80 ከመቶ በላይ የዓለም ህዝብ የባህል ሕክምና ተጠቃሚ  መሆኑን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከባህል ሕክምና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በህብረተሰቡ ዘንድ የተለያዩ እይታዎች ቢኖሩም 80 ከመቶ በላይ የዓለም ህዝብ የዘርፉ ተጠቃሚ መሆኑን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ።

የባህላዊ ሕክምና አጠቃቀም ምጣኔና ፈዋሽነት በቤተ ሙከራ የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢፌዴሪ  ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮ መፍትሄ ሀገር በቀል የባህል ሕክምና ማዕከል ባለሙያ አቶ ማስተዋል አለሙ እንደገለጹት  የባህል ሕክምና ለዘመናዊ ሕክምና መሠረት ነው። ዘርፉ ከቀደምት አባቶች ሀገረሰባዊ እውቀት እየተሸጋገረ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚተላለፍ የሕክምና ዘርፍ ሲሆን ለተለያዩ ዓይነት በሽታዎች ፈውስ በመሆን እንደሚታወቅም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የማህበራዊ እሴት ልማት ባለሙያ ኢንጂነር ፈቃዱ ኃይሌ በዓለም ውስጥ 80 ከመቶ በለይ ህዝብ ባህላዊ ሕክምና እንደሚጠቀም የዓለም ጤና ድርጅት መረጀ ያመለክታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የባህል ሕክምና መረጃዎች ዲጂታል የማድረጉን ሥራ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እየሠራ እንደሚገኝም ኢንጂነር ፍቃዱ አስታውቀዋል።

በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ሀርማው ሀንሰን ጥናት ኢንስቲትዩት የባህልና ዘመናዊ መድኃኒት ምርምር ባለሙያ ትዕግሥት ፍሰሃ በበኩሉዋ የባህል ሕክምና መድኃኒቶችን አጠቃቀም ምጣኔና የፈዋሽነት ደረጃቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የቤተ ሙከራ ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግራለች።

በየመንገዱ ከሚሸጡ የባህል መድኃኒቶች መከከል አንደንዶቹ መርዛማ የሆኑ ሊኖሩ ስለሚችሉ በጤና ላይ የጎንዮሽ ችግር ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ተጠቃሚው ህብረተሰብ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ብላለች።

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ባዘጋጀው የጤና ኢግዚቢሽን የተለያዩ ባህላዊና ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎቶችና ምርቶች ለእይታ ቀርበዋል።

በእስካአሁኑ ቆይታ ከመቶ ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ኢግዚቢሽኑን ስለመጎብኘታቸው የተገለፀ ሲሆን በየዕለቱ በአማካይ ከ5 ሺህ ህዝብ በላይ እየጎበኘው እንደሚገኝ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጀ አመላክቷል።

የሲደማ ክልል ጤና ቢሮ ሠራተኞችና የዘርፉ ኃላፊዎችም የጤና ኢግዚቢሽኑን ጓብኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ጌታሁን አንጭሶ