያሉን ስሙ እንደይገለጽ የጠየቀው፥ በከተማው በኤሌክትሪክ ዕቃዎች ንግድ የተሰማራው ግለሰብና በአልባሳትና የጫማ ንግድ ስራ ላይ የተሰማራው ማቴ በለጠ ነው። የኮንትሮባንድ ንግድ ህጋዊ ነጋዴን አክሳሪና ለሀገርም ዕድገት ጠንቅ መሆኑን በመጥቀስ።

በጨርቃ ጨርቅ ንግድ ላይ የተሰማራችው ብስራት ዝናሬ በበኩሏ፥ የኮንትሮባንድ ንግድ ህጋዊ ነጋዴዎችን ለኪሳራ እየደረጋቸው መሆኑን ትናገራለች። ህጋዊ ነጋዴ በትክክለኛው መንገድ ታክስ ከፍሎ፣ የንግድ ፈቃድ አውጥቶ፣ ቤት ተከራይቶና ሠራተኛ ቀጥሮ በመሥራት በሚሸጠው ዕቃ ላይ የሚያዋጣውን ዋጋ ይተምናል። ሆኖም ጨርቅ በኮንትሮባንድ በብዛት የሚገባ በመሆኑ የህጋዊ ነጋዴው ዋጋ በጣም ውድ ነው በሚል ፈላጊ ያጣል። ይህንን በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል ብናሳውቅም መፍትሔ ያልተበጀለት ችግር ሆኗል በማለት ብሶቷንና ቅሬታዋን ትናገራለች።

የአርባምንጭ ከተማ ምክትል ከንቲባና የንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ አቶ ምህረቱ ተሰማ፥ የንግድ ስርዓቱን በከፍተኛ ደረጃ እየተፈታተኑ ካሉት ችግሮች አንዱ የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ መሆኑን ይናገራሉ። የገቢ ኮንትሮባንድ፣ ጥይት፣ መሳሪያዎች፣ ልባሽ ጨርቅ፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቶርሺንና ጫማዎች ሲሆኑ፤ ወጪ ኮንትሮባንድ ደግሞ ከብት፣ ፍየሎችና በጎች የመሳሰሉ ከተማውን አቋርጠው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በብዛት የሚወጡበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል። ገቢ ምርቶች በተለይ ከአጎራባች ሀገር ኬኒያ በዋናነት የመግባት አዝማሚያ እንደሚታይ ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ ህገወጥነትን መከላከል የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ ባለመሆኑ የሁሉንም ባለድርሻ ርብርብ የሚጠይቅ ነው፡፡ ገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ በየትኛውም የአገሪቱ አቅጣጫ አለ። በአርባምንጭ መግቢያና መውጪያ አካባቢዎች መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች በማቋቋም ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ያን ያህል የሚያረካ ግን አይደለም። ስለዚህም ነው “ሁሉም እንዲሳተፉበት የተደረገው” ይላሉ። አሁንም መላው የንግዱ ማህበረሰብና ህዝብ እንዲሳተፍበት ካልተደረገ ሁሉንም ነገር በመንግሥት ብቻ መቆጣጠር አይቻልም የሚል ሃሳብ አላቸው። ሁሉም ነገር የሚሠራው በህዝቡ ውስጥ ነው። በመሆኑም ድርጊቱን በመቆጣጠር ረገድ ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እንዳሉ ሁሉ የህብረተሰቡ ተሳትፎም በዛው ልክ ሊያድግ ይገባል ብለዋል፡፡

የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጻራ እንደሚሉት ከሆነ፥ አዋጁ ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር ሥልጣን የሰጠው ለፌዴራል ፖሊስ ነው። ይሁን እንጂ በገቢና ወጪ በቀጥታ የሚሳተፉ ሌሎች ተቋማትም ይመለከታቸዋል። ህዝቡና የክልል መስተዳደር አካላትም ተቀናጀተው መሥራት አለባቸው። የቅንጅት ሥራው ቀደም ሲል ከነበረው ጊዜ አሁን የተሻለ ነው። በዚህም በተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው።

ህገወጥነትን ለመከላከል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ድርሻ አለው የሚሉት አቶ ገበየሁ፥ ለአብነትም በቀን 24 መጋቢት 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ 41 በርሜል ቤንዚን በህገወጥ መንገድ ጭኖ ሊጓዝ የነበረ ኤፍ.ኤስ.አር መኪና በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ይናገራሉ፡፡ ልባሽ ጨርቆች፣ አደንዣዥ ዕጽ፣ መሳሪያ፣ ጥይት፣ ጫማዎችና ሌሎች ህገወጥ የሆኑ ወንጀሎችን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ከህብረተሰቡ በሚደርሳቸው ጥቆማ ሆነ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት በሚመጣላቸው መረጃ መሠረት በቅንጅት እየሰሩ ለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡

በአገር ደረጃ ለተያዙ የልማት ሥራዎች የገንዘብ ምንጩ ከግብርና ታክስ የሚሰበስበው ገቢ ነው። የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ ደግሞ ይህን አቅም የሚያዳክም ነው። የሚገባው የዕቃ ዓይነት የደህንነትና የጤና ጠንቅ ሊሆን የሚችል ነው። በህብረተሰቡም ላይ የጤና አደጋ የሚያደርስ የዕቃ ዓይነት አብሮ የሚገባበት ሁኔታም አለ። ለምሳሌ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሀኒቶች፣ የታሸጉ ምግቦች፣ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች አብረው ይገባሉ። በአማራ፣ በቤኒሻንጉልና በጋምቤላ ክልሎች በርካታ የጦር መሣሪያዎች በዚህ ዓመት የተያዙበት ሁኔታ መኖሩን መጥቀስ ይቻላል። ይሄ የአገሪቱን ዜጎች ደህንነትና ሰላም ከመጉዳት አንፃር ትልቅ ስጋት የሚፈጥር ነው።

ኮንትሮባንድ በህጋዊ ነጋዴ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። በርካታ ቅሬታዎችም እንደሚቀርብላቸው አቶ ምህረቱ ይናገራሉ። ህጋዊ ነጋዴ በተመሳሳይ ዕቃ ከኮንትሮባንድ ነጋዴው ጋር ሊወዳዳር አይችልም። የሚቀርቡትም ቅሬታና አቤቱታዎች ትክክለኛ ናቸው። ይህን ችግር በየጊዜው ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው። ለምሳሌ ባለፈው በጀት ዓመት በከተማው ከነበረው ግብር ከፋይ አሁን ላይ ወደ ህጋዊ የንግድ ስርዓቱ እየመጡ ያሉ አዳዲስ ግብር ከፋዮች ለዚህ እንደማሳያ ማንሳት የሚቻል ነው፡፡ ሆኖም የመቆጣጠሩ ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቢሠራም የሚጠበቀውን ያክል ባለመሆኑ አሁንም ሰፊ ትግልና ጥረት እንደሚጠይቅ ይገልጻሉ።

በአጠቃላይ በየአካባቢው የተጀመሩ ሥራዎች በተወሰነ ደረጃ ውጤት ያስገኙ ቢሆንም አሁንም ሠፊ ሥራ የሚቀር መሆኑን ይጠቅሳሉ። «ክትትሉን ለማጠናከር የተጀመረው እንቅስቃሴ በሁሉም ቦታ ሽፋን ያገኘ አይደለም። ይህን ማስፋትና ማጠናከር ያስፈልጋል። አሁንም ኮንትሮባንድ የሚወጣና የሚገባ አለ» በማለት የችግሩን ስፋትና አሳሳቢነት ያነሳሉ። ኮንትሮባንድ የአገሪቱን የገበያ ሁኔታ የሚያዳክም በመሆኑ የፌዴራልም ሆነ የክልል አካላት ትኩረት ሰጥተው በጋራ መሰራት አለባቸው የሚል ማሳሰቢያም አላቸው።

በሁሉም አካባቢ ወጥ የሆነ የንግድ ዘዴ ባለመኖሩ ኮንትሮባንድ ነጋዴው እንደፈለገ ከአርሶ አደሩና ከአርብቶ አደሩ እንስሳትን አዋጭ ባልሆነ ዋጋ መሸመቱ ጉዳት እንዳለው ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት አርብቶ አደሩ ከእንስሳቱ ተገቢውን ዋጋ እያገኘ አይደለም። እንደ አገርም እንስሳትንና ከእንስሳት የሚገኘውን ውጤት በመሸጥ መገኘት ያለበትን የውጭ ምንዛሬ እያሳጣ ነው ኮንትሮባንድ።

ህገወጥ ነጋዴዎችን ማሸነፍ የሚቻለው አሳዶ በመያዝ ብቻ ሳይሆን ወጥ የንግድ ዘዴ በመዘርጋት ጭምር ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ኤክስፖርት በሚደረጉ ምርቶች ላይ የተጠናከረ የንግድ ሁኔታዎች አለመፈጠሩ አሳሳቢ ነውና አሁንም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ጉዳዩ የጋራ መከላከል፣ የጋራ ጥረትና ቁርጠኝነትን ይሻል።

በዘላለም ተስፋዬ