በወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 322ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ 266 ሚሊዮን ብር የሚገመት የመንግስት ሀብት ለማዳን መታቀዱ ተጠቆመ

በወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 322ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ 266 ሚሊዮን ብር የሚገመት የመንግስት ሀብት ለማዳን መታቀዱ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዘንድሮ የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዞኑ 322ሺህ በላይ  ወጣቶችን በማሳተፍ 266 ሚሊዮን ብር የሚገመት የመንግስት ሀብት ለማዳን ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ የሀዲያ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ገለፀ።

በዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የ2015 ዓ.ም የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በዞኑ ፎንቆ ከተማ አስተዳደር ተካሄዷል።

የሀዲያ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሻለ ደሳለኝ በፕሮግራሙ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በጎነት ለኢትዮጽያ ከፍታ በሚል መርህ በሚካሄደው በዚህ ትልቅ ተግባር ቤት ለሌላቸው ገንብቶ በመስጠት፣ ቤት ውስጥ ተጠልለው እንዲያድሩ ማድረግና መሰል በጎ ተግባራት ከወጣቶቹም ባሻገር ለትውልድ የበጎነትን አሻራ ማኖሪያ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።

በዘንድሮ የወጣቶች የክረምት በጎ ተግባራት በዞኑ 322ሺህ 900 ወጣቶችን በማሳተፍ 266 ሚሊዮን ብር የሚገመት የመንግስት ሀብት ለማዳን ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገለጸው፥ ሁሉም ወጣቶች በበጎ ተግባራቱ በመሳተፍ አሻራቸውን ሊያኖሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ በበኩላቸው፥ መርኃ ግብሩ ለሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና የወጣቶችን ባለቤትነት ማረጋገጥን ዓላማ ያደረገ መሆኑን አንስተው በጎነትን ወጣት ላይ ማስረጽ ደግሞ ለቀጣይ በጎ ማህበረሰብ የመፍጠርን እድል ከፍ ያደርጋል ብለዋል።

ሀገር በበጎ አሳቢ ትውልድ ይገነባል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው እንዲህ ዓይነት ተግባራት የተሸረሸሩብንን ነባር በጎ እሴቶቻችንን ማስመለሻም ጭምር እንደሆ ጠቁመዋል።

አቶ አብርሃም አክለውም በጎነት ለራስ መሆኑን አንስተው ሀገራችን ባለፉት ጊዜያት ተጋርጦባት የነበረን ፈተና በዜጎቿ የተባበረ ክንድ በድል በተሻገረችበት ብሎም በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር  በአንድ ጀምበር 5 መቶ ሚሊየን ችግኞችን በመትከል ሀገራዊ ተልዕኮን ባሳካንበት ማግስት መሆኑ የዘንድሮን የወጣቶች የክረምት በጎ ተግባር ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

በክረምት በጎ ተግባራት መስጀመሪያ መርግብር ወቅት ያነጋገርናቸው አንዳንድ ወጣቶች በበኩላቸው ከዚህ ቀደምም በተለያዩ በጎ ተግባራት በመሳተፍ ከህብረተሰቡ ጎን መሆናቸውን አንስተው ተግባራቱ በአንድ ወቅት ታይተው  የሚጠፉ ሳይሆኑ  በዘላቂነት የሚያስቀጥሉት  ተግባር እንደሆነ ገልፀዋል።

“በጎነት ለኢትዮጲያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው መርኃ ግብር የችግኝ ተከላና የአረጋዊያን ቤት የማደስ ተግባራት ተከናውነውበታል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን