በፌደራል እና በክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አዘጋጅነት የፌደራል፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተሮች 22ኛ ዓመታዊ ጉባዔ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው

በፌደራል እና በክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አዘጋጅነት የፌደራል፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተሮች 22ኛ ዓመታዊ ጉባዔ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 08/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በፌደራል እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አዘጋጅነት የፌደራል፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተሮች 22ኛው ዓመታዊ ጉባዔ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

ዋና ኦዲተር መ/ቤት ገለልተኛ የሆኑ የኦዲት አገልግሎቶችን በማከናወን የመልካም አስተዳደርና የመንግሥት ተቋማት አፈጻጸም ውጤታማነትን ለማጎልበት እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት፤ዋና ኦድተር መ/ቤቱ የመንግሥት ሐብትና ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋል እንዲቻል አሠራሮች ህጋዊ መሠረት እንዲይዙ በማድረግ እያከናወነ ያለው እንቅስቃሴ የላቀ ነው።

የክዋኔ ኦዲት በተገቢው መደረጉ ከዕውቀት ማነስ ለሚፈጠሩ ችግሮች ድጋፍ መደረግና በአሠራር ጥሰት የሚፈጸሙ ጉድለቶች በሕጋዊ አሠራር እንዲጠየቁ እየተሰሩ ያሉት ተሞክሮዎች አበረታች እንደሆነ አመላክተዋል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወንድሙ ኩርታ እንደገለጹት፤ የክልሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤት አዳዲስ ባለሙያዎችን በመያዝ የድጋፍና ክትትል ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል  የላቀ ሥራ እየሰራ ይገኛል።

ዓለም አቀፍ የኦዲት ተቋማት መመዘኛዎችን መሠረት በማድረግና ገለልተኛ የሆኑ የኦዲት አገልግሎቶችን በማከናወን የመልካም አስተዳደርና የመንግሥት ተቋማት አፈጻጸም ውጤታማነትን በማጎልበት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሃላፊ ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ገልጸዋል።

በሀገር ደረጃ የሚገኙ የፌደራል፣ የክልልና የከተማ ኦዲተሮች ዘመናዊ አሠራርን በመከተል ዓለም አቀፋዊና ደረጃውን የጠበቀ የኦዲት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ኃላፊዋ አክለዋል።

ለ22ኛ ጊዜ የሚደረገው ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን ሁሉም ከፍተኛ ባለድርሻ አካላት አስተዋጽዖ ማበርከቱን የገጹት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ይህን ጉባዔ ለየት የሚያደርገው ደግሞ የትግራይ ክልል ዋና ኦድተር ኃላፊዎች ተሣታፊ በመሆናቸው ነው ብለዋል።

በፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የውጭና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የፋይናንስ ጉዳይ አስተባባሪ አቶ ኢዮብ ጉታ በ4ቱም ክልሎች የተካሄደውና ለክልሎች የተሠጠውን የድጋፍና ድጎማ በጀት የነጠላ ኦዲት አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።

ጉባዔው በቆይታው የቀረቡትን አፈጻጸም ሪፖርቶችን በመገምገምና ውይይት በማድረግ  የቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል አቶ ኢዮብ ጉታ።

የጉባዔው ተሳታፊዎችም የነቃ ተሳትፎ በማድረግና ልምዳቸውን በማጋራት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

በቦንጋ ከተማ እየተደረገ ባለው ጉባኤ ላይ የተለያዩ የክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዘጋቢ፡ መለሠ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን