የኢትዮጵያን ከፍታን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ ወጣቶች ግንባር ቀደም ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጌዴኦ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ከገደብ ወረዳ አስተዳደር ጋር በመተባበር “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የ2015 ዓ.ም ክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዞናዊ የመክፈቻ መርሐ ግብር በገደብ ወረዳ በገልቻ ቀበሌ አካሂደዋል።

የገደብ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አዲሱ አየለ እንደተናገሩት፥ በወረዳው ባለፉት ጊዜያት ወጣቶች የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በመሳተፍ፣ በደም ልገሳ፣ በክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት፣ ለወላጅ አጥ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስና አልባሳት በማሰባሰብ ተግባራት ላይ በመሳተፍ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በ2015 ዓ/ም በበጋ ወራት 105 ያረጁ ቤቶችን በማደስ ለሕብረተሰቡ ግልጋሎት ማዋላቸውን የጠቆሙት አቶ አዲሱ፥ በክረምቱ የበለጠ ውጤት ለማምጣት የግንዛቤ ትምህርት መስጠታቸውን አስረድተዋል።

የጌዴኦ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደግነት ኃይሉ በበኩላቸው፥ የ2015 ዓ.ም የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶች በስፖርት፣ በጤና፣ በሰላምና ጸጥታ፣ በከተማ ጽዳትና ውበት፣ በኮንትሮባንድ ቁጥጥርና በሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎቶች በንቃት በመሳተፍ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አብራርተዋል።

“በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የ2015 ዓ.ም የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተጀምሯል።

በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በ15 የትኩረት መስኮች 234 ሺህ አንድ መቶ ወጣቶችን በማስተባበር 600 ሺህ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራበት አቶ ደግነት ተናግረዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር የዞኑ ወጣቶች ቀደም ሲል በሰው ሕይወትና በእንስሳት ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው አጎራባች ዞኖችና ክልሎች ድንበር ተሻጋሪ አገልግሎት በመስጠት በክልሉና በፌዴራል መንግሥት ዕውቅና መቸራቸውን አስታውሰዋል።

በዘንድሮ ዓመትም በመንግሥት ያልተሸፈኑ የልማት ሥራዎችን በማሟላት ለሕብረተሰቡ ነጻ አገልግሎት በመስጠት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡና ለሀገር ያላቸውን አጋርነት እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።

በዞን ደረጃ ከአንድ ሺህ በላይ አሮጌ ቤቶችን ጠግነው ለአቅመ ደካሞች ለማስረከብ ታቅዶ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ የጠቆሙት አስተዳዳሪው 182 ሚሊዮን ብር ከብክነት ለማዳን እንደሚሠራም አብራርተዋል።

የሚመለከታቸው ክፍሎች ሁሉ ለወጣቶቹ ምቹ የአገልግሎት ስነምህዳር በመፍጠር የበኩላቸውን  እንዲወጡም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ እስራኤል ብርሃኑ – ከፍሰሃገነት ጣቢያችን