ከ25 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የትምህርት መሠረተ ልማት ማሻሻያ ፕሮግራም መጀመሩ ተገለጸ

ከ25 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የትምህርት መሠረተ ልማት ማሻሻያ ፕሮግራም መጀመሩ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከ25 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የትምህርት መሠረተ ልማት ማሻሻያ ፕሮግራም መጀመሩን የቤንች ሸኮ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

መምሪያው በጉራፈረዳ ወረዳና በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የተማሪዎች መማሪያ ክፍል ግንባታ ሳይት ርክክብ አድርጓል።

የቤንች ሸኮ ዞን ትምህርት መምሪያ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ማሻሻያ ፕሮግራም መጀመሩን የመምሪያው ኃላፊ አቶ ግዛው ሀይሌ ተናገረዋል።

የመማር ማስተማር ሥራውን ውጤታማ ማደረግ የሚቻለው የተማሪውን መማሪያ ክፍል ምቹ ማደረግ ሲቻል በመሆኑ በጉራፈረዳ ወረዳ ቢፍቱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጨማሪ አራት ክፍልን የያዘ አንድ ብሎክ በ5 ሚሊየን ብር ለማስገንባት ባለድርሻ አካላት ባሉበት የሳይት ርክክብ መደረጉን ኃላፊው ገልፀዋል።

አቶ አሸናፊ ዘሪሁን የጉራፈረዳ ወረዳ ምክትል አስተዳደሪና የግብርና አካባቢ ጥበቃ ህብረት ሥራ ጽፈት ቤት ኃላፊ በበኩላቸው፥ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ላበረከተው ድጋፍ አመስግነው እንደ ወረዳ መንግስት በየተኛውም ለሚታገዙ ሥራዎች የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ተናገረዋል።

ሥራው ሲጀመር ውጤታማ እስከሚሆን ድርስ የት/ቤቱ የወላጅ መምህራን ህብረትን ጨምሮ ሁሉም የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የጉራፈረዳ ወረዳ አስተዳደር ተጠሪ አቶ ኦይሳ አለሙ በበኩላቸው፥ በክረምቱ ከሚከናወኑ ተግባራት የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ መሠረተ ልማት ግንባታ አንዱ መሆኑን ገልፀው ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ በማደረግ በኩል የሰው ሀይልም ጨምሮ የተለያዩ ማቴሪያሎችን ለመደገፍ የማስተባበር ሥራ እንደሚያከናወኑም ተናገረዋል።

የዞኑ ትምህርት መምሪያ አንድ ብሎክ አራት ክፍል ያለው የመማሪያ ግንባታ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ያነጋገርናቸው የቢፍቱ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ማህበረሰቦች አመስግነው የትምህርት ልማት ሥራውን ተደጋግፎ በመሥራት በኩል ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።

በተመሳሳይም በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር በአማን ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትም አራት ክፍል ያለው አንድ ብሎክ ከ7 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ለመገንባትም የሳይት ርክክብ ተደረጓል።

በዚህን ወቅት የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ ግሩም ተማም በበኩላቸው በዞኑ ትምህርት መምሪያ በኩል የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሻሻል የተወሰደው ቁርጠኝነት የሚበረታታና የሚመሰገን ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።

ለከተማ አስተዳደሩ በዚህ ክረምት ወራት የሚጠናቀቅ ሁለት ፕሮጀክት መሰጠቱ ትልቅ ዕድል እንደሆነና ግንባታው እስኪጠናቀቀ ድርስ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደረጉም ተናገረዋል።

የዞኑ የትምህርት መምሪያ ኃላፊው አቶ ግዛው ሀይሌ በማጠቃለያቸው ለትምህርት ቤቶች የመሠረተ ልማት ማሻሻያ ፕሮጀክት ትኩረት መሰጠቱ የነገው ሀገር ተረካቢ የሆኑ ዜጎች የሚያፈሩት ተቋም በመሆኑ፥ ሁሉም ለግንባታው ስኬት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባቸው አስገንዘበዋል።

ትምህርት ቤቶችን ምቹ ከማደረግም ባሻገር በመልካም ስነ ምግባር የታነፀ ዜጋን ለማፍራት ወላጆች እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት የዘወትር ክትትልና ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አቶ ግዛው አፅንኦት ሰጥተዋል።

የቢፍቱ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ግንባታ ሳይት የተረከበው ኦሜጋ ጠቅላላ የሥራ ተቋራጭ ስራ አስኪያጅ አቶ ጫኔ ቶስ እና አቶ ታደሰ ወረቁ የታደሰ ወረቁ ጠቅላላ የሥራ ተቋራጭ በበኩላቸው ግንባታዎችን በተያዘለት ጊዜ አጠናቀው ለማሰረከብ ጥረት እንደሚያደረጉም ገልፀዋል።

በሳይት ረክክቡ የወረዳና የከተማ  አስተዳደሪዎች የት/ጽፈት ቤት ኃላፊዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን