“ትንበያው ከአየር ሁኔታው ጋር የተጣጣመ ሥራ አንዲሰራ ያደርጋል” – አቶ ከፍያለው አየለ

የሳምንቱ እንግዳችን አቶ ከፍያለው አየለ ናቸው፡፡ ትውልዳቸው በሲዳማ ክልል ዳራ ወረዳ አዳሜ ቴሶ ቀበሌ ነው፡፡ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ካጠናቀቁ በኋላ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ በሜትዎሮሎጂ ትምህርት ዘርፍ ተምረዋል፡፡ ቀጥሎም በጅማ ዩኒቨርስቲ በማህበረሰብ ጤና ሳይንስ እንዲሁም በአዳማ ዩኒቨርስቲ በሜትዎሮሎጂ ትምህርት 2ኛ ድግሪያቸውን ሰርተዋል፡፡

በ2001 ዓ/ም በጅማ የሜትዎሮሎጂ ባለሞያ ሆነው ሥራ የጀመሩት አቶ ከፍያለው በ2011 ዓ/ም በደቡብ ክልል ሜትዎሮሎጂ ባለሞያ በመሆን ለሶስት አመታት አገልግለዋል፡፡ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ሜትዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት የደቡብ ክልል ሜትዎሮሎጂ ማእከል መሪ ሥራ አስፈፃሚ በመሆን እያገለገሉ ይገኛል፡፡ የሜትዎሮሎጂ ማእከሉ እያከናወነ በሚገኘው የሥራ እንቅስቃሴ ዙሪያ ያደረግነውን ቆያታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

መልካም ንባብ

በደረጀ ጥላሁን

ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ከፍያለው፦ እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፦ የሜትዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት አመሰራረት በአጭሩ ቢገልጹልን?

አቶ ከፍያለው፦ በኢትዮጵያ የአየር ትንበያ ሥራ ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ መረጃዎችን ለመሰብሰብ የሚረዱ ጣቢያዎችን በመትከል ነበር ሥራ የጀመረው። ከዚያም እያደገና የሥራ ዘርፉን እያሰፋ በመምጣት አሁን የደረሰበት ደረጃ ደርሷል። በዚህም የአየር ሁኔታን መሰረት በማድረግ ለግብርና ሥራ የሚረዱ መረጃዎችን መሰጠት ዋና ሥራ ተደርጎ ሲሰራ ነበር። ከ19ኛው መቶ አጋማሽ በኋላ በአቪዬሽን ዘርፍ ከአየር በረራ ጋር የተገናኙ መረጃዎችን እንዲሰጥ ተብሎ እንደ አንድ አገልግሎት ዘርፍ ተቋቁሞ ነበር። ከዚያም እ.ኤ.አ 1980 መጨረሻ አካባቢ ኤጄንሲ ሆኖ ተቋቋመ፡፡ በዚህም ለግብርና፣ ውሃ፣ ጤና እና አካባቢ ጥበቃ ከመሳለሉ ዘርፎች ጋር በጋራ እየሰራ የቆየ ተቋም ነው፡፡

ንጋት፦ የሜትዎሮሎጂ ትንበያ መረጃዎች ጠቀሜታ እንዴት ይገለፃል?

አቶ ከፍያለው፦ የሜትዎሮሎጂ ትንበያ ለተለያዩ ተቋማት ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። ትንበያውን መሰረት አድርገው የሚሰሩ አካላት ከአየር ሁኔታው ጋር የተጣጣመ ሥራ እንዲሰሩ ከማድረጉ በተጨማሪ በአየር ለውጥ ሳቢያ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ እገዛ ያደርጋል፡፡

በዚህ መሰረት በተለይ የግብርና ልማትን እውን ለማድረግ የአየር ጠባይን ማወቅ ተገቢ ነው። ኤጄንሲው የአግሮክላማይቲክ የእርጥበት ቀጠናዎች ክፍፍል በክልልና በወረዳ ደረጃ ተግባራዊ ሊያደርጉ የሚችሉ ጥናቶችን በማካሄድ የግብርና ሜትዎሮሎጂ የምክር አገልግሎቶች ለአርሶ አደሩ ያደርሳል። በተጨማሪም ለግብርና ልማት መጎልበት አስተዋጽኦ ያላቸው እንደ አማካይ የዝናብ መጠን፣ የዝናብ መለዋወጥ ባህሪ፣ የሙቀት እና የትነት መጠን፣ የድርቅ ክስተት ሁኔታ ወዘተ ሥራዎች ለተገልጋይ በአግባቡ እንዲደርሳቸው ያደረጋል፡፡

በብሄራዊ ሜትዎሮሎጂ ኤጄንሲ የሚሰበሰቡ መረጃዎችም በዓይነትና በመጠን ረገድ ብዙ ናቸው፡፡ በቁጥር፣ በጽሁፍ፣ በምልክት፣ በካርድ፣ በቻርት፣ በሪፖርት፣ በምስልና በመሳሰሉት ተሰብስበው ለሚመለከታቸው አካል ይሰራጫሉ፡፡

ንጋት፦ በሜትዎሮሎጂ ማእከሉ በዋናነት የተከናወኑ ተግባራት ምን ይመስላሉ?

አቶ ከፍያለው፦ የሜትሮሎጂ ኢንስትቲዩቱ በመንግስት እውቅና ተሰጥቶት ከተቋቋመ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ የአየር ሁኔታን መሰረት በማድረግ መረጃ ለመሰብሰብ የሚረዱ ጣቢያዎች ተቋቁመዋል፡፡ ከነዚህ ጣቢያዎች መረጃዎችን በመሰብሰብ እና በመተንተን ለግብርና፣ ውሃ፣ አካባቢ ጥበቃ፣ አደጋ ስጋት መከላከል እንዲሁም አየር በረራ ለመሳሰሉት ውሳኔ ለመስጠት እንዲያስችላቸው መረጃ ይሰጣል። ከዚህ በተጨማሪ ለፖሊሲ አውጪዎች ውሳኔ የሚያሰጥ መረጃ በመስጠት አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ በኢንስትቲዩቱና በእኛም እየተሰራ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ሜትዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት በኩል ሀገራዊና ክልላዊ መረጃዎች የሚሰራጭ ሲሆን የደቡብ ክልል ሜትዎሮሎጂ ማእከል ይህን መረጃ መሠረት በማድረግ ለዞንና ወረዳዎች እንዲደርስ እናደርጋለን፡፡

ንጋት፦ የሜትዎሮሎጂ ትንበያን ዘመናዊ ከማድረግ አኳያ ምን ተሰርቷል?

አቶ ከፍያለው፦ በመረጃ መቀበያ ጣቢያዎች ዘመኑ የሚጠይቀው ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እንጠቀማለን፡፡ ሥርጭት እና መጠኑን ለማብዛት ሥራዎች ተሰርተዋል። እንዲሁም የአካባቢን ሁኔታ ያገናዘበና የአየር ንብረት ለውጥን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ምርምሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ይሠራል፡፡

አዳዲስ ቴክኖሎጂን ከመጠቀም አንፃር የተለያዩና ለሜትዎሮሎጂ ሥራችን እገዛ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመናል። ፕላስትክ ሬን ጌጅ፣ ክላውድ ሲዲንግ የመሳሰሉት በኢንስትቲዩቱ የሚሰሩ ናቸው። ከዚህ ሌላ አዳዲስ ራዳር መትከል እና የመብረቅ መከታተያ መሣሪያዎች እንዲሁም የአየር ብክለትን መከታተል የሚያስችሉ መሳሪያዎችም አሉን፡፡ ለእነሱም የግንዛቤ መፍጠር ሥራዎች በስፋት ተሰርቷል፡፡

በምርምር ደረጃ ተደጋግፈን የምንሰራው ከዋናው መስሪያ ቤት እና ከምርምር ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምርምሩን በገንዘብ ሊደግፉ ከሚችሉ አካላትም ጋር ነው፡፡ ከዚህ ሌላ በተለይ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ጋር በጋራ የምንሰራቸው ሥራዎች አሉ፡፡

ንጋት፦ የአደጋ ስጋትን ቀድሞ ከማስጠንቀቅ አኳያ የሚሰሩ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?

አቶ ከፍያለው፦ የምናገኘውን መረጃ መሠረት በማድረግ ለሚመለከተው አካል በወቅቱ እናደረሳለን፡፡ ከአየር ለውጥ ጋር ተከትሎ የሚከሰቱ የጎርፍ፣ የድረቅ እና ወቅታዊ የወረርሽኝ በሽታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እናቀርባለን፡፡

አደጋዎችን ከመቀነስ አኳያም የግንዛቤ መፍጠር ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ከባድ ዝናብ ሲዘንብ ለጎርፍ ተጋላጭ የሚሆኑ አካባቢዎች አሉ፡፡ በተለይ ተዳፋት መሬት ባለበት እና በውሃ ዳር እንዲሁም ደራሽ ወንዝ ያለበት አካባቢ ተጠቂ ይሆናል። ሜትዎሮሎጂ አደጋን በመቀነስ ልማትን ከማፋጠን በተጨማሪ በሰው እና በንብረት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ እንደ ማእከል ሆኖ ይሰራል፡፡

የአየር ለውጥን ተከትሎ በክልሉ የአየር ሁኔታው የመቀያየር ባህሪ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ ክስተቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ተጽእኖ እንዳያደርሱ ወይም ተጽእኖውን ለመቀነስ የሚረዱ መረጃዎችን እናደርሳለን፡፡ የዝናብ አጀማመር፣ ከባድ ዝናብ የሚዘንብባቸውና ጎርፍ ሊያስከትሉ የሚችሉባቸው አካባቢዎች መረጃዎችን መሰረት በማድረግ እንጠቀማለን። ጎርፍ፣ ድርቅ፣ የዝናብ መቆራረጥ የመሳሰሉት እና ከፍተኛ የሙቀት ሁኔታ የተለመዱ ችግሮች ናቸው፡፡

ንጋት፦ ቅድመ ማስጠንቀቂያን ከመተግበር አኳያስ ምላሹ ምን ይመስላል?

አቶ ከፍያለው፦ በኛ በኩል ሜትሮሎጂ ትንበያውን መሠረት አድርገን መረጃዎችን ለባለድርሻ አካላት እናደርሳለን፡፡ ተጠቃሚው አካል መረጃውን መሰረት በማድረግ እርምጃ ይወስዳል፡፡ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ህብረተሰቡ እንዲያውቀው እናደርጋለን፡፡ እርምጃ የሚወስደው አካል ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡

አደጋ ከመድረሱ በፊት ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ችግሩን የመከላከልና የመቀነስ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ ይሁን እንጂ የችግሩ ተጠቂ አካባቢ ሲደርስ እንደተፈለገው ላይሆን የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ እነዚህም ታች ያለው መዋቅር መረጃውን በወቅቱ ካለማድረስ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡

ንጋት፦ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ተለይተው ይታወቃሉ?

አቶ ከፍያለው፦ የአደጋ ሥጋት ያለባቸው አካባቢዎችን ቀደም ሲል የአደጋ ሥጋት አመራር መስሪያ ቤት ባወጣው መረጃ ተካተዋል፡፡ አሁን ላይ የአደጋው ድግግሞሽ እየጨመረ የመጣ ነው፡፡ ቀጣይ በጥናትም የሚዳብር ሆኖ በኛ በኩል የተለዩት ደቡብ ኦሞ፣ ኮንሶ፣ ጋሞ፣ ጎፋ የታችኛው አካባቢ ላይ ስለሆኑ ወራጅ ወንዝ በአብዛኛው ሌላ ቦታ የሚዘንበው በነዚህ አካባዎች ጉዳት ያደርሳል። ከዚህ በተጨማሪም በሲዳማ ክልል ጭሬ አካባቢ ከቦታ አቀማመጥ ጋር በተገናኘ ተጋላጭ ናቸው፡፡

ከላይኛው አካባቢ ደግሞ ሀዲያ ላይ ሻሻጎ አካባቢ፣ ደቡብ ምእራብ ክልል በአብዛኛው በእጽዋት የተሸፈነ ስለሆነ የጎርፍ ችግር ባይታይም ኮንታና ዳውሮ የቦታው አቀማመጥ ተዳፋት የሆነበት አካባቢ ለጎርፍ ተጋላጭ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ደቡብ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን የጫሞ፣ አባያና ሀዋሳ ሀይቆች ተደጋጋሚ ዝናብ በሚኖርበት ወቅት የውሃ መጨመር ይከሰታል፡፡ የብላቴ ወንዝን ተከትሎም እንዲሁ፡፡ ይህም ሰውን ከማፈናቀልና ሥራን ከማስተጓጎል በተጨማሪ ጎርፍ ሆኖ አካባቢውን ሊያጠቃ ስለሚችል ቀድሞ እንዲጠነቀቁ መረጃ የመስጠት ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ንጋት፦ የደቡብ ሜትዎሮሎጂ ማእከል ተደራሽነቱን ቢገልጹልን?

አቶ ከፍያለው፦ በኢትዮጵያ ሜትዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት የደቡብ ክልል ሜትዎሮሎጂ ማእከል ቀድሞ በደቡብ ክልል የነበሩትን ይዞ የማእከላዊና ደቡብ ኦሮሚያ የሚገኙ ቦረናን በከፊል ጉጂ፣ የምስራቅ ሸዋ እና ምእራብ አርሲ ዞኖችን በማካተት እየሰራን እንገኛለን፡፡

በክልሉ 172 የሜትሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ ሀያ አራት የሚሆኑት ሀገራዊ መረጃዎችን በመሰብሰብ ለዋናው፣ ለዓለም ሜትዎሮሎጂ እና ለኛም መረጃውን የሚሰጡ ናቸው፡፡ አርባ ምንጭና ሀዋሳ ያሉት ሁለት ጣቢያዎች ደግሞ አለም አቀፍ ናቸው፡፡ መረጃን ይሰበስባሉ፣ ወዲያው ለዓለም አቀፍ ሜትዎሮሎጂ ያደርሳሉ፡፡

የሜትዎሮሎጂ መረጃ አገልግሎቱ በርካታ ነው፡፡ የግብርና ምርት ማሳደግን ጨምሮ በውሃ ዘርፉ እንዲሁ በሀይድሮ ፓወር የግድቦች ደረጃን መከታተል ይገኝበታል። የውሃ ግድቦች ሲሰበሩ ጎርፍ ሆኖ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል የክትትል ስራ ይሰራል። ለአየር በረራ በክልላችን እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለበረራ የሚሆን የሜትዎሮሎጂ መረጃ ይሰጣል፡፡ አደገኛ የአየር ሁኔታ ሲፈጠርም መረጃውን እናደርሳለን፡፡

ንጋት፦ ቀረ የሚሉት ሀሳብ ካለዎት እድሉን ልስጥዎ፡-

አቶ ከፍያለው፦ ትንበያዎች ሲወጡ ቀድሞ የተመዘገቡ መረጃዎች የምንጠቀም ሲሆን እነዚህም ለቀጣይ ትንበያችን መነሻዎች ይሆናሉ፡፡ ያወጣነውን መረጃ ለዓለም አቀፍ ሜትዎሮሎጂ በመስጠት እነሱ የተሻለ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ያወጡታል። የሚያወጡት መረጃንም እንደ ግብአት የምንጠቀመው ይሆናል፡፡

ከዚህ ሌላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የውቅያኖስ ሙቀት፣ መሬት ላይ የሚከሰተው የአየር ግፊት፣ የንፋስ ፍጥነት አቅጣጫ፣ መሬት እና የውሃ ሀይል እንዲሁም ሙቀት በተለያዩ መንገዶች ይመዘገባሉ፡፡ መረጃውን የሚመዘግቡና የሚተነትኑት ዓለም አቀፍ ተቋማት ናቸው። መረጃ ድንበር ስለሌለው ከነዚህ ተቋማት በመውሰድ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታና የመሬት አቀማመጥ መሠረት አድርገን ዋና መስሪያ ቤቱም ሆነ እኛ በመረጃው ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡ ስለዚህ መረጃዎችን በተገቢው መጠቀም እንደሚገባ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡

ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ከፍያለው፦ እኔም አመሰግናለሁ።