የህብረተሰቡን የመሠረተ-ልማት ፍላጎት ለማሟላት የውስጥ ገቢን አሟጦ መሰብሰብ ወሳኝ ተግባር በመሆኑ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 03/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የህብረተሰቡን የመሠረተ-ልማት ፍላጎት ለማሟላት የውስጥ ገቢን አሟጦ መሰብሰብ ወሳኝ ተግባር በመሆኑ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ የሀዲያ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።
በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች የግብር አከፋፈሉ ሂደት ከጅምሩ ስኬታማ መሆኑም ተገልጿል።
በሀዲያ ዞን ጃጁራ ከተማ አስተዳደር 437 በ’ሐ’ የግብር ከፋይነት የተመደቡ ሲሆን 2 ሚሊየን 1መቶ 36ሽህ 227 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በአጭር ሰዓታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ማሳካት እንደተቻለ የከተማው ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ማዳሞ ገልፀዋል።
በግብር መሰብሰብ ሂደቱ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በነጋዴው ዘንድ ቀደም ብሎ በመሰራቱ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ኃላፊው ተናግረዋል።
ልማትና ገቢ የማይነጣጠሉ እንደመሆናቸው ባለፉት ዓመታት በተሰበሰበው ገቢ ግዙፍ የልማት ስራዎች በከተማው መጀመራቸውን የገለፁት የጃጁራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ብርሃኑ ፋንታዬ የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎች ከግብ እንዲደርሱ ግብር ከፋዩ በታማኝነት የሚጠበቅበትን በወቅቱ መወጣት ይገባዋል ብለዋል።
የአካባቢውን ማህበረሰብ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ ሊሰጥ የሚችልና የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የጤና ጣቢያ የማስፋፊያ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ከንቲባው ጠቁመዋል።
በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የ’ሐ’ የግብር አከፋፈል ሂደት በይፋ መጀመሩን የገለፁት ደግሞ የሀዲያ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ መሳይ ተስፋዬ በአንዳንድ ከተማ አስተዳደሮች ከጅምሩ ስኬታማ የግብር አከፋፈል ሂደት መታየቱን አስረድተዋል።
“ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ ቃል የንቅናቄ ስራው በስፋት ከመከናወኑ ባሻገር የመንግስት መዋቅሩና ነጋዴው ማህበረሰብ በመግባባታቸው ጉብኝት ባደረጉበት የጃጁራ ከተማ አስተዳደር በአጭር ሰዓት ውስጥ ማጠናቀቅ ተችሏል ብለዋል።
በጃጁራ ከተማ አስተዳደር በግብር ማስጀመሪያው መርሃግብር የዞንና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች የተገኙ ሲሆን በዕለቱ ግንባር ቀደም ለሆኑ ግብር ከፋዮችም የዕውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ፡ ዳኜ አየለ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አለማየሁ ባውዲ በክልሉ የሚገኙ የየተለያዩ ብሔሮች ዘመን መለወጫ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ !!
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አት ደመቀ መኮንን በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ንግግር አደረጉ
300 ለሚሆኑ ወላጅ አጥ ተማሪዎች ኢትዮ- ቴሌኮም ሳውላ ድስትሪክት ከ270 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ