በዘንድሮ የክረምት ወራት በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ላይ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ከ2.4 ሚሊዮን በላይ የፍረፍሬ ችግኞችን ለመትከል ተቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል – የስልጤ ዞን አስተዳዳሪ  

በዘንድሮ የክረምት ወራት በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ላይ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ከ2.4 ሚሊዮን በላይ የፍረፍሬ ችግኞችን ለመትከል ተቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል – የስልጤ ዞን አስተዳዳሪ  

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 22/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዘንድሮ የክረምት ወራት በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ላይ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ከ2.4 ሚሊዮን በላይ የፍረፍሬ ችግኞችን ለመትከል ተቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የስልጤ ዞን አስተዳዳሪ አስታወቁ።

በዞኑ ምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ የዞንና የወረዳ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የፖም ችግኝ ተከላ መርሃግብር ተካሂዷል።

በወረዳው የሚገኙ አንዳንድ አርሶአደሮችም የፖም ፍሬን በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በወረዳው በተመረጡ ክላስተሮች የፖም ፍሬ ችግኝ ተከላ እየተከናወነ ሲሆን በዚህም ፍሬውን ምዕረብ ሙጎ፣ ሙጎ ተራራ እና በቢላሎ ቀበሌያት በስፋት በማምረት ይታወቃሉ።

በወረዳው ሙጎ ተራራ ቀበሌ ያነጋገርናቸው አርሶአደሮችም የፖም ምርትን በአካባቢያቸው ማምረት ከጀመሩ ወዲህ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ሌሎች የችግኝ ዓይነቶችን የመትከል ተግባር በማከናወን ላይ መሆናቸውን የጠቁሙት አርሶአደሮቹ  ከዘርፉ የተሸለ ገቢ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም የገበያ ትስስር አለመኖሩ ችግር እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሸምሱ ሀምዲኖ በበኩላቸው በወረዳው እስከአሁን 6መቶ 44 ሄክታር መሬት በፍራፍሬ መልማት መቻሉን ገልጸው እየተስተዋለ ያለውን የገበያ ትስስር ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ቀጣይ የፖም ምርትን በብዛትና በጥራት በመምራት ገበያ የማፈላለግ ስራ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በተለይም ወረዳው ለፖም ፍሬ ምርት ምቹ በመሆኑ ይህንኑ ለማስፋፋትና ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በዘንድሮው ዓመት በክላስተርና በመደበኛው 104ሺ የፖም ችግኞችን ለማትከል ተቅዶ እየተሰራ ሲሆን እስከአሁን ባለው ሂደትም 80በመቶ ማከናወን ተችሏል ነው ያሉት።

የምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሹክረቶ አባቢያ በወረዳው የፖም ፍሬ ማልማት ከተጀመረ ከ10ዓመታት ባላይ ያስቆጠረ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት ህብረተሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የደጋ ፍረፍሬን ምርትን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የተነገሩት ዋና አስተዳዳሪ ለዚህም በዘርፉ ተጠቃሚ የሆኑ ሞዴል አርሶአደሮች ማሳያዎች ናቸዉ ብለዋል።

በችግኝ ተከላው መርሃግብር የተገኙት የስልጤ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ አሊ ከድር በዞኑ በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ላይ ዘርፈብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን የችግኝ ዓይነቶችን የመትከል ተግባር በስፋት እየተከናወነ ሲሆን በዓመቱ በአጠቃላይ ለመትከል ከተያዘው 79ሚልዮን ችግኞች ውስጥ 2.4ሚልዮኑ የፍራፍሬ ችግኞች መሆኑን ተናግረዋል።

በዘርፉም የሚፈለገውን ጥቅም ማግኘት እንዲቻል ቀደምሲል የነበረንን አመለካከት በመቀየር አዳዲስ አሠራሮችን ተከትለን መስራት ይኖርብናል ያሉት አቶ አሊ በልዩ ሁኔታ በፖም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ናስር ጀማል – ከሆሳዕና ጣቢያችን