ለአቅመ ደካሞች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት – የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ

ለአቅመ ደካሞች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት – የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 20/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለአቅመ ደካሞች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ ገለፁ፡፡

ዋና አስተዳዳሪው እና የዞኑ አስተባባሪ ኮሚቴ በሐመር ወረዳ ቱርሚ ከተማ አስተዳደር ለአንዲት አቅመ ደካማ እናት የተገነባ ቤት መርቀው አስረክበዋል።

በሐመር ወረዳ ቱርሚ ከተማ አስተዳደር ኑሮአቸውን ያደረጉት ወ/ሮ ሐሚ ጋሮ  ቤታቸው ፈርሶ ለመጠለል ተቸግረው እንደነበር ተናግረዋል።

አራት ልጆቻቸውን እንጨት በመልቀም የሚያስተዳድሩት እኚህ እናት ከልጆቻቸው ጋር ፀሀይና ብርድ ይፈራረቅባቸው እደነበር ያስታውሳሉ፡፡

መንግስት ያለባቸውን ችግር ተገንዝቦ ስላደረገላቸው እገዛ አመስግነዋል።

ቤቱን መርቀው ያስረከቡት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ እንደዞን ከዚህ በፊት ከሦስት መቶ በላይ ቤቶች ለአቅመ ደካሞች ገንብቶ ማስረከብ ተችሏል ብለዋል።

በዚህ ክረምት ከ580 በላይ ቤቶች እንደሚገነቡና እንንደሚታደሱም ዋና አስተዳዳሪው አስረድተው ሁላችንም የፈጣሪ ትዕዛዝ ጭምር በሆነውና ለህሊና እርካታ በሚሰጠው በጎ ተግባር መሳተፍ አለብን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በርካታ ዜጎች በቤት ችግር ኑሮአቸውን የሚመሩ እንዳሉ የገለፁት የደቡብ ኦሞ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሀላፊ አዘብ ራያ፤ በዚህም መምሪያው ከዞን አስተዳደርና ከሌሎች አካላት ጋር በመቀናጀት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረው በዚህ ክረምትም የተጠቀሰው የቤት ግንባታና ጥገና እውን እንዲሆን ልንረባረብ ይገባል ብለዋል ሀላፊዋ።

መረዳዳትና መደጋገፍ የብልጽግና ፓርቲ እሴቶች በመሆናቸው ዜጎች ካላቸው ጉስቁልናና ድህነት ተላቀው ወደተሻለ ብልጽግና ከፍታ ላይ መድረስ እንዲችሉ ዘር፣ ሀይማኖት፣ ቀለም ልዩነት ሳይኖር በተቀደሰው ተግባር መሳተፍ ያስፈልጋል ያሉት የደቡብ ኦሞ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ተካልኝ ጋሎ ናቸው።

ለቤቱ ግንባታ የዞኑ አስተዳደር 2መቶ ሺህ እንዲሁም የቱርሚ ከተማ አስተዳደር 70 ሺህ ብር ወጪ በማውጣት መገንባቱ ተገልጿል።

ለግንባተው  አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የዕውቅና ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ቅርንጫፍ ጣቢያችን