በሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል የመድሀኒት አቅርቦት ችግር እንዲፈታላቸው የሆስፒታሉ ተገልጋዮች ጠየቁ

በሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል የመድሀኒት አቅርቦት ችግር እንዲፈታላቸው የሆስፒታሉ ተገልጋዮች ጠየቁ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል የሚታየው የመድሀኒት አቅርቦት ችግር እንዲፈታላቸው የሆስፒታሉ ተገልጋዮች ጠየቁ።

ሆስፒታሉ የ2015 በጀት ዓመት የ4ኛ ሩብ ዓመት የማህበረሰብ አቀፍ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

ከሆስፒታሉ  ተገልጋዮች መካከል አቶ መሰለ ማሳ፣ መምህርት ምናሉሽ ዘለቀ እና አቶ አብርሃም ስሪና  በጋራ እንደገለጹት በሆስፒታሉ የሚሰጡ የእናቶችና ህጻናት፣ የቀዶ ጥገና፣ የተመላላሽና ተኝቶ ህክምና አገልግሎቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ መምጣታቸውን አስረድተዋል።

በሆስፒታሉ ለረጅም ጊዜ በተለያየ ምክንያት አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ የህክምና መገልገያ መሣሪያዎች ጥገና ተደርጎላቸው አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው አስተያዬት ሰጪዎቹ አድንቀዋል።

ተገልጋዮች አክለውም በሆስፒታሉ የመድሀኒት አቅርቦት ችግር ጎልቶ የሚታይ በመሆኑ ከግል መድሀኒት መደብሮች በመግዛት ለከፍተኛ ወጪ እና እንግልት እየተዳረጉ በመሆናቸው ችግሩ እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።

የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ሊቃውንት አዛዘ በበኩላቸው፥ ሆስፒታሉ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ መቆየቱን ጠቁመው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል የተገልጋዩን ማህበረሰብ እርካታ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የተነሳው የተገልጋዮች ቅሬታ ተገቢ መሆኑን ጠቁመው፥ ለጤና መድህን እና ለዱቤ ህክምና ከሆስፒታሉ ጋር ውል የገቡ ተቋማት በወቅቱ ክፍያ ባለመፈጸማቸው ሆስፒታሉን ባጋጠመው የበጀት ዕጥረት ችግሩ መፈጠሩን አንስተው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት አቅም በማጠናከር ሰሞኑን አቅርቦቱን ለማሻሻል ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በተቋሙ የሚስተዋለውን የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል በሆስፒታሉ በ2015 በጀት ዓመት 1 ሺህ 37 ሕሙማን ድንገተኛ የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ጠቅሰው፥ በሆስፒታሉ ቀደም ሲል የሚስተዋለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር መፈታቱንም ገልጸዋል።

የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ማኖተ በበኩላቸው፥ ሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሻሻል ከማህበረሰቡ ጋር የጀመረውን ውይይት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የሆስፒታሉን አቅም በማጠናከር የተገልጋይ እርካታ ለማሳደግ መምሪያው ከዞን አስተዳደር ጋር በመቀናጀት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በአካባቢው የደም ባንክ አገልግሎት ባለመኖሩ ምክንያት በርካታ እናቶቻችና ሕፃናት ለሞት መዳረጋቸውን ጠቅሰው የተጀመረው የደም ባንክ ግንባታ ሲጠናቀቅ ቀደም ሲል የነበረው ችግር በዘላቂነት እንደሚቀርፍና ለዞኑ እና ለአጎራባች ወረዳዎች የደም ባንክ አገልግሎት እንደሚሰጥ አንስተዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን