ከሳውላ ቃቆ የመንገድ አካል የሆነው የቃቆ ዎሞሮ የመንገድ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ተጠየቀ

ከሳውላ ቃቆ የመንገድ አካል የሆነው የቃቆ ዎሞሮ የመንገድ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ተጠየቀ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 18/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኦሞ ዞን ከሳውላ ቃቆ የመንገድ አካል የሆነው ቃቆ ዎሞሮ የመንገድ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ተጠየቀ።

የመንገዱ ግንባታ ያለበትን ደረጃ የዞኑ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት መስክ ምልከታ አድርገዋል።

መንገዱ 30 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን 13 ኪሎ ሜትሩ ጥገና የሚደረግለት መሆኑ ተገልጿል።

ከ6 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በሶዶ ዲስትሪክት ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ግንቦት 2014 ዓ.ም በሁለት ዓመት ጊዜ ገደብ ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ውል አስሮ ወደ ሥራ መገባቱን የፕሮጀክቱ ስትራክቸራል መሐንዲስ ያሬድ አለሙ አስረድተዋል።

በአሁን ወቅት የመንገዱ አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተገነባ መሆኑንም ሀላፊው ተናግረው መንገዱ አሁን ባለበት ደረጃ መለስተኛ ተሽከርካሪዎችን እያስተናገደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የመንገዱ ዳገታማ የሆነው ክፍል በዝናብ ወቅት አፈሩ በውሃ የሚሸርሸር በመሆኑ ይህ አስፈልት እንዲነጠፍ ተደርጓል ይህ ሥራም በአጭር ጊዜ እንደሚጀመር ተብራርቷል።

በአሁን ወቅት የመንገዱ ቆረጣና ሙሌት 85 በመቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም አጠቃላይ የግንባታ ሂደት ገና ከ30 በመቶ ያልዘለለ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአማካሪ መሐንዲስ ተጠሪ መሐንዲስ ተስፋዬ ደሴ ናቸው።

 ከዚህ በፊት የግንባታ ጥሬ ዕቃዎች እጥረት እንደነበር አስታውሰው በአሁን ወቅት መንገዱ ፈጥኖ ማለቅ እንዲችል በተወሰነው መሠረት ይህ ችግር ተፈቷል ሲሉም ሀላፊዎች ተናግረዋል።

የመንገዱን ግንባታ በ2016 ዓ/ም ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ለማስረከብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተገነባ ስለመሆኑም ተገልጿል።

የማሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጳውሎስ ጎዳና እንደገለፁት በግንባታ ላይ የሚገኘው መንገድ ከዚህ በፊት ለእንቅስቃሴ የማይመች ከመሆኑ ባሻገር ወላድ እናቶችና ህሙማንን ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ እጅግ ፈተኝ እንደነበር ያስታውሳሉ።

በአሁን ወቅት ግንባታ እያካሄደ ያለውን ተቋራጭ በመደገፍ መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቷል ሲሉም ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

የመንገዱ ግንባታ ያለበትን ደረጃ መስክ ምልከታ ያደረጉ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በበኩላቸው ከሣውላ ቃቆ የመንገድ አካል የሆነው ቃቆ ዎሞሮ ተራራ ከዚህ በፊት ሦስት ተቋራጮች ወስደው ወደ ግንባታ ቢገቡም መንገዱን አጠናቅቆ ማስረከብ አልቻሉም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁን ወቅት ግንባታ እያካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር እያከናወነ ያለው የግንባታ ሂደት ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል አቶ ንጋቱ።

መንገዱ ለዘመናት ለአካባቢው ማህብረሰብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱንም ዋና አስተዳዳሪው አስታውሰው በአሁን ወቅት መንግስት የተጀማመሩ ፕሮጀክቶችን መጨረስ የሚል ዕቅድ ነድፎ እየሠራ ይገኛል።

በዚህም ቃቆ -ዎሞሮ የመንገድ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የዞኑ አስተዳደር አስፈለጊ በሆኑ ጉዳዮች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ይህንንም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በመስክ ምልከታው የመንገዱ ግንባታ ሂደት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጥ መቻሉን አቶ ንጋቱ ገልፀው በቀጣይ አሁን ካለበት ይበልጥ ሳይቆራረጥ በተያዘለት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ሊሠራ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎችም  የህዝቡ መልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ እየዘለቀ ያለውን ቃቆ-ዎሞሮ የመንገድ ግንባታው በውሉ መሠረት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አበራ – ከጂንካ ቅርንጫፍ ጣቢያችን