የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ መክፈላቸው የንግድ ስራቸውን በነፃነት እንዲሰሩ እንዳስቻለቸው የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ተናገሩ

የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ መክፈላቸው የንግድ ስራቸውን በነፃነት እንዲሰሩ እንዳስቻለቸው የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ መክፈላቸው ለአካባቢያቸው ልማት የድርሻቸውን ከመወጣታቸው ባሻገር የንግድ ፈቃዳቸውን በማደስ በተሰማሩበት የንግድ ስራ በነፃነት እንዲሰሩ እንዳስቻለቸው አንዳንድ የጠምባሮ ወረዳ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ተናገሩ።

የወረዳው ገቢዎች ቅ/ጽ/ቤት የታዳጊ ማዘጋጃ ቤቶች አቅም በማጎልበት ወረዳው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመስብሰብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የ2015 ግብር ዘመን ከሐምሌ 1 ጀምሮ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች የግብር አሰባሰብ በቀለጣ ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።

የሚጠበቅባቸውን የዘመኑን ግብር ሲከፍሉ ካነጋገርናቸው የቀለጣ ከተማ ግብር ከፋዮች መካከል ወጣት ማንደሩ መነቻ እና ኃይሌ በሰጡን አስተያየት የምንከፍለው ግብር ተመልሶ ለልማት የሚውል መሆኑን በመረዳት የተጣለባቸውን ግብር በወቅቱና በታማኝነት መክፈላቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው ሰፊ የመሰረተ ልማት ስራዎች ሊሟሉ እንደሚገባ የሚገልጹት ግብር ከፋዮቹ፥ በተሰማሩበት የንግድ ዘርፍ የመብራት መቆራረጥ ቢቀረፍላቸው በየአካባቢያቸውን ልማት ከማገዝ ወደ ኃላ የሚያግድ አንዳች ነገር እንደማይኖር ጠቁመዋል።

አዲስ የገቢ ግመታ ተጥሎ ከአቅማቸው በላይ ቢሆንም ግብራቸውን ከፍለው በማጠናቀቃቸውና የንግድ ፈቃዳቸውን በማሳደሳቸው ስራቸው በነፃነት እንዲሰሩ እንዳስቻላቸው አስተያየት ሰጪዎቹ አመላክተዋል።

በወረዳው ገቢዎች ባለስልጣን ቅ/ጽ/ቤት ትምህርትና ስልጠና ባለሙያዋ አይናለም ኦርሽሶ በሰጡን አስተያየት አዲሱን የገቢ ግብር ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ከግብር ከፋዮች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎ ገቢውን የመሰብሰብ ስራ መጀመሩን ገልፀው፥ ግብር ከፋዩም አዲሱን የገቢ ግመታ እየከፈለ መሆኑን ገልፀዋል።

የወረዳው ገቢዎች ባለስልጣን ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥበቡ ታገሰ በበኩላቸው ወረዳው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ የታዳጊ ማዘጋጃ ቤቶች አቅም ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው የተለያዩ የገቢ ምንጮችን በመለየት በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ከእቅድ በላይ መፈፀም መቻሉን የገለጹት አቶ ጥበቡ፥ ገቢን በመሰብሰብ የህዝቡን ልማት ለማገዝ ሲል የሚያደርገውን የነቃ ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ግብር የማስከፍልና የንግድ ፈቃድ የማደስ ስራ ከንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ጋር በቅንጅት የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም ኃላፊው ገልፀዋል።

ዘጋቢ: ጡሚሶ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን