ገቢን በመሰብሰብ ለአካባቢው ሁለንተናዊ ልማት ለማዋል የሚደረገዉ ጥረት ስኬታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል – በካፋ ዞን የዴቻ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት

ገቢን በመሰብሰብ ለአካባቢው ሁለንተናዊ ልማት ለማዋል የሚደረገዉ ጥረት ስኬታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል – በካፋ ዞን የዴቻ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ገቢን በመሰብሰብ ለአካባቢው ሁለንተናዊ ልማት ለማዋል የሚደረገዉ ጥረት ስኬታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ በካፋ ዞን የዴቻ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት ገለጸ።

ጽ/ቤቱ ከሀምሌ 01 ቀን 2015 ጀምሮ የሚከናወነውን የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮችን ገቢ ለመሰብሰብ የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አካሂዷል።

በመረሃ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ጥራቱ ገ/ዮሐንስ አሁን ላይ በወረዳው በተለያዩ ዘርፎች የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ወሳኝ ነዉ ብለዋል።

ይህን ማድረግ እንዲቻል የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮችን ግብር ከወቅቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር ማጣጣም እንዲቻል አዲስ የዕለት ሽያጭ ትመና መከናወኑን ተናግረው በዚህ ስራ በወረዳው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 284 ህገ-ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ ማዕቀፍ ማስገባት መቻሉንም ገልጸዋል።

ከሀምሌ 03 ቀን 2015 ጀምሮ በሚከናወነው የደረጃ “ሐ” ገቢ አሰባሰብ ከ3 ሚሊዮን 5 መቶ 77 ሺህ ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን ያብራሩት አቶ ጥራቱ ለስኬቱም የባለድርሻ አካላትን ትብብር ጠይቀዋል።

የንቅናቄ መድረኩን የመሩት የወረዳው ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አስራት አደቶ በወረዳዉ ያለውን እምቅ አቅም በአግባቡ በመለየት ገቢን መሰብሰብ ይገባል ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ የአመለካከትና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ኃላፊነታቸዉን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመድረኩ ላይ የወረዳው ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤን ጨምሮ የሁሉም ቀበሌ አስተዳዳሪዎች፣ የወረዳ አስተባባሪዎች፣ የማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጆችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ግብርን በወቅቱ በመሰብሰብ ለታለመለት ዓላማ ለማዋል የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን