ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በግብጽ የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ ነበር – ዶክተር ለገሰ ቱሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በግብጽ የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ ነበር – ዶክተር ለገሰ ቱሉ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በግብጽ የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በግብጽ፥ ካይሮ በተካሄደው ‘የሱዳን ጎረቤት አገራት ጉባዔ’ የነበራቸውን ተሳትፎ አስመልክቶ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በግብጽ ቆይታቸው ሦስት አበይት ተግባራትን በተሳካ መልኩ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

በመጀመሪያም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መሰረተ-ልማት የተሟሉለት ዘመናዊውን አዲሱ ካይሮን መጎብኘታቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም የኃይማኖት ተቋማት፣ ሙዚየምና ሌሎች ሥፍራዎችን መጎብኘታቸው ጠቁመው ጉብኝታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ የሚሆን ልምድ መቀመራቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር የተሳካ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በነበራቸው የሁለትዮሽ ስብሰባ አገራቱ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ከሥምምነት መድረሳቸውን ገልጸዋል።

አገራቱ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ቀጣይ የትብብር ዘርፎች እንዲሁም በአካባቢያዊ ሰላምና ደኅንነት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው መምከራቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የጋራ ተጠቃሚነት መርህን መሰረት ያደረገ ትብብር ለሁለቱ አገራት ሕዝቦች ዘላቂ ጥቅምና ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን መሪዎቹ ከመግባባት መድረሳቸውን አንስተዋል።

ሁለቱ አገራት በመተማመን መንፈስ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋለውን አለመረጋጋት ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ ለቀጣናው ልማት ወሳኝ መሆኑን መሪዎቹ አጽንኦት ሰጥተዋል ነው ያሉት።

ይህንን ለማድረግ ሁለቱ አገራት ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት በመከባበርና በሰጥቶ መቀበል መርህ አጋርነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው መወያየታቸውን ተናግረዋል።

የሱዳንን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት በግብጽ ካይሮ የመከሩት የጎረቤት አገራት መሪዎች ተፋላሚ ኃይሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ሥምምነት እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

በችግር ላይ የሚገኙ ሱዳናውያን ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያገኙና ሁለቱ ኃይሎች ሁሉን አቀፍ ውይይት በፍጥነት እንዲጀምሩ መሪዎቹ ከሥምምነት መድረሳቸውንም ተናግረዋል።

ይህም ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የሱዳን ሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረገ መልኩ መከናወን እንዳለበት መሪዎቹ የውሳኔ ሃሳብ ማሳለፋቸውንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በተመሳሳይ የሱዳን ችግር እንዲፈታ እንዲሁም ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ያላትን ጽኑ አቋም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውንም አብራርተዋል።