የሚጤስ ውሀ !!!

የሚጤስ ውሀ !!!

በአንዱዓለም ሰለሞን

መዳረሻችን ሩቅ ነው፡፡ ይህ ግን ለኪሎ ሜትሩና ለመንገዱ እንጂ ለልባችን ግን አይደለም፡፡ ሁሉም የእኛ ነውና አብረን የእኛ ወደሆነው የኢትዮጵያ ክፍል እንጓዝ ዘንድ ነው ለዛሬ የመረጥኩት፡፡

ኢትዮጵያ ሰፊ ብቻም ሳትሆን መልከ ብዙ ነች። ገጾቿን በገለጥን ቁጥር ብዙ ዓይነት ቀለምና አስደናቂ ተፈጥሮን እናያለን። ተፈጥሮ ደግሞ የውበት መገለጫ ነው። መንፈስን ዘና የሚያደርግ፣ ውስጥን በሀሴት የሚሞላ፡፡

ጉዟችንን ጀምረናል፡፡ ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል አቅንተን በጣናዋ ፈርጥ ፣ በባህር ዳር ጥቂት አረፍ ብለን ጢስ ዓባይ ላይ ቆይታ አድርገን እናበቃለን፡፡ የታላቁ ዓባይ ጉዞም እንዲሁ ነው፡፡ ከመነጨበት ተነስቶ፣ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በገባር ወንዞች አቅሙን አጎልብቶ ይጓዝና ከሀገሩ ድንበር አልፎ ይፈሳል፡፡ ሲፈስ ታዲያ ዝም ብሎ አይደለም፡፡

ሌሎች የከበረ ማዕድን ያህል ዋጋ የሚሰጡትን ለም ዐፈራችንን ተሸክሞ እየተገማሸረ ሲጋልብ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡ እኛ፤ “ ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” በማለት ብንዘብትበትም፣ ለመኖሪያችን ብርሀን እንዲፈነጥቅ ለማድረግ ግን ብዙ ዘግይተናል፡፡ እንዲያው ብቻ በጸጸት፣ በቁጭትና በሀዘን እንጉርጉሮ ስንሸኘው ኖረናል ፡- “አልገባቸውም ትርጉሙ ዕንባዬን “ዓባይ” የሚሉ ዕንባዬን “ውበት” የሚሉ በጉንጬ ላይ ሲንቆረቆር ንጹህማ ቢሆን ነበር ግና ኩሌን ከዓይኔ ጠርጎ ውበት ከየት እንዴት አርጎ ? ”

ዕንባዬን “ዓባይ” የሚሉ

ዕንባዬን “ውበት” የሚሉ

በጉንጬ ላይ ሲንቆረቆር

ንጹህማ ቢሆን ነበር

ግና ኩሌን ከዓይኔ ጠርጎ ውበት ከየት እንዴት አርጎ ?

አሁን ግን፤ የእኛ ትውልድ ይህ ታሪክ ሲቀየር በማየቱ ዕድለኛ ነው፡፡ ዓባይ ዛሬ ለሀገሩ ኩራት፣ ለወገኑ እራትና መብራት እየሆነ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ዛሬ እኛ በዓባይ ውበት ስንደነቅ፣ ቅኔ ስንቀኝለትም ሆነ ስንኝ ስንቋጥርለት ደስ እያለን እንጂ ቁጭት እያንገበገበን አይደለም፡፡ ከሀዋሳ እስከ አዲስ አበባ ያለውን 286 ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዘን ከሀገራችን ርዕሰ መዲና ደርሰናል፡፡

ቀጣዩ፣ ማለትም ከአዲስ አበባ እስከ ባህር ዳር ያለው ጉዞ ደግሞ 495 ኪሎ ሜትር ርቀትን ይሸፍናል፡፡ ታላቁን ወንዝ የምናገኘው ግን ጎሀ ጽዮንን አልፈን ከተጓዝን በኋላ ነው፡፡ በመንገዳችን ላይ የዓባይ ወንዝ፣ በድርሰቶቻችን፣ በስነ ቃሎቻችንና በአፈ ታሪክ ዝናውን ስናነብና ስንሰማ በኖርነው በዚህ በረሀ እንደ አስፈሪ ዘንዶ እየተጥመለመለ በጸጥታ ሲጓዝ ነው፡፡ እኛም በዜማ አጅበነው ጉዟችንን እንቀጥል፦

“የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና ፣

የማይደርቅ የማይለቅ ለዘመን የጸና ፤

ከጥንት ከጽንሰ አዳም ገና ከፍጥረት ፣

የፈሰሰ ውሀ ፈልቆ ከገነት ፤

ግርማ ሞገስ የሀገር ጸጋ የሀገር ልብስ ፣ ዓባይ … ፣ የበረሀው ሲሳይ ፤ ”

ባህር ዳር ከተማ ላይ፣ ዓባይ ዳግም ይጠብቀናል፤ ከጣና ተወዳጅቶ፡፡ የጣና ሀይቅን ሰንጥቆ ሲያልፍ ማየት የሚያስደንቅ ትዕይንት ነው፡፡

ጽዱዋ የባህር ዳር ከተማና አካባቢዋ ለቱሪስት መስህብ የሚሆኑ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ሀይማኖታዊ መስህቦችንና ቅርሶችን በጉያዋ ይዛለች። ጣናን ከማየትና ከጀልባ ላይ ከመንሸራሸር ባሻገር ታላቁን ዳጋ እስጢፋኖስን ጨምሮ ሌሎች የጣና ገዳማትን መጎብኘት ሌላኛው የከተማዋ ገጸ በረከት ነው፡፡

በዚያ ታሪክ አለ፡፡ ዕውቀትን የያዙ የብራና መጽሀፍትና የተለያዩ ቅርሶች ለዘመናት ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ ጣና አክብሮ ለትውልድ ያሻገረው፣ ሸሽጎ ለእኛ ያቆየው ሀብት ብዙ ነው፡፡ አሁን ለመዳረሻችን ተቃርበናል። በዘንባባዎቿ በምትታወቀው ከተማ ጥቂት አረፍ ብለን ጉዟችንን ስንቀጥል በ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፤ የጢስ ዓባይ ፏፏቴ፡፡ ይህን ፏፏቴ ለመጎብኘት ተመራጩ ጊዜ ክረምት ነው፡፡

ያኔ ዓባይ ይሞላል፡፡ ሞልቶ መፍሰስ ብቻ አይደለም፤ ልክ በእሳት እንደ ተለኮሰ ደመራ ይጤሳል፡፡ የሚጤስ ውሀ፤ ጢስ ዓባይ! እንዲህ እየጤሰና በቀደዳቸው አራት ሰፋፊ ቦዮች እየፈሰሰ 42 ሜትር ቁልቁል ይወረወራል፡፡ ወደ ጎን 400 ሜትር ስፋት ያለው ይህ ማራኪ ፏፏቴ የዓባይ ግርማ ሞገስ የሚታይበት ነው፡፡ ከአጠገቡ ሳይደርሱ፣ ገና ከርቀት በዙሪያ ገባው ባሉ እጽዋት ተሸሽጎ የሚያስገመግመው ድምጹ ከርቀት ይሰማል፡፡

እየቀረቡ ሲመጡ እንደ በረዶ ብናኝ የሚረጨው ውሀ እንደ ውሽንፍር ልብስዎን ያበሰብሳል፡፡ ታዲያ ምን ይገድዎታል፡፡ በርቀት ሆነው ውበቱን ከማድነቅ ባሻገር አጠገቡ ተጠግተው ይህን “በረከቱን” መቋደስም አንዱ የጉብኝቱ አካል ነው፡፡ ጢስ አባይ በበርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ጎብኝዎች ይጎበኛል፡፡ ያም ሆኖ ቦታውን ለጎብኝዎች ምቹ ለማድረግ መሰራት የሚገባቸው ስራዎች አሉ፡፡

ከዚህ አንጻር በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይበል የሚያሰኙ ናቸው፡፡ በቋሚነት በዓመት አንድ ጊዜ በተለየ መልኩ ቦታው እንዲጎበኝ ለማድረግ ታስቧል፡፡ ይህ ዕቅድ ይፋ ሲደረግም የሀገራችን ታዋቂ አርቲስቶች በቦታው ተገኝተው ነበር፡፡ ይህ የተደረገውም የቱሪስት መስህቡን ይበልጥ ለማስተዋወቅ በሚል ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ ቦታው ለዕይታ ማራኪ ነው፡፡

ከፏፏቴው ባሻገር ዙሪያ ገባው በተፈጥሮ ውበት ያጌጠና በአረንጓዴ ልምላሜ የደመቀ፡፡ ወዲህ ደግሞ የአካባቢውን ባህል የሚያንጸባርቁ የተለያዩ ባህላዊ አልባሳትንና ዕቃዎችን የሚሸምቱበት፡፡ ቦታውን ማልማት የታላቁን ወንዝ ውበት ለዓለም ከመግለጥ ባሻገር የከተማዋን ነዋሪዎችንም መጥቀምም ነው፡፡

ጢስ አባይ ውለው ቢያድሩበት የማይሰለች የተፈጥሮ መስህብ ነው። እንኳንስ ከሌላ አካባቢ የመጣ እንግዳ ይቅርና እዛው ተወልደው ያደጉትና አብዝተው የተመላለሱበት የአካባቢው ነዋሪዎች ሊያዩት ይናፍቁታል፡፡ ይህ ስሜት እንደ ሱስ የሆነባቸው ደግሞ ከፏፏቴው አጠገብ ካለ ቋጥኝ ላይ ተቀምጠው፣ በዋሽንታቸው ዓባይን ያነጋግሩታል፡፡ ለዚህ የትዝታቸው ተምሳሌት፣ የተስፋቸው ምልክት ለሆነ ታላቅ ወንዝ እያንጎራጎሩ ያዜሙለታል፤ ይቀኙለታልም፡፡

እነሆ ዛሬ ዓባይ ለሀገሩ መብራት ከመሆን ባሻገር የተስፋ ብርሀን ሊፈነጥቅ ቤኒሻንጉል ላይ መሰረት ተጥሎበታል። ከዚህ በፊት ጢስ ዓባይን የጎበኘ ሰው የደስታ ስሜቱ በቁጭት ሀሳብ መደፍረሱ አይቀሬ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ግን አንድ ጎብኚ የሚሰማው ስሜት ከዚህ በተቃራኒው ነው፤ ጢስ ዓባይ ላይ ሆኖ ጉባን ባሰበ ጊዜ ሀሴትን ያደርጋልና ።