“ከ50 በመቶ በላይ ግብርናው ኩታ ገጠም ሆኗል” – አቶ ገርማሜ ጋሩማ

“ከ50 በመቶ በላይ ግብርናው ኩታ ገጠም ሆኗል” – አቶ ገርማሜ ጋሩማ

የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ ገርማሜ ጋሩማ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት የደቡብ ማእከል ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ትውልዳቸው በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ነው፡፡ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ካጠናቀቁ በኃላ በ1978 ዓ.ም ከሀዋሳ እርሻ ኮሌጅ በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡

የስራ ህይወታቸውን በአላጌ ሚቶ እርሻ ልማት በማድረግ እስከ ቡናና ሻይ ልማት የቡና ማሻሻያ ፕሮጀክት /ሲፕ/ ድረስ ሰርተዋል፡፡ በ1985 ዓ/ም ቤንች ማጂ ከቀበሌ እስከ ዞን የግብርና ባለሞያ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በ1988 ዓ/ም በሀሮማያ ዩኒቨርስቲ በእርሻ ትምህርት የመጀመሪያ ድግሪ ተመርቀው ወደ ቤንች ማጂ በመመለስ ካገለገሉ በኋላ በ1994 ዓ/ም በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ ቀጥሎም የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል፡፡

አቶ ገርማሜ በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ባገኙት የትምህርት እድል በ2006 ዓ/ም በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ 2ኛ ድግሪ ሰርተዋል፡፡ ከዚያም በ2010 ዓ/ም በፌደራል ግብርና ሚንስቴር የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ጀነራል በመሆን ከሰሩ በኋላ ከ2015 ዓ/ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት የደቡብ ማእከል ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ ይገኛል፡፡

ከእንግዳችን ጋር በግብርና ትራንስፎርሜሽን ማእከሉ የሥራ እንቅስቃሴ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

መልካም ንባብ

በደረጀ ጥላሁን

ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ገርማሜ፦ እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፦ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት አመሰራረት እንዴት ነበር?

አቶ ገርማሜ፦ የሀገራችን ግብርና በርካታ ማነቆዎች አሉበት፡፡ እንደሚታወቀው የግብርና ሥራ በሀገራችን በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረ ቢሆንም ማደግ አልቻለም። የግብርና ሥራው እንዳያድግ ማነቆዎችን በመለየት የሚያስወግድ እንዲሁም የግብርና ሽግግር ሊያፋጥን የሚችል አንድ ማእከል እንደሚያስፈልግ በመንግስት ታምኖበት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ በመባል ተመሰረተ፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት ከ10 ዓመት በፊት የተመሰረተ ሲሆን በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና ደቡብ ክፍል ማእከሎችን በማቋቋም የግብርና ሥራውን ዘመናዊ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል፡፡

ንጋት፦ የማእከሉ ተግባር እንዴት ይገለጻል?

አቶ ገርማሜ፦ የደቡብ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ማእከል በዋናነት ግብርና እንዳይለወጥና እንዳያድግ ማነቆ ሆነው የያዙትን ችግሮች ለመለየት ጥናትና ምርምር ያደርጋል፡፡ የተለዩት ማነቆዎች ላይ ምን ቢሰራ ሊፈቱ ይችላሉ በሚለው ላይ የመፍትሄ ሀሳብ በማምጣት እና የተገኙ መፍትሄዎችን ደግሞ ሰርቶ እንዲያሳይ ተልእኮ ወስዶ ይሰራል፡፡ ለዚህም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንዲሰራና ሥራው ውጤታማ ሆኖ ሲገኝ የማስፋት ሥራ በመስራት ለሚመለከተው አካል እንዲያስተላልፍ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

ተግባሩን ለማሳካት በርካታ ፕሮጀክቶች ተቀርጸዋል፡፡ ከነዚህም አንዱ የግብርናውን ችግር ይፈታል የተባለው የግብርና ኩታ ገጠም እርሻ ሥራ ወይም የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ነው፡፡ ይህ የሆነውም የኩታ ገጠም እርሻ ሁሉም አርሶ አደር አንድ አይነት እውቀት አይኖራቸውምና መሬታቸውን ክላስተር ሲያደርጉ ግን እኩል ታታሪነት፣ ተወዳዳሪነትና እውቀት ይዘው ለመስራት ይረዳቸዋል፡፡ ከዚህ ሌላ ገበያን በተሰባሰበ መልክ ያገኛሉ፤ ተወዳዳሪም ይሆናሉ ተብሎ በተመረጡ 11 ሰብሎች ላይ ኩታ ገጠም እርሻን እንዲመሰረት ተደረገ፡፡ ይህ ሲደረግ ታዲያ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆኑ በመለየት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው።

ሌላው አርሶ አደሩ ለብዙ አመታት የተጠቀመበት ኋላ ቀር አስተራረስ በመቀየር ሜካናይዜሽን መስፋፋት እንዳለበት በማመን ነው ወደ ሥራ የተገባው፡፡ እንዲሁም አርሶ አደሩ የገበያ መረጃ እንዲያገኝ ለማድረግ ተችሏል፡፡ የግብርና ሰራተኞች በሁሉም አካባቢ ላይደርስ ይችላል፡፡ ስለዚህ አርሶ አደሮች በግብርና ላይ ያጋጠማቸውን ችግሮች ሊፈቱበት የሚችል 8028 የሚባል የመረጃ መለዋወጫ ሥርዓት ተፈጠረላቸው። ማንኛውም አርሶ አደር ይህን ቁጥር በመጠቀም የሚፈልገውን መረጃ ማግኘት ይችላል፡፡

ንጋት፦ በግብአት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የተሰራው ሥራ ምን ይመስላል?

አቶ ገርማሜ፦ የግብርና ግብአት ለምርት እድገት አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን አርሶ አደሩ በሚገባ ተገንዝቧል፡፡ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለውን ፋይዳ ከግብርና ጋር በመሆን ሰርተን አሳይተናል፡፡ ስራው እየሰፋ ሲሄድ የግብአት ፍላጎት እየጨመረ ይመጣል። ዘንድሮ የተፈጠረው እጥረት ከአለም አቀፍ እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ማየት ያስፈልጋል፡፡ ካለፉት አመታት የበለጠ በጀት ቢመደብም ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ አሻቅቧል፡፡ አሁን ላይ በበልግ፣ መኸር እንዲሁም በጋ ላይ በመስኖ ይመረታል፡፡ ስለዚህ ፍላጎት መጨመሩ ግድ ነው፡፡

በኛ በኩል የግብአት አቅርቦትና ሥርጭት ችግርን ለመፍታት አርሶ አደሮች ለግብአት የሚሆን ቁጠባ እንዲቆጥቡ ለማድረግ ከቆጠቡት ላይም ማዳበሪያ እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ ለዚህም ደቡብ ላይ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ስራውን ይሰራል፡፡ በሌላ በኩል ሁሉም ቀበሌያት ግብአት ላይደርስ ይችላል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የግብርና ትራንስፎርሜሽን የግብአት ሥርጭት ማእከል በመክፈትና በማሳደግ የአንድ ማእከል የግብአት አቅርቦት ሥርዓትን መሰረተ፡፡ አሁን በደቡብ ውስጥ 80 የሚሆኑ የግል የግብርና ግብአት መሸጫ ማእከላት ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ግብአት ገዝተው አርሶ አደሩ መንደር ድረስ እንዲገባ ያግዛሉ፡፡ ይህም ችግር መፍቻ ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል።

ሌላው ችግር የዘር አቅርቦት ነው፡፡ የዘር ሥርዓት ለማሻሻል ማህበረሰብ አቀፍ የዘር ሥርዓት ተብሎ ተመስርቶ ለበርካታ ማእከላት ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ለስራቸው የትራክተር፣ የዘር ማበጠሪያ፣ የመጋዘን እና ተሸከርካሪ በማመቻቸት ዘር ለአርሶ አደሩ እንዲቀርብ ተሰርቷል፡፡

ንጋት፦ አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም እርሻ ከሚያገኘው ጥቅም ባሻገር ሌሎች አገልግሎቶች እንዲያገኝ የተሰራው ሥራ ምን ይመስላል?

አቶ ገርማሜ፦ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት የአርሶ አደሩን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ አገልግሎቶችን እንዲስፋፉ የተለያዩ ሥራዎች ተሰርቷል፡፡ በተለያዩ ሥፍራዎች የገበያ ማእከሎች ተገንብተዋል። ምርት የማሰባሰብያና የመጫኛ ቦታዎች እየተገነቡ ነው፡፡ ዘመናዊ የችግኝ ጣቢያዎች ተከፍተዋል። /ለአቨካዶ በሲዳማ ለሙዝ አርባ ምንጭና በሌሎችም/ ወጣቶች የሚሰለጥኑበት ማሰልጠኛ ማእከላት ተገንብተዋል፡፡

ሌላው አጠቃላይ ግብርናን የመለወጥ ሥራ በጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ሙዝ፣ አቨካዶ፣ ማንጎ፣ ቲማቲምና ሽንኩርት ላይ በተሰራው ሥራ ምርትና ምርታማነት እያደገ ነው፡፡ ለዚህም ቴክኖሎጂ በማስተዋወቅ፣ በሽታ በመከላከል፣ መረጃ በመስጠት የገበያ ሥርዓትን በማሳለጥ፣ መጋዘኖችን በመገንባት እና ግብአት በማቅረብ ጥሩ ጥሩ ሥራ ተሰርቷል፡፡ ይህን በማሳየት ሥራው እየሰፋ የሚሄድበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

ንጋት፦ ሥራው በየትኞቹ አካባቢዎች ላይ ያተኩራል?

አቶ ገርማሜ፦ ሥራው በ66 ወረዳዎች ላይ እየተሰራ ነው፡፡ በደቡብ ምዕራብ፣ በቤንች ማጂ፣ ካፋ፣ ዳውሮ እና ኮንታ በበቆሎ እና በሰሊጥ እንዲሁም ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ባስኬቶ እና ደቡብ ኦሞ በበቆሎ፣ በሙዝ፣ በማንጎ እና በሰሊጥ ላይ ይሰራል፡፡ ጉራጌ እና ሀላባ ስንዴና ጤፍ፣ በስልጤ ስንዴ፣ ከምባታ ጠምባሮ በጤፍ፣ ሀዲያ ስንዴ፣ ጤፍና በቆሎ፣ የም በጤፍ ይለማል፡፡ በሲዳማ ላይ በቆሎ፣ ቲማቲም፣ አቨካዶ እና የመሳሰሉት ላይ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ቀጥሎም በሌሎች ወረዳዎች እየሰፋ የሚሄድ ይሆናል፡፡

ንጋት፦ አርሶ አደሩ የኩታ ገጠም ሥራውን ወደ ተግባር ቀይሮታል ማለት ይቻላል?

አቶ ገርማሜ፦ የግብርና ክላስተር መፍጠር ዋናው ተግባር በመሆኑ በደቡብ ከ50 በመቶ በላይ ግብርናው ኩታ ገጠም ሆኗል። ይህም አርሶ አደሩ ሥራውን ተቀብሎት እያሰፋ መሆኑን ያሳያል፡፡ ለማሳያነትም የስንዴና የጤፍ ሰብልን ስናይ ስንዴ ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ እንዲሁም ጤፍ ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ ኩታ ገጠም ሆኗል፡፡ ይህም በሰፊው የሚቀጥል ይሆናል፡፡

የግብአት አቅርቦት ማእከላት ክልሎች ደግፈውት በየወረዳው ወጣቶች እንደየፍላጎታቸው ተደራጅተው የሚሰሩ ሲሆን የግብርና ትራንስፎርሜሽን በሥራው የተወሰነ ድጋፍ ነው ያደረገው፡፡ አሁን ግን ያለምንም ድጋፍ ተቋቁመን እንስራ የሚሉ 35 የሚሆኑት ሥልጠና ብቻ በመስጠት ተቋቁመዋል፡፡

ንጋት፦ ህገ ወጥ የግብአት አቅርቦት ለመከላከል ምን እየተሰራ ነው?

አቶ ገርማሜ፦ ለአርሶ አደሩ አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ ግብአቶች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ማዳበሪያ በመንግስት አማካይነት የሚገባ ነው፡፡ ይህም ለዩኒየኖች ይከፋፈላል።

ስለዚህ በህገ ወጥ መንገድ የሚወጣበት መንገድ አይኖርም፡፡ ሌሎች ኬሚካሎች ድንበር አካባቢ ያሉ ሰዎች እንደማንኛውም ኮንትሮባንድ እቃ ሊያስገቡና ሊያሰራጩ ይችላሉ፡፡ በቁጥጥር የተያዘም አለ፡፡ ይህን ለመከላከል ታዲያ ጥራት ያለው ግብአት ከአስመጪዎች በመረከብ በተቋቋሙ የግብአት መሸጫ ማእከላት በማቅረብ ችግሩን መፍታት ይቻላል፡፡ ይህም እየተሰራበት ያለ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ዩኒየኖች ብቻ ለማቅረብ በቂ ባለመሆናቸው ከብሄራዊ ባንክ ጋር በመነጋገር በቀጥታ የሚያስመጡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ለዚህም በደቡብ ያሉ ዩኒየኖች ቀጥታ ከውጪ የሚያስገቡበት ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሰራ ይገኛል፡፡

ንጋት፦ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

አቶ ገርማሜ፦ ሥራውን ለብቻችን ሆነን የምንሰራው አይደለም፡፡ ስለዚህ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራን እንገኛለን፡፡ በዋናነት ከግብርና ቢሮ፣ ከንግድና ገበያ ልማት፣ ከህብረት ሥራ እንዲሁም ከውሃና መስኖ እና ሌሎችም ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው፡፡

የክልሉ ትራንስፎርሜሽን ሴንተር ዋና ሰብሳቢዎች ርእሰ መስተዳድሮች ናቸው። የዞን አስተዳዳሪዎች ደግሞ አባል ናቸው። ከዚያ ውጪ የእሴት ሰንሰለት ህብረት አለ። ከገበያ ልማት፣ ከነጋዴ፣ ከአስመጪዎችና ላኪዎች ጋር እንዲሁም ከፋብሪካዎች ጋር በጋራ እንሰራለን፡፡

ከእርሻ እስከ ጉርሻ ያለውን ሂደት በሙሉ አንድ ላይ አድርገን እንሰራለን፡፡ ለብቻ ሰርተን ችግሩን መፍታት አይቻልምና፡፡

ንጋት፦ ቀረ የሚሉት ሀሳብ ካለዎት?

አቶ ገርማሜ፦ አርሶ አደሩ ከዘልማድ አስተራረስ በመውጣት ዘመናዊ ግብርናን በመጠቀም ምርትና ምርታማነት እንዲያሳድግ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡ በዚህም የግብርና ትራንስፎርሜሽን ማእከል ሥራውን የበለጠ በማስፋፋት የሀገራችንን የግብርና ሥርዓት ዘመናዊ ለማድረግ የበለጠ እየሰራ ይገኛል። ማእከሉ ተልእኮውን ለማሳካት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ ሲሆን አሁንም ትብብሩን በማስቀጠል የሚሰራ ይሆናል፡፡

ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ገርማሜ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡