የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታልን ወደ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ

የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታልን ወደ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 28/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታልን ወደ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለማሳደግ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ሆስፒታሉ አስታውቋል፡፡

ሆስፒታሉ ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ሚሺገን ባገኘው ድጋፍ የአዋቂ ድንገተኛ፣ የእናቶችና ህጻናት ህክምና ክፍል የያዘ ህንጻ እያስገነባ ይገኛል፡፡

የግንባታው ሂደት በሆስፒታሉ የቦርድ አባላት ተጎብኝቷል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አንዱአለም መንግስቱ እንደገለጹት ሆስፒታሉ 2 ሚሊየን ለሚደርሱ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

ሆስፒታሉን ወደ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ደረጃ ለማሳደግ ግብ አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አቶ አንዱአለም ጠቁመው በዚህም የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን ለመሙላት የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል ፡፡

ኮሚቴው በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ የአካባቢው ተወላጆችና ግብረሰናይ ድርጅቶችን ለማሳተፍ ባደረገው ጥረት ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ሚሺገን የስነተዋልዶ ጤና የስልጠና ማዕከል ጋር የሁለትዮሽ ውል መገባቱን ተናግረዋል ፡፡

ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ሚሺገን ጋር በተገባው ውል ለአዋቂ ድንገተኛ እና ለእናቶችና ህጻናት የተሟላ ህክምና ለመስጠት የሚያስችል በ2ሺ 530 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የህንጻ ግንባታ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ግንባታው አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ተገቢውን ህክምና መስጠት የሚያስችል እንደሆነ አቶ አንዱአለም ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው የህንጻው ግንባታ ሲጠናቀቅ የህክምና መስጫ መሳሪያዎች እንደሚያሟላ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደተናገሩት በሆስፒታሉ እየተከናወነ ያለው ግንባታ ሆስፒታሉን ወደ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለማሳደግ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ያስችላል፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባላቸው ዕውቀትና አቅም በጤናው ዘርፍ ለአገራቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሆስፒታሉ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ በቀለ አየለ በበኩላቸው ሆስፒታሉ መሰረቱ የህዝብ ተሳትፎ እንደሆነ ተናግረው ኮሚቴው የሆስፒታሉን ደረጃ ለማሳደግ ህብረተሰቡንና ግብረሰናይ ድርጅቶችን በማሳተፍ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡

በሆስፒታሉ እየተከናወነ ያለው ግንባታ በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ የተናገሩት አቶ በቀለ መሟላት ያለባቸው ቀሪ ግብአቶችን ለማሟላት እንደሚንቀሳቀሱ አስታውቀዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ ሰለሞን ጉግሳ የሆስፒታሎች አደረጃጀት በማሳደግ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል እየተከናወነ ያለው ግንባታ ቀደም ሲል ህዝቡ ሲያነሳ የነበረውን የደረጃ ማሳደግ ጥያቄ የሚመልስና ለህብረተሰቡ የተሟላ ህክምና ከመስጠት በተጨማሪ እንግልትና አላስፈላጊ ወጪ ያስቀራል ብለዋል ፡፡

ዘጋቢ፡ አለምሰገድ ኢስጢፋኖስ- ከወልቂጤ ጣቢያችን