በ30″ 40″ 30″ ፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት የተሻለ ውጤት አስመዘገበ – የባስኬቶ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት

በ30″ 40″ 30″ ፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት የተሻለ ውጤት አስመዘገበ – የባስኬቶ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ30″ 40″ 30″ ፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን የባስኬቶ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ገለጸ።

በልዩ ወረዳው በመንግስታዊ ተቋማትና በግለሰብ ግቢ ክፍት ቦታዎች ባለፈው አንድ አመት 30 ሺህ የፍራፍሬ ችግኞች መተከላቸውም ተመላክቷል።

በልዩ ወረዳው ላስካ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ በግብርና ጽ/ቤትና በተለያዩ ግለሰቦች ግቢ በሚገኙ ክፍት ይዞታዎች ላይ የተተከሉ የፍራፍሬ ችግኞች ይበል የሚያሰኝ ምርት ሰጥተዋል።

የአታክልትና ፍራፍሬ ልማቱ ያለበት ደረጃ በአመራሮች በተጎበኘበት ወቅት ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ለማ መንገሻ እንደተናገሩት ባሳለፍነው አመት ከ30 ሺህ በላይ ችግኞች በ17 የተመረጡ ቀበሌያትና በ102 መንደሮች የተተከሉ ሲሆን ዛሬ ለፍሬ ደርሰዋል ብለዋል።

የላስካ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ታሪኩ በበኩላቸው በሆስፒታሉ ግቢ 4 ሺ የሙዝ ችግኞችን በመትከል ለፍሬ የደረሱ ሲሆን የግቢው ሰራተኛና አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ ደንበኞችን በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

30″40″30″ ፍራፍሬ ልማት ስራን ከሌማት ትሩፋት ፕሮጀክት ጋር በማስተሳሰር የሚተገበር መሆኑን የተናገሩት የባስኬቶ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታመነ ታምርሶ በተለይ በሙዝ፣ አቮካዶ፣ ማንጎ ሌሎችም የአትክልት ልማቶች የተገኘውንም ውጤት በመቀመር በሌሎች ተቋማትም እንዲስፋፉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን